ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ በድል ጉዞው ቀጥሏል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ሳምንት ሦስተኛ ጨዋታ ዛሬ ረፋድ 4:00 ላይ ተካሂ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድሬዳዋ ከተማን 2 ለ 1 በማሸነፍ ተከታታይ ሦስተኛ ድሉን አስመዝግቧል፡፡

ሀዋሳ ላይ እየተደረገ ያለው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አስረኛ ቀኑ ላይ ይገኛል፡፡ በሦስተኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከ ድሬዳዋ ከተማ አገናኝቷል፡፡ ተመሳሳይ የመሐል ሜዳ እንቅስቃሴ አዘንብሎ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኤሌክትሪኮች የመሐል ሜዳውን ክፍል ከመስመር ተከላካይነት ወደ መሐል ሜዳ ተመልሳ ስትጫወት የተመለከትናት እፀገነት ብዙነህ እና ሰሚራ ከማል በማዋሀድ እና በፅዮን ፈየራ ሚዛን አጠባበቅ ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል ተጠግቶ ለመጫወት ጥረቶችን አድርገዋል፡፡

ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው በማዕድን ሳህሉ ላይ ትኩረትን ያደረገ ነገር ግን በረጃጅሙ በሚጣሉ ዕድሎች በቁምነገር ካሳ እና ፀጋነሽ ወራና ማጥቃት አማራጫቸው አድርገዋል ይሁን እንጂ ወደ ግብ ተጠግቶ ከመሞከር ይልቅ ከርቀት ያገኙትን አጋጣሚ ወደ ግብ መለጋትን ምርጫቸው በማድረጋቸው በቀላሉ ኳሶቻቸው ሊባክኑ ችለዋል፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች መሐል ሜዳ ላይ ገና ከጅምሩ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበረችው ሰሚራ ከማልን 10ኛው ደቂቃ ላይ በጉዳት በማጣቱ በምትኩ ቤዛዊት ተስፋዬ ተክታት ገብታለች። አማካይዋም ወደ ሜዳ እንደገባች ባደረገችው አስደናቂ ብቃት ከብዙዎች አድናቆት ተችሯታል፡፡

12ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ተከላካዮች የአቋቋም ስህተት ታክሎበት ቤዛዊት መሐል ለመሐል የሰጠችውን ኳስ ከተለመደው የመስመር አጥቂነት ቦታ ወደ ፊት አጥቂነት አድልታ ስትጫወት የነበረችው ወርቅነሽ ሜልሜላ አግኝታ ወደ ጎልነት ለውጣ ኤሌክትሪክን መሪ አድርጋለች፡፡ በተመሳሳይ ወርቅነሽ ከቅጣት ምት ጥሩ ዕድልን ብታገኘም በቀላሉ አምክናዋለች፡፡
ድሬዳዋ ከተማዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ ረጃጅም ኳስ ላይ ትኩረት አድርገዋል። በዚህም መንገድ የተገኙትን ሁለት ዕድሎች የቀድሞዋ የአርባምንጭ ከተማ የመስመር አጥቂ ፀጋነሽ ወራና ሁለት ጊዜ ሞክራ ብረት የገጨባት ድሬዳዋ ከተማዎችን ምናልባት አቻ የሚያደርጉ ያለቀላቸው ንፁህ የግብ አጋጣሚዎች ቢሆንም ወደ ውጪ ወጥተውባታል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ድሬዎች በተወሰነ መልኩ የጨዋታ ቅርፅ ለመያዝ ቢሞክሩም የኢትዮ ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ መሠረት ማኔ መሠሉ አበራን ቀይራ በማስገባት እፀገነትን ወደ ተከላካይ ስፍራ እንዲሁም ሳራ ነብሶን በፊት አጥቂነት ቀይራ ካስገባች በኃላ ቡድኑ ወደ መከላከል አዘንብሎ በሚገኙ ዕድሎች በቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመሄድ የተከተሉት የጨዋታ መንገድ ውጤታማ ያደረጋቸው ነበር፡፡

ድሬዳዋ ከተማዎች ኃይላቸውን አሟጠው ወደ ማጥቃት ወረዳ ብቅ ባሉበት ጊዜ አስገራሚዋ አማካይ ቤዛዊት ተስፋዬ 81ኛው ደቂቃ ላይ የሰጠቻትን ኳስ ተቀይራ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ያደረገችሁ ሳራ ነብሶ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ 2 ለ 0 መሪነት ያሸጋገረችዋን ግብ አስቆጥራ የግብ መጠኑን ከፍ አድርጋለች፡፡

መደበኛ የጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ለክለቧ ጎል ለማስቆጠር ነቅላ የመጣችው አምበሏ አሳቤ ሙሶ ለድሬዳዋ ግብ አስቆጥራ ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት ሁለት ወደ ግብነት የተለወጡ ኳሶችን ያቀበለችው ቤዛዊት ተስፋዬን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡

ጊዜያዊ ሰንጠረዥ
# ክለብ ተጫ ልዩ ነጥብ
1 ኤሌክትሪክ 3 3 9
2 መከላከያ 3 3 7
3 ንግድ ባንክ 2 10 6
4 ሀዋሳ ከተማ 2 3 4
5 ጌዴኦ ዲላ 2 0 2
6 አአ ከተማ 3 -1 2
7 አቃቂ ቃሊቲ 3 -2 2
8 ድሬዳዋ ከተማ 3 -3 1
9 አዳማ ከተማ 3 -4 1
10 አርባምንጭ ከተማ 2 -9 0

© ሶከር ኢትዮጵያ