በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የዛሬ ሁለተኛ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጌዲኦ ዲላን 2 ለ 1 አሸንፏል፡፡
ለዕይታ ማራኪ በነበረው የሁለቱ ክለቦች የ 10:00 ጨዋታ በተለይ የጌዲኦ ዲላ የአጨዋወት መንገድ አስገራሚ የነበረ ሲሆን የንግድ ባንክ የማጥቃት እንቅስቃተሻለ የነበረበት የመጀመሪያ አጋማሽ መመህከት ችለናል፡፡ በዚህም 8ኛው ደቂቃ ረሂማ ዘርጋው በቀኝ አቅጣጫ ስታሻግር ሎዛ አበራ ኳሱ ሳይበርድ ወደ ግብ መታው የጌዲኦ ዲላዋ መታሰቢያ ክፍሌ ብልጠቷን ተጠቅማ ከግቡ ትዩዩ የመታችዋን ኳስ አውጥታባታለች፡፡
የንግድ ባንክን የጨዋታ መንገድ የተረዱ የሚመስሉት ዲላዎች ምንም እንኳን ጨራሽ የሚባል አጥቂን በቡድኑ ውስጥ ይዘው መመልከት ባንችልም በአስደናቂ ክህሎቷ ለቡድኗ ስኬታማነት የጎላ ድርሻ ስታበረክት የነበረችው እፀገነት ግርማ 22ኛው ደቂቃ ላይ ጌዲኦ ዲላን መሪ ያደረገች ግብ አስቆጥራለች፡፡ ተጫዋቿ ከመሐል ሜዳ ወደ ንግድ ባንክ የግራ አቅጣጫ ባደላ ቦታ ላይ አራት ተጫዋቾች አልፋ ኳሱን እየነዳች ወደ ግብ ክልል ካመራች በኃላ ለአማካዩዋ ወርቅነሽ መሠለ ሰጥታት አማካዩዋም ወደ ግብ መትታ ንግስቲ መፀዛ ስትፋው በራሷ ጥረት ያመጣችውን ኳስ ነው በስተመጨረሻም ወደ ግብነት የለወጠችው፡፡
ሎዛ አበራ ከአራት ደቂቃዎች መልስ ንግድ ባንክን አቻ የሚያደርግ ዕድልን አግኝታ ሳትጠቀም ቀርታለች፡፡ መሀል ሜዳ ላይ ድክመት ይታይባቸው የነበሩት ንግድ ባንኮች በፍጥነት 29ኛው ደቂቃ ላይ ትዕግስት ያደታን በማስወጣት እመቤት አዲሱን ቀይረው አስገብተዋል፡፡ ተጫዋቿም ተቀይራ እንደገባች ለአጥቂዎች ቶሎ ቶሎ ኳሶችን በማሻገር አቻ እንዲሆኑ አስችላለች፡፡ 33ኛው ደቂቃ እመቤት በቀኝ በኩል ያሻገረችውን ኳስ ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረችው ሎዛ አበራ አስቆጥራው ባንኮችን አቻ ማድረግ ችላለች፡፡ ንግድ ባንክ ተጨማሪ መሪ ሆኖ ወደ መልበሻ ክፍል ሊገባ የሚችልበትን ዕድል በብርቱካን ገብረክርስቶስ ቢያገኝም ወደ ግብነት ሳይለወጥ ወጥተዋል፡፡
ሁለተኛው አጋማሽ አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ በንግድ ባንክ ተበልጦ በነበረበት የመሐል ሜዳ ላይ ስመኝ ምህረቴ እና ፋሲካ መስፍንን ቀይሮ በማስገባት ብልጫን የወሰደበት ነበር፡፡ ጌዲኦ ዲላዎች ወደ ማጥቃት ወረዳው በሚመጡበት ወቅት አንሰው ስለሚገኙ እና የቱሪስት ለማ ግላዊነት ታክሎበት በቀላሉ ሲያገኙት የነበረውን ዕድል በተደጋጋሚ አምክነውታል፡፡
በተቃራኒው ንግድ ባንኮች በመልሶ ማጥቃት ከመስመር በሚነሱ ጥቂት አጋጣሚዎች ሙከራን በማድረጉ ተሽለው ታይተዋል፡፡ በተለይ ረሂማ ዘርጋው ሁለት ጊዜ ከጌደኦ ዲላዋ ግብ ጠባቂ መስከረም ሰርሜሎ ጋር ተገናኝታ የተዳነባት ክስተት የሚያስቆጩ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ በሌላ ሙከራ ዓለምነሽ ገረመው ለማሸማት ወደ ጎል የላከቻት ኳስ አቅጣጫ ቀይራ ወደ ጎል ስታመራ የጌዲኦ ዲላዋ ተከላካይ መታሰቢያ ክፍሌ ከግቡ መስመር ላይ በግንባር ገጭታ አውጥታዋለች፡፡
ኳስን መስርተው በመጫወት ንግድ ባንክን ሲፈትኑ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች የታዩት ዲላዎች ያለቀላቸውን ዕድሎችን አግኝተው ደካማ የአጨራረስ አቅማቸው በተቃራኒው ግብ እንዲያስተናግዱ አድርጓቸዋል፡፡ 87ኛው ደቂቃ ብርቱካን ገብረክርስቶስ የተከላካዮችን ስህተት አይታ ያሳለፈችው ኳስ አየር ላይ እያለ ከመሀል አፈትልካ በመውጣት ረሂማ ዘርጋው በግንባር ገጭታ በማስቆጠር ንግድ ባንክን ወደ መሪነት አሸጋግራለች፡፡ ጎሉንም ካስቆጠረች በኃላ ደስታዋን በዕንባ ገልፃለች፡፡ ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ ብልጫን የወሰዱት ጌዲኦ ዲላዎች እንዳደረጉት ጥረት ግብ ሳያስቆጥሩ በንግድ ባንክ 2 ለ 0 ሽንፈት ገጥሟታል፡፡
ልሳን የሴቶች ስፖርት ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ብርቱካን ገብረክርስቶስን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡
ጊዜያዊ ሰንጠረዥ | ||||
# | ክለብ | ተጫ | ልዩ | ነጥብ |
1 | ንግድ ባንክ | 3 | 11 | 9 |
2 | ኤሌክትሪክ | 3 | 3 | 9 |
3 | መከላከያ | 3 | 3 | 7 |
4 | ሀዋሳ ከተማ | 2 | 3 | 4 |
5 | ጌዴኦ ዲላ | 3 | -1 | 2 |
6 | አአ ከተማ | 3 | -1 | 2 |
7 | አቃቂ ቃሊቲ | 3 | -2 | 2 |
8 | ድሬዳዋ ከተማ | 3 | -3 | 1 |
9 | አዳማ ከተማ | 3 | -4 | 1 |
10 | አርባምንጭ ከተማ | 2 | -9 | 0 |
© ሶከር ኢትዮጵያ