“…አሰልጣኙ የራሱ ምክንያት ይኖረዋል” – አስቻለው ግርማ

ድሬዳዋ ከተማ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ጨዋታውን አድርጎ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ድል እንዲያሳካ ትልቁን ሚና ከተወጣው አስቻለው ግርማ ጋር ቆይታ አድርገናል።

በጅማ የእግርኳስ ህይወቱን ጅማሮው አድርጎ በሱሉልታ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ተጫውቶ ያሳለፈው ፈጣኑ አስቻለው ግርማ በሰበታ ከተማ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል ዘንድሮ እየቀረው በክለቡ ባለመፈለግ በቅርቡ ስምምነት መለያየቱ ይታወቃል፡፡ በመጨረሻው የዝውውር ጊዜ ድሬደዋ ከተማን የተቀላቀለው አስቻለው ከሁለተኛ ሳምንት ተቀይሮ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ከማቀበል አንስቶ በዛሬው ዕለት በአዲሱ ክለቡ የመጀመርያውን ጎል ጅማ አባ ጅፋር ላይ አስቆጥሯል። ሰበታ የወጣበት ምክንያት እንደማያሳምነው እና በቀጣይ ከድሬደዋ ከተማ ጋር ስለሚያስበው ነገር ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አግኝተነው አጭር ቆይታ አድገናል።

” ከሰበታ የወጣሁበት መንገድ አሳማኝ አይደለም። ዓምና ጥሩ የውድድር ጊዜ አሳልፌ ነበር። እኔ የማውቀው ዘንድሮ ሰበታ እንደምጫወት ነበር። ሆኖም በመጨረሻ ሰዓት በንግግር መፍታት የምንችለው ጉዳይ ሆኖ ሳለ አሰልጣኝ አብርሀም እንደማይፈልገኝ ነገረኝ። አሰልጣኙ የራሱ ምክንያት ይኖረዋል። እንደ አሰልጣኝ አብርሀምን በጣም የማከብረው ነው። ካጠፋሁም ይቅርታ እጠይቀዋለው። ግን ቢረዳኝ ጥሩ ነበር፤ አልተረዳኝም። ምንግዜም ሰዎች ምክንያት ናቸው። ፈጣሪ ይመስገን ድሬዳዋ ጥሩ አጀማመር እያደረኩኝ ነው።

“ድሬደየዳዋ እስካሁን ባለኝ ነገር ፈጣሪ ይመስገን። በጣም የሚገርማችሁ እውነት ለመናገር ዝግጅት እንኳን አልሰራሁም። ሰበታ ነበርኩ፤ ዝግጅት ይጠሩኛል ብዬ እየጠበኩ ነበር፤ አልጠሩኝም። በጊዜው መልቀቂያ ጠብቄ ነበር። የተሻለ ቡድን አግኝቼ አልሰጥም አሉኝ። ቡድን በማላገኝበት ሰዓት አሰልጣኙ አልፈልግህም አለኝ። ይህ ተገቢ አይደለም፤ የተጫዋችን ሞራል መንካት ነው። ችግር የለውም፤ ሰዎች ቢገፉህም ፈጣሪ ያነሳሀል። ምንም ሳልሰራ ይህን እያደረግኩ ነው። ከዚህ በኃላ እየሰራው ስሄድ የተሻለ ነገር አደርጋለሁ። በአጋጣሚ ከዚህ ቀደም በሌላ ክለብ አብረውኝ ከተጫወቱት ከኤልያስ ማሞ እና ያሬድ ጋር አብሬ ስለተጫወትኩ ከቡድኑ ጋር በቶሎ ለመዋሀድ አልተቸገርኩም። እግርኳስ ነው፤ በቀጣይም ከድሬ ጋር የተሻለ ነገር እሰራለው።

“ጎሉን አግብቼ ደስታዬን ያልገለፅኩት ጅማ ትውልድ ስፍራዬ ነው። ለዛ ነው ደስታዬን ያልገለፅኩት።”


© ሶከር ኢትዮጵያ