በፍጥነት ጎሎችን ባስተናገደው ጨዋታ ፋሲል ከነማ ወላይታ ድቻን 3-2 ማሸነፍ ችሏል።
ሁለቱም ተጋጣሚዎች ካለፈው ጨዋታቸው የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ አድርገው የገቡ ሲሆን በድቻ በኩል አማኑኤል ተሾመ በኤልያስ አህመድ በፋሲል ወገን ደግሞ በረከት ደስታ በሀብታሙ ተከስተ ቦታ ጨዋታውን ጀምረዋል።
ጨዋታው በ23 ደቂቃዎች አራት ግቦች የተስተናገዱበት የመጀመሪያ አጋማሽ አሳይቶናል። ለአጥቂዎች ፌሽታ ለተከላካዮች ድንጋጤ በፈጠሩት ቅፅበቶችም ሙጂብ ቃሲም 4ኛው ደቂቃ ላይ እንየው ካሣሁን ከቀኝ መስመር ያሻማለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ሲያስቆጥር 13ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከሽመክት ጉግሳ የሰነጠቀለትን እና ጨረፍ አድርጎ ያመቻቸለትን ኳስ የፊት አጥቂው ቀላል ባለ አጨራረስ ከመረብ በማሳረፍ ፋሲሎችን መሪ አድርጓቸዋል።
በሁለቱም ግቦች ስር የኃላ መስመር ተከላካዮች እጅግ ተዘናግተው በታዩበት ጨዋታ ቀጣዩን ግብ የማስቆጠር ተራ ድቻዎች ወስደዋል። በሁለት ግብ መምራት የቻሉት ፋሲሎች ያደረባቸው የእርግጠኝነት ስሜት እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ወደመዘናጋት ሲወስዳቸው አምስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር የተቆጠሩት። 18ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ወልዴ ከርቀት ወደተጋጣሚ የግብ ክልል የጠለውን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ሲያወርድለት ስንታየሁ መንግሥቱ አክርሮ በመምታት አስቆጥሯል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ከቅጣት ምት በተነሳ ኳስ ፀጋዬ ብርሃኑ ቡድኑን አቻ ያደረገበት ጎል አስቆጥሯል።
ከግቦቹ በኋላ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት በአስገራሚው አጋማሽ የተከላካዮች ስህተት ሌሎች ግቦችንም ሊያሳየን ተቃርቦ ነበር። የፋሲሉ ሙጂብ ቃሲም እና የድቻው ቸርነት ጉግሳ ያደረጓቸው ሌሎች ሙከራዎችም ግብ ከመሆን የዳኑት ተከላካዮች ተረባርበው በመደረባቸው ነበር። 36ኛው ደቂቃ ላይ የድቻው መስመር ተከላካይ መሳይ አገኘው ከርቀት ወደ ግብ ልኮት በግቡ አግዳሚ የተመበሰውም ኳስ ሌላው አስደንጋጭ ሙከራ ሆኖ አልፏል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ፋሲሎች ሙሉ ኃይላቸውን በማጥቃት ላይ ሲያደርጉ ድቻዎች ጥንቃቄ ጨምረው ተመልሰዋል። 63ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተነሳውን ኳስ ያሬድ ባዬ በግንባር ገጭቶ በአግዳሚው የተመለሰበት እና 65ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ጥላሁን ከሽመክት ጉግሳ ተቀብሎ በቀጥታ መትቶት ተከላካዩ መሳይ አገኘው ያወጣው ኳስ የዐፄዎቹ ከባድ ሙከራዎች ሆነዋል።
በአንፃሩ ድቻዎች ለአጥቂያቸው ስንታየሁ መንግሥቱ ቀጥተኛ ኳሶችን ከመላክ ባለፈ በአመዛኙ በራሳቸው ሜዳ ላይ መቆየትን መርጠዋል። ጨዋታው በዚህ መልክ ቀጥሎ ደጉ ደበበ ተቀይሮ በገባው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ላይ በሰራው ጥፋት ፋሲሎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኘተዋል። ሙጂብ ቃሲም ፍፁም ቅጣት ምቱን ሲመታ ሰዒድ ሀብታሙ ቢያድነውም ከመመታቱ በፊት መስመሩን በመልቀቁ በድጋሚ እንዲመታ ተደርጎ ሙጂብ 72ኛው ደቂቃ ላይ ሦስተኛውን ግብ አስቆጥሯል። አጥቂው አዲሱ የውድድር ዓመት ከተጀመረ ወዲህ ሐት-ትሪክ የሰራ የመጀመርያ ተጫዋችም መሆን ችሏል።
ከግቡ በኋላ ድቻዎች ዳግም ወደ ማጥቃት ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። 80ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየሁ መንግሥቱ በቀኝ በኩል ተከላካዮችን ታግሎ ገብቶ የሞከረው ኳስም የወጣው አግዳሚውን ታክኮ ነበር። ሆኖም በተጋጣሚያቸው መነቃቃት ወደ ኃላ ያልተመለሱት ፋሲሎች ወደ ፊት ገፍቶ የመጫወት ሀሳባቸውን ሳይቀይሩ ጨዋታውን በ 3-2 ውጤት አጠናቀዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ