” ከዚህ በኃላ ወደ ኃላ ተመልሶ ተከላካይ ሆኖ መጫወት አይታሰብም” – ሙጂብ ቃሲም

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያውን ጎል ያስቆጠረው እና በዛሬው ጨዋታ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ሐት-ትሪክ ከሰራው ሙጂብ ቃሲም ጋር ቆይታ አድርገናል።

በእግርኳስ ህይወቱ ከግብጠባቂነት እስከ አጥቂነት ተጫውቷል። ሲዳማ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ፣ አዳማ ከተማ እና ያለፉትን ሦስት ዓመታት በዐፄዎቹ ቤት እየተጫወተ ይገኛል። የዋልያዎቹ አጥቂ ሙጂብ ቃሲም ፋሲሎችን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ የቡድኑ ወሳኝ አጥቂ መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛል። በተለይ ዓምና ውድድሩ በኮሮና ቫይረስ እስከተሰረዘበት ጊዜ ድረስ በ13 ጎሎች በማስቆጠር የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን እየመራ ነበር። የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ መልክ ዘንድሮ ሲጀምር የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ጎል በማስቆጠር ስሙን አፅፎ ነበር። በዚህ ያላበቃው የሙጂብ ጉዞ አሁን ደግሞ ዐምና የሊጉን የመጀመርያ ሐት-ትሪክ እንደሰራ ሁሉ ዘንድሮም በሊጉ በአንድ ጨዋታ ሦስት ጎሎች ያስቆጠረ የመጀመርያው ተጫዋች በመሆን ሌላ ስኬት አስመዝግቧል። እስካሁን ባለው ሁኔታ ከፍተኛ ጎል አግቢነትን በአምስት ጎል እየመራ ከሚገኘው ድንቁ አጥቂ ሙጂብ ቃሲም ጋር ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አግኝተነው አዋርተነው ተከታዩን ሀሳብ አካፍሎናል።

ሙጂብ ተመልሶ ተከላካይ ይሆናል ?

ኧረ የማይታሰብ ነው። በጣም ከባድ ነው። ምን አልባት ቡድኑ ውስጥ የተለየ ነገር ተፈጥሮ (ተቸግሮ) ተከላካይ ሆኜ እንድጫወት ከተገደድኩ እንጂ ከዚህ በኃላ ወደ ኃላ ተመልሶ ተከላካይ ሆኖ መጫወት የማይታሰብ ነው። በዚሁ በአጥቂነቱ ነው የምቀጥለው።

ዐምና የመጀመርያ ሐት-ትሪክ ሰራህ ዘንድሮስ መድገምህ እንዴት ነው ?

ያው አንዳንዴ ዕድለኝነት ነው። ከዛም ባለፈ በጣም ደስ ይላል። ዐምና ሐት ትሪክ ሰርቼ ዘንድሮም እኔ በመጀመሬ ይህ ለኔ ትልቅ ታሪክ ነው። ጥሩም አጋጣሚ ነው።

ዐምና ያጣህውን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ዘንድሮ ታሳካለህ ?

ከፈጣሪ ጋር ይሄን ነው የማስበው። ዞሮ ዞሮ ዋናው የማስቀድመው የቡድኔን ውጤት ነው። ቡድናችን ዓመቱን በስኬት እንዲያጠናቅቅ ሁላችንም ጠንክረን እየሰራን ነው። ከዚህ በዘለለ ቡድናችን ጥሩ ሆኖ ካጠናቀቀ እኔም በዚህ መሐል ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ለመሆን ከቀን ወደ ቀን ራሴን ለማሻሻል እየሰራሁ ነው። ከፈጣሪ ጋር ይህን ለማሳካት የምችለውን አደርጋለው።

ጎል አግብተህ እንደ ጎልፍ ተጫዋች ደስታህን የምትገልፅበት መንገድ የተለየ ሚስጢር አለው ?

በፊት የትውልድ አካባቢዬ አለታወንዶ በትንሽ ሜዳ ላይ የፕሮጀክት ውድድር በወረዳ ላይ ስጫወት ሁልግዜ ጎል ሳገባ በዚህ መንገድ ከጓደኞቼ ጋር ደስታዬን እገልፅ ነበር። ይሄን ለማስታወስ ነው ሁሌም ጎል አግብቼ በዚህ መንገድ ደስታዬን የምገልፀው። ይሄን ማድረጌ ያስደስተኛል። ከዚህ ውጭ የጎልፍ ጨዋታን ተጫውቼ አላውቅም።


© ሶከር ኢትዮጵያ