ሦስቱን ወንድማማቾች ያገናኘው ጨዋታ…

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በተካሄደው የፋሲል ከነማና የወላይታ ድቻ ጨዋታ ሦስቱን ወንድማማቾች አግናኝቶ ነበር። እኛም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበንላቸዋል የሰጡንን ምላሽ ይዘን ቀርበናል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ በተለያዩ ዘመናት በአንድ ቡድን አብረው የሚጫወቱ ወንድማማቾች ሲያስመለክተን እንደቆየ ሁሉ የአንድ ቤተሰብ አካል ሆነው በተቃራኒ የመጫወት አጋጣሚ ሲከሰት ኖሯል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከአንድ ቤተሰብ የወጡት የጉግሳ ልጆች የሆኑት ሦስቱ ወንድማማቾችን እየተመለከትን እንገኛለን። ታላቅ ወድምዬው ሽመክት ለፋሲል ከነማ፣ ቸርነት እና አንተነህ ጉጉሳ ደግሞ ለወላይታ ድቻ እየተጫወቱ ይገኛሉ። በዛሬው ዕለትም በተቃራኒ ማልያ የተገናኙትን ሦስቱን ወንድማማቾችን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበንላቸው ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል።

ቸርነት ጉግሳ

ሜዳ ውስጥ በተቃራኒ መጫወት ያለው ስሜት ምን ይመስላል?

በጣም ደስ ይላል። የበለጠ አንድ ላይ ሆነን በአንድ ማልያ አብረን ብንጫወት የበለጠ ደስ ይለኝ ነበር። አንድ ቀንም አይቀርም። በአንድ ክለብ አብረን ተጣምረን እንጫወታለን ብዬ አስባለሁ።

ከሽመክት የምታደንቅለት ምንድነው ?

ለማልያ የሚሞት ተጫዋች ነው። ለለበሰው መለያ ትልቅ ክብር ይሰጣል። ይህን በጣም አደንቅለታለው። ሜዳ ውስጥ በጣም ታታሪ ነው። ያለውን ነገር ሁሉ ነው የሚሰጠው ይህ ነገሩ በጣም እወድለታለው።

አንተ እና ሽመክት ሁለታቹሁም በአንድ አይነት ሚና ነው የምትጫወቱት። በችሎታ ማን ይበልጣል ?

(በጣም እየሳቀ…) ምንም ጥያቄ የለውም ሽሜ ከእኔ የተሻለ በሀገራችን አሉ ከሚባሉ የመስመር አጥቂዎች አንዱ ነው። እኔም ሁሌም እርሱ የደረሰበት መድረስን ነው የማስበው።

ሽመክት ጉግሳ

ሜዳ ውስጥ በተቃራኒ መጫወት ያለው ስሜት ምን ይመስላል?

ደስተኛ ነኝ ግን፤ ግን በጣም ከባድ ነው። አብረህ በአንድ ማልያ ብትጫወት መልካም ይመስለኛል። ለለበስነው ማልያ ስለምንጫወት ምንም የሚኖር ነገር የለም። ግን በተቃራኒ ሆኖ መጫወት ይከብዳል። በተለይ ለኔ ብዙ ጊዜ ይከብደኛል።

ለምን ይከብድሀል ?

ምን አለ መሰላችሁ፤ በተለይ ወላይታ ላይ ስንጫወት ለኔ ይከብደኛል። ቤተሰብ በጣም ይጨነቃል። እንዳጋጣሚ ሆኖ ሶዶ ላይ እርስ በእርስ የምንገናኘው የማይሆን ሰዓት ነው። ድቻ ላለመውረድ ሲጫወት እኛ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ሆነን ነው ከዚህ ቀደም የምንገናኘው። ይህ ለኔ በጣም ያስጨንቀኛል። ፈጣሪ ይመስገን በተገናኘንበት ጨዋታ ሁሉ በመልካም ሁኔታ ነው የተጠናቀቀው።

ወደፊት በጋራ የመጫወት ህልም አላችሁ ?

አዎ የማይቀር ነው። በእርግጠኝነት አንድ ቀን በአንድ ማልያ መጫወታችን የማይቀር ነው።

ከቸርነት የምትወድለት ?

ቸርነት በጣም ጎበዝ ተጫዋች ነው። ድሪብለር ነው። ሰው መቀነስ ይችላል። ጠንካራ ምቶች አሉት፤ ፈጣንም ነው። የመስመርም ቀጥተኛ አጥቂ ሆኖ መጫወት ይችላል። ሰውነቱ በጣም ያምራል። ወደ ፊት ጥሩ የሚቀርፀው አሰልጣኝ እያገኘ ሲመጣ በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ነግሶ የሚወጣ የተሻለ ደረጃ የሚደርስ ተጫዋች ይሆናል።

ቤታችሁ እናንተን የሚከተል ታናሽ ወንድም አለ?

አጋጣሚ ሆኖ ሌላ ታናሽ ወንድም የለም። ቤት ታናሽ እህት ነው ያለችን። ሦስታችን ከአንድ ቤት ከተጫወትን አይበቃም? (እየሳቀ…)

አንተነህ ጉግሳ

እነርሱ የመስመር አጥቂ ናቸው። አንተ ተከላካይ በመሆን ለምን ተለየህ ?

(እየሳቀ) ያው በልጅነታችን ስንጫወት አንዳንዴ ተፈጥሮ የሚያስገድድህ ነገር አለ። ያው እኔ ቁመቴ ከእነርሱ ትንሽ ከፍ ስለሚበልጥ ተከላካይ አደረጉኝ እንጂ እኔም በመስመር አጥቂነት ነበር የምጫወተው፤ አሰልጣኝ ነው ወደ ኃላ ያደረገኝ።

ከሽመክት የምትወድለት ምንድነው ?

ቸርነት ቅድም ብሎልሀል። በጣም ለማልያ ታማኝ ታታሪ ተጫዋች ነው። ቅድሚያ ለራሱ አይሰጥም። ቡድኑ እንዲያሸንፍ ከመፈለጉ የተነሳ ለቡድን አጋሮቹ አመቻችቶ ሲያቀብል የሚደሰት ሰው ነው። ብዙ ጊዜ ይሄን ሲያደርግ ትመለከታለህ። ስለዚህ ከራሱ ይልቅ ለቡድኑ የሚጫወት በመሆኑ ይሄን በጣም እወድለታለው።

በመጨረሻ የምታስተላልፈው መልዕክት?

በተለያየ ማልያም ቢሆን ከአንድ ቤተሰብ አብረን በመጫወታችን በጣም ነው ደስ የሚለው። ግን የሚገርማችሁ እናታችን እኛ በተለያየ ቡድን እየተጫወትን ስንገናኝ በጣም ትጨነቃለች። ውጤቱ ምንም ይሁን ምንም እርሷ በጣም ትጨነቃለች። ዛሬ ጨዋታውን በቴሌቭዥን ተመልክታዋለች። በዚህ አጋጣሚ “እኛ በሠላም ወጥተናል አታስቢ እናታችን” እንላታለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ