በወልቂጤ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የዛሬው ጨዋታ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ
ስለጨዋታው…
ተጋጣሚያችን ጠንካራው ባህር ዳር ከተማ ነው። የተወሰነ የቅርፅ ለውጥ አድርገን ነው ወደ ሜዳ የገባነው። የመረጥነው መንገድም አዋጥቶቶን የመጀመሪያውን አጋማሽ ጎል አግኝተን ወጥተናል። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሙሉ ለሙሉ ኳስ ተቆጣጥረን የመሀል ሜዳ ብልጫውን ወስደን ለመጫወት አስበን ነበር የገባነው። ነገር ግን ያው ከውጤቱ ጋር ተያይዞ ተጫዋቾ ያንን ውጤት ለማስጠበቅ የነበራቸው ፍላጎት አለ ፤ ጫና አለ። ወጣ ገባ ያለ እንቅስቃሴ ነበር። ተጨማሪ ጎሎች ማግኘት የምንችልባቸው ዕድሎች ፈጥረናል። ልጆቻችን ሜዳ ውስጥ የነበራቸው ታታሪነት ጨዋታውን አሸንፈው ለመውጣት ያሳየት ቁርጠኝነት በጣም የሚያስደስት ነው። የተመዘገበው ውጤት ይገባናል ብዬ ነው የማስበው።
ስለአህመድ ሁሴን…
አህመድ ሁሴን ገና እያሰገ ያለ ተጫዋች ነው ፤ የልምድ እጥረቶች አሉበት። ሆኖም ግን ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተጋጣሚ ተከላካይ ላይ ጫና የመፍጠር እንቅስቃሴው በጣም ጥሩ ነው። ጎል ላይ የሚገኝበትም መንገድ እንደተመለከታችሁት ነው። የመጨረሻ ንኪኪው ላይ ብዙ ስራ ይጠይቃል። ከጎል ስለራቀ እና ወደ ጎል ለመምጣት ያለው ጉጉት ከፍተኛ ስለሆነ አንዳንዴ ለማመን የሙያስቸግሩ ኳሶች ይሳታሉ። በሂደት ግን ይመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። እኛም በእሱ ተስፋ አንቆርጥም።
አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ
ስለጨዋታው…
በመጀመሪያ ተጋጣሚዎችን እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። በመጀመሪያው አጋማሽ በተለይ ጎል ከገባብን በኋላ በአካልም በአዕምሮም ደክመን የታየንበት ነበር። እንደአጠቃላይ እንደ 90 ደቂቃ ጥሩ አልተጫወትንም። በቡድኔ ደስተኛ አይደለሁም። መሸነፋችን የሚጠበቅ ነው ፤ ጥሩ ካልተጫወትን። ግን ያው እግር ኳስ ነው እና ለሚቀጥለው ጨዋታ ራሳችንን አዘጋጅተን እንመጣለን።
ቡድኑ በቶሎ ወደ ጨዋታ መንፈስ ስላለመመለሱ…
ጎል ሲያስተናግዱ ያንን መቀበል የቻሉ አልመሰለኝም። ገና ብዙ ደቂቃ እንዳለን መረዳት አልቻሉም። ከእጃችን የወጣውን ጨዋታ የታክቲክም የተጫዋችም ለውጥ በማድረግ እጃችን ውስጥ ለመመለስ ሞክረናል። ግን በስህተት ያታጀበ በመሆኑ በምንፈልገው መልኩ ቡድኔ ማጥቃትም የጎል ዕድል መፍጠርም አልቻለም። ከዚህ ብዙ መማር እና ብዙ መስራት እንደሚኖርብን ነው የምረዳው።
© ሶከር ኢትዮጵያ