የሁለት ግዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ የሆነው ኤሌክትሪክ ዛሬ ረፋድ ላይ ሜክሲኮ በሚገኘው የኤሌክትሪክ ክበብ አዳራሽ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በተፈጠሩ የዳኝነት ችግሮች እና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለሚዲያ አካላት መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ስፖርት ክለቡ ከዳሽን ቢራ ጋር ጎንደር ፋሲለደስ ስታዲየም ላይ ባደረገው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በፌድራል ዳኛ ሚካኤል አርአያ ሆን ተብሎ የዳኝነት በደል የደረሰበት መሆኑን አስረግጦ ተናግሯል፡፡
ጨዋታውን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን አምበሉን አዲስ ነጋሽ ለ8 ወራት ሲያግድ ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ ለ10 ጨዋታ መቀጣታቸው ይታወሳል፡፡ አማረ በቀለ ደግሞ የአራት ጨዋታ ቅጣት ተጥሎበት እንደነበር ይታወሳል፡፡
የኤሌክትሪክ ክለብ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዩሃነስ ለገሰ ክለቡ በቅርብ ግዜያት ተደጋጋሚ የዳኝነት በደሎች እያጋጠመው በመሆኑ ሁኔታዎች የማይሻሻሉ ከሆነ ክለቡ እራሱን ከሊጉ ሊያገል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ “የዳኝነት በደሎቹ እየበዙ እየመጡ ነው፡፡ ፌድሬሽኑ ነገሮችን የማያሻሽል ከሆነ ክለባችን በሊጉ መሳተፉን ሊያቆም ይችላል፡፡ በሌሎች የእድሜ እርከን የሚገኙ ቡድኖቻችን ግን መጫወታቸውን ይቀጥላሉ፡፡
“ጀማሪ ዳኞች ጨዋታዎችን በማጫወታቸው ችግሮች እየተፈጠሩ ነው፡፡ እኛ ተጫዋቾቻችን ሁሌም የምንመክረው ተጋጣሚያዎቻችን፣ ዳኞችን እና ፌድሬሽኑን በችሎታ በልጠው እንዲያሸንፉ ነው፡፡ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ባደረግነው ጨዋታ አጥቂያችን ፒተር ኑዋድኬ አግባብ ባልሆነ መንገድ በቀይ ካርድ ወጥቷል፡፡ እነዚህ በደሎች ከግዜ ወደ ግዜ ተባብሰዋል፡፡ ኩፐር ቴስት ያላለፉ ዳኞች ጨዋታዎችን እያጫወቱ ነው፡፡ ይህ በጣም ተገቢ ያልሆነ አሰራር ነው፡፡”
አቶ ዩሃንስ አክለው የተላለፉት ቅጣቶች ተጋቢ እንዳልሆኑ አስረድተዋል፡፡ “አሰልጣኝ ብርሃኑ ጭራሽ ተጫዋቾቻችን ከዳኛው ጋር ወደ ፀብ እንዳያመሩ እያገላገሉ ነበር፡፡ አዲስም ከአንድ አምበል እንደሚጠበቀው ዳኛውን ለማናገር ሄደ እንጂ ለሌላ ነገር አላደረገም፡፡ ይልቅ ተጫዋቾቻችን በዚሁ ጉዳይ ምክንያት ሌሎች ዳኞች እንደጠመዱቸው ነግረውናል፡፡ እንዳንዶቹ ዳኞች ገና እንቀባበላችኋለን ማለታቸውን ሰምተናል፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ ለፌድሬሽኑም በምስል የተደገፈ ማስረጃ አቅርበን በቂ አይደለም ተብለናል፡፡” ብለዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ክለቡ ከዳሽን ቢራ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ምስል ለሚዲያ አካላት አሳይቷል፡፡