ሪፖርት | አራተኛው ሳምንት በአሰልቺ ጨዋታ ተዘግቷል

አዳማ እና ሲዳማን ያገናኘው ጨዋታ እጅግ ደካማ ከሆነ እንቅስቃሴ ጋር ያለግብ ተጠናቋል።

አዳማ ከተማዎች ታሪክ ጌትነት ፣ እዮብ ማቲዮስ እና በቃሉ ገነነን በዳንኤል ተሾመ ፣ አካሉ አበራ እና አክሊሉ ተፈራ በመለወጥ ጨዋታውን ሲጀምሩ ሲዳማዎች ባደረጓቸው ለውጦች ደግሞ አማኑኤል እንዳለ እና ዮሴፍ ዮሀንስን በክፍሌ ኪአ እና ዳዊት ተፈራ ምትክ ተጠቅመዋል።

እጅግ የተቀዛቀዘ የነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ጥቂት ሙከራዎችን ብቻ የተመለከትንበትም ነበር። መሀል ሜዳ ላይ በመነጣጠቅ በተሞላው እንቅስቃሴ ቀጥተኝነት ይታይባቸው የነበሩት ሲዳማዎች ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ መስለው ይታዩ እንጂ አብዛኞቹ ሙከራዎቻቸው ከሳጥን ውጪ የሚደርጉ እና ኢላማቸውን ያልጠበቁ ነበሩ።

ገና በ19ኛው ደቂቃ የፊት አጥቂያቸው ይገዙ ቦጋለን በጉዳት ምክንያት ቀይረው ለማስወጣት የተገደዱት ሲዳማ በመጠኑ ቀረብ ይሉ የነበሩ ቢሆንም የአበባየሁ ዮሐንስ የ24ኛ እና 33ኛ ደቂቃ ሙከራዎችም ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመን እምብዛም የፈተኑ አልነበሩም። 3ኛው ደቂቃ ላይ በየኋላሸት ፍቃዱ ጥሩ የርቀት ቀጣት ምት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገው በመሳይ አያኖ የከሸፈባቸው አዳማዎችም 23ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው ከጀሚል ያዕቆብ ተቀብሎ ከቅርብ ርቀት ካደረገው ደካማ ሙከራ ውጪ ከተጋጣሚ ሳጥን ርቀው አልፎ አልፎ ከሚገኙ የቆሙ ኳሶች ብቻ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ነው አራባ አምስቱ ደቂቃ የተጠናቀቀው።

የተነቃቃ መስሎ በጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ ሁለት ከባባድ ሙከራዎች ተደርገዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛኸኝ መትቶት ዳንኤል ተሾመ የተፋውን ኳስ አዲሱ አቱላ በድጋሚ ሞክሮ ግብ ጠባቂው አድኖበታል። አዳማዎችም ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ በሰጡት ምላሽም የኋላሸት ፍቃዱ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ነበር በመሳይ አያኖ የተመለሰበት። ያም ቢሆን ጨዋታው ወደ ቀደመ መልኩ ተመልሶ ውል አልባ እንቅስቃሴዎችን ሲያስመለክተን ቆይቷል። በቀሩት ደቂቃዎችም ከተመስገን በጅሮንድ እና የኋላሸት ፍቃዱ ለግብ ጠባቂዎች ቀላል ከነበሩ የርቀት ሙከራዎች በኋላ ትርጉም ያለው የማጥቃት ሂደት ሳንመለከት የዋና ዳኛ ምስጋናው መላኩ ፊሽካ እጅግ አሰልቺውን ጨዋታ በቃ ብሎታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ