ከአራተኛ ሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በኃላ የተጋጣሚዎቹ የአዳማ ከተማ እና ሲዳማ ቡና አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ቀጣዩን ቆይታ አድርገዋል።
አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል – አዳማ ከተማ
ስለጨዋታው…
እንዳያችሁት ሁለታችንም ተሸንፈን ነው የመጣነው። ከዛ ለመውጣት ያደረግነው ትግል ነው እና ውጤቱ አልከፋኝም። ከሽንፈት እንደመምጣታችን ተጫዋቾች ላይ ጭንቀት አለ። ከዚህ የተነሳ አንዳንድ ጥቃቃን ስህተቶች አሉ ፤ በጉጉት የሳትናቸው። እነሱን ደግሞ በሚቀጥለው አሻሽለን ለመምጣት እንሞክራለን። በውጤቱ ግን አልተከፋሁም።
ስለሚቆራረጡ ቅብብሎች…
ያው ከጉጉት ነው ፤ ትንሽ ሜዳውም ያስቸግራል። በአብዛኛው ተጫዋቾች ጉዳት ላይም ናቸው። ስድስት ሰባት ልጆች ጉዳት ላይ ነው ያሉት። ቀይረን ያስገባነው አብዲሳም ከጉዳት ነው። እና ከጉዳት ሲመለሱ ጥሩ ፍሰት ያለው ኳስ እንጫወታለን።
ጉዳቱ ከተከታታይ ጨዋታዎች ምክንያት ስለመሆኑ….
አዎ ሊሆን ይችላል። እኛ ሀገር አልተለመደም ፤ አዲስ ነገር ነው። በሂደት ይቀረፋል ብዬ አስባለሁ ፤ ያልለመድነው ስለሆነ ነው።
አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
ስለጨዋታው…
ኳሱን ይዘን ተረጋግተን መጫወት አልቻልንም። ዛሬ ጭራሽ ወደ ፊት የሚሄዱት በቀላሉ ነው የሚቆረጡት። ፊት ያለው ልጅ እንደተጀመረ ተጎዳ። የእሱ ቅያሪ ላይ የነበረው ልጅም ገብቶ ጥሩ ነገር አላሳየም። ዞሮ ዞሮ የመጨረሻ ቡድን የተሰራባቸው ልጆች በየጨዋታው መውጣታቸው ዋጋ እያስከፈለን ነው። ከመጀመሪያ አሰላለፍ ስድስት ሰባት ተጫዋች ማጣት ትንሽ ዋጋ እያስከፈለን ነው። በዚህ የተነሳ የበድኑ ሥነ ልቦና ወረድ ያለ የመስላል። ያው እግር ኳስ ነው ፤ ጠንክሮ ሰርቶ ወደ ውጤታማነት ለመምጣት መስራት ነው።
የውጪ ተጫዋቾችን አለማካተት ስላለው ተፅዕኖ…
እጅግ በጣም ተፅዕኖ አለው። አንደኛ ከቃሚ አሰላለፍ ውስጥ ሦስት ተጫዋቾች ጉዳት ላይ ይገኛሉ። ከውጪ ያመጣናቸው ተጫዋቾችም በየቦታው በድኑን ይጠቅማሉ ብለን ነው። ቢያንስ ከዋና ቡድኑ ወደ ሰባት ተጫዋቾች የሉንም ማለት ነው። በዚህ መንገድ ነው ሦስቱንም ጨዋታ ያደርገነው። ይሄ ሌላው ፈታኝ ነገር ነው የሆነብን። ለወልቂጤው ጨዋታም ይደርሱ እንደሆን አላውቅም።
© ሶከር ኢትዮጵያ