ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋቾች ትኩረት

የ4ኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጠናቀቅን ተከትሎ በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸውን ዓበይት ተጫዋች ላይ ያተኮሩ ጉዳዮች በቀጣዩ ፅሁፍ ተዳሷል።

👉የውጪ ግብ ጠባቂዎች ዋጋ የሚያስከፍሉ ጥፋቶች መበራከት

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውጭ ግብጠባቂዎች በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከቀደሙት ዓመታት አንፃር በቁጥር ረገድ መቀነስ ቢያሳይም የተቀሩት ግብጠባቂዎች እስከዚህኛው ሳምንት ድረስ በየቡድኖቻቸው የነበራቸው ተፅዕኖ ይህ ነው የሚባል አልሆነም።

ይልቁንስ በየጨዋታው ከሚኖራቸው አዎንታዊ አበርክቶ ይልቅ ቡድናቸውን ዋጋ የሚያስከፍሉ ጥፋቶችን በተደጋጋሚ እየፈፀሙ ይገኛል።

በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት ፓትሪክ ማታሲ ለፋሲል ከነማዎች ብቸኛውን የጨዋታውን የማሸነፊያ ግብ በስጦታ ያበረከተበት፣ መሐመድ ሙንታሪ በአላስፈላጊ ጀብደኝነት በቀጥታ ቀይ ካርድ ወጥቶ ቡድኑን ጭንቀት ውስጥ የጣለበት፣ ሀሪስተን ሄሱ ቀላሉን ነገር መከወን ባለመቻሉ ባህር ዳርን ከተማን ለሽንፈት የዳረገበት፣ ጄኮ ፔንዜ ጅማ አባ ጅፋር በፋሲል ከነማ በተረታበት ጨዋታ ሙጂብ ቃሲም ባስቆጠራት ጎል ወቅት መያዝ የሚችለውን ኳስ ትቶ ተጎድቻለው ብሎ ሲንከባለል የተቆጠረችው ግብ፣ የፋሲሉ ሚኬል ሳማኬ የጎል ክልሉን ለቆ ኳስ ለማፅዳት ሲሞክር አምልጦት ብዙዓየሁ እንደሻው ያስቆጠረበት በጉልህነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ጥፋቶች ነበሩ። ይህን ስንል ግን የሀገራችን ግብጠባቂዎች ስህተት አይሰሩም ባንልም ከሀገራችን ግብጠባቂዎች በንፅፅር የተሻለ አቅም አላቸው በሚል አመክንዮ ወደ ሀገራችን የውጪ ምንዛሪ ፈሰስ ተደርጎባቸው የሚመጡት እነዚሁ የውጭ ዜጋ ግብ ጠባቂዎች የሚሰሩት ስህተት መበርከት ግን ጥያቄ እንዲነሳ የሚጋብዝ ነው።

👉እድለ ቢሶቹ ይገዙ ቦጋለና አልሳሪ አልመህዲ

ምንም እንኳን በተለያየ ምክንያት ቢሆንም ይገዙ ቦጋለ እና አልሳሪ አልመህዲ የጨዋታ ሳምንቱ እድለ ቢስ ተጫዋቾች ነበሩ።

ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ላይ የሲዳማ ቡና የአጥቂ መስመርን በፊት አውራሪነት እየመራ ወደ ሜዳ የገባው ወጣቱ አጥቂ ይገዙ ቦጋለ ገና በጊዜ ጉዳትን አስተናግዶ በእሱባለው አለማየሁ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎቹ የተሸነፈው ቡድኑ በሦስተኛው ጨዋታ አንዳች አውንታዊ ውጤትን ለማስመዝገብ የይገዙን ግልጋሎት እንደመፈለጉ ተጫዋቹ ባጋጠመው ጉዳት ቡድኑን ማገዝ ባለመቻሉ ከሜዳ ተቀይሮ ሲወጣ እያነባ መውጣቱ ሁኔታውን በቀላሉ ጠቅልሎ የሚገልፅ ክስተት ነበር።

በተመሳሳይ አዲሱ የውድድር ዘመን ከተጀመረ ወዲህ እስካሁን ለቡድኑ ምንም ጨዋታ ማድረግ ያልቻለው የወልቂጤ ከተማው አማካይ አልሳሪ አልመህዲ ቡድኑ ባህርዳር ከተማ 1-0 እየመራ ከእረፍት መልስ መጠነኛ የበላይነት አሳይተው የነበሩትን የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ ለመግታት አብዱልከሪም ወርቁን በ69ኛው ደቂቃ ቀይሮ ወደ ሜዳ ቢገባም ሜዳ ላይ መቆየት የቻለው ግን ለዘጠኝ ደቂቃዎች ብቻ ነበር።

በአንድ የጨዋታ ቅፅበት በአየር ላይ የነበረን ኳስን ለመግጨት በሚሻማበት ወቅት የባህርዳር ከተማውን አምበል ፍቅረሚካኤል ዓለሙን በክርን በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሊወገድ ችሏል።

👉ተቀይሮ ገብቶ ተቀይሮ የወጣው እሱባለው

በጉዳት እና በውጪ ተጫዋቾች የሥራ ፈቃድ አለመጠናቀቅ ምክንያት በርካታ ተጫዋቾቹን መጠቀም ያልቻለው ሲዳማ ቡና አዳማን በገጠመበት የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የፊት አጥቂው ይገዙ ቦጋለን 19ኛው ደቂቃ ላይ ነበር በጉዳት ያጣው። ቦታውን ለመሸፈንም በመስመር አጥቂነት የተጠቀመው ሀብታሙ ገዛኸኝን ወደ መሐል አጥቂነት አሸጋሽጎ እሱባለው ጌታቸውን በመስመር አጥቂነት ቀይሮ አስገብቷል። መሰል አጋጣሚዎች ለተጠባባቂ ተጫቾቾች ራስን የማሳያ እና በአሰልጣኞች ዘንድ የሚጣልባቸውን ዕምነት ከፍ ማድረጊያ ተደርገው ይወሰዳሉ። ሆኖም ሲዳማ እንደቡድን የተዳከመ እንቅስቃሴ እያሳየ ባለበት ጨዋታ ላይ ወድ ሜዳ የገባው እሱባለው ልዩነት መፍጠር አልቻለም። አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉም በሜዳ ላይ ለተጫዋቹ ምክርን ሲያስተላልፉ ቢቆዩም በሁለተኛው አጋማሽ 62ኛ ደቂቃ ላይ በተመስገን በጅሮንድ ቀይረው አስወጥተውታል። ለ43 ደቂቃዎች ሜዳ ላይ የቆየው እሱባለው በክስተቱ ሊፈጥርበት ከሚችለው ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት አንፃር ዳግም ዕምነትን አግኝቶ ወደ ሜዳ የሚመለስበትን ሁኔታ በቀጣይ ሳምንታት የምንጠብቀው ይሆናል።

👉ኢዳላሚን በሜዳ ላይ ተጫዋችነት መግባት

በቂ የዝግጅት ጊዜ ያልነበረው እና በዝውውር ወቅት በነበረበት ችግር ምክንያት ባልተሟላ ቡድን ወደ ሜዳ የገባው ጅማ አባ ጅፍር አዳማን በገጠመበት ጨዋታ ላይ ሁለተኛ ግብ ጠባቂም በስብስቡ ውስጥ አላካተትም ነበር። ጨዋታውን የጀመረው አቡበከር ኑሪ ከ8 ደቂቃዎች በኋላ በቀይ ካርድ ሲወጣ በተጠባባቂነት ከተያዙ ተጫዋቾች ውስጥ በቁመት ዘለግ የሚለው ኢዳላሚን ናስር የግብ ጠባቂነት ኃላፊነቱን ተረክቦ ገብቷል። በጨዋታው አራት ግቦችን ቢያስተናግድም የአቅሙን ስለመጣሩ ግን አጠያያቂ አልነበረም። ይኸው የተከላካይ መስመር ተጫዋች ታድያ ቡድኑ በዚህ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ሲገጥም በግራ መስመር ተከላካይነት ጨዋታውን ጀምሯል። አጋጣሚውም በአራቱ ሳምንታት በግብ ጠባቂነት እና በሜዳ ላይ ተጫዋችነት ያገለገለ ተጫዋች አድርጎታል።

👉ባለ ሐት-ትሪኩ ሙጂብ ቃሲም

በተሰረዘው የውድድር ዘመን 2ኛ ሳምንት ጨዋታ ጎንደር ላይ ድሬዳዋ ከተማን አስተናገዶ 5-0 በሆነ ውጤት ፋሲል ከነማ ሲረመርም በወቅቱ ሙጂብ ቃሲም በ8፣ 80 እና 90ኛ ደቂቃ ባስቆጠራቸው ግቦች የ2012 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ሐት-ትሪክ የሰራ ተጫዋች መሆን ችሎ ነበር።

ዘንድሮም ታሪክ ራሱን ደገመና በ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ጎል አስቆጣሪ የሆነው ሙጂብ ፋሲል ከነማ ወላይታ ድቻን 3-2 በሆነ ውጤት ሲረታ የቡድኑን ሦስት የማሸነፍያ ግቦችን በማስቆጠር እንደ አምናው ሁሉ የአዲሱን የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ሐት-ትሪክ የሰራ ተጫዋች መሆን ችሏል።

ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት በመደበኝነት ከተሸጋገረ ወዲህ ግብ ማምረቱን የቀጠለው ሙጂብ ከአራት ጨዋታዎች በሦስቱ ላይ ያስቆጠረ ሲሆን በአጀማመሩ ከቀጠለ ዐምና የጎች አግቢነት ሰንጠረዡን እየመራ በኮሮና ምክንያት ሊጉ እንደመቋረጡ የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ክብር ዘንድሮ ሊያጣጥም ይችላል።

👉የአስቻለው ድንቅ አጀማመር

የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ኮከብ አስቻለው ግርማ ሰበታ ከተማን ለቆ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ካመራ ገና ሁለት ሳምንት ቢያስቆጥርም በቡድኑ በፍጥነት አዎንታዊ ተፅእኖ እየፈጠረ ይገኛል። በሦስተኛው ሳምንት ቡድኑ በኢትዮጵያ ቡና በተሸነፈበት ጨዋታ ኢታሙና ኬሙይኔ ላስቆጠረው ጎል ሲያመቻች በአራተኛ ሳምንት ድሬዳዋ ጅማን 2-0 በማሸነፍ የዘንድሮውን የመጀመርያ ድል ሲያሳካ አንዱን አስቆጥሮ ናንጄቦ ላስቆጠረው ሁለተኛ ጎል ደግሞ በግሩም ሁኔታ አመቻችቷል።

ታታሪው ተጫዋች በድንቅ ጅማሮው ከቀጠለ የማጥቃት እንቅስቃሴው በኤልያስ ማሞ ላይ ጥገኛ ለሆነው እና የጎል እድሎችን በማይታመን መልኩ ለሚያመክነው የፍስሐ ጥዑመ ልሳን ቡድን አዲስ የማጥቃት አድማስ እንደሚፈጥርለት ይጠበቃል።

ተጫዋቹ ከዚህ ሳምንት ጨዋታ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት “ምንም የመዘጋጃ ጊዜ ሳላገኝ ይህን እያደረግኩ ነው። ከዚህ በኃላ እየሠራው ስሄድ የተሻለ ነገር አደርጋለሁ። በአጋጣሚ ከዚህ ቀደም በሌላ ክለብ አብረውኝ ከተጫወቱት ከኤልያስ ማሞ እና ያሬድ ዘውድነህ ጋር አብሬ ስለተጫወትኩ ከቡድኑ ጋር በቶሎ ለመዋሀድ አልተቸገርኩም። እግርኳስ ነው፤ በቀጣይም ከድሬ ጋር የተሻለ ነገር እሰራለው።” ሲል በቀጣይ ከዚህም በላይ እንደሚሻሻል ተናግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ