ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

4ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዚህኛው ሳምንት የታዘብናቸውን ዓበይት ክለብ ነክ ጉዳዮች በተከታዩ ፅሁፍ ለመዳሰስ ሞክረናል።

👉 መልክ እየያዘ የመጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በመጀመሪያው ሳምንት በፋሲል ከነማ ከተረታበት ጨዋታ ወዲህ መሻሻሎችን እያሳየ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን በዚህኛው ሳምንት ሰበታ ከተማ ላይ ተቀዳጅቷል።

በፈረሰኞቹ የ4-2 የበላይነት በተጠናቀቀው የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ በሀዋሳው ጨዋታ ከጉዳት የተመለሰው ጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አቤል ያለውና ጋዲሳ መብራቴ ቀሪዎቹን ግቦች ለቅዱስ ጊዮርጊስ አስገኝተዋል።

የግብ እድሎችን የመፍጠር ችግር የነበረበት ቡድን በተለይ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከፍተኛ እምርታን አሳይቷል። በዚህም አይነተኛ ለውጥ ውስጥ ከጉዳት የተመለሰው ጌታነህ ከበደ እና አቤል ያለው አይነተኛ ሚናን እየተወጡ ይገኛል።

የጎል መንገድ መንገዱ ወለል ብሎ የተከፈተለት የሚመስለው ቡድኑ በስብስቡ በበቂ ሁኔታ ያልተጠቀመበት አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ከጉዳት የተመለሰው ሳላዲን ሰዒድን መያዙን ስናስተውል የፊት መስመሩ ምን ያህል በአማራጭ የተሞላ እንደሆነ ለመመልከት ይረዳል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት ዓመታት በፊት መስመሩ ድክመት የነበረው ቢሆንም በተቃራኒው የተከላካይ መስመሩ ጥንካሬ ቡድኑ ላይ ጎል ለማስቆጠር አዳጋች የነበረ እና በጠባብ ውጤት አሸንፎ እንዲወጣ የሚረዳውም ነበር። ይህ ጥንካሬው ዘንድሮ በመከላከል አደረጃጀቱም ሆነ በግላዊ ስህተቶች የሳሳ ሲሆን በየጨዋታዎችም ጎል እያስተናገደ ይገኛል። በብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት ወቅት ጉዳት አስተናግዶ የነበረው አስቻለው ታመነ በሰበታው ጨዋታ ዳግም ወደ ጨዋታ መመለስ ምናልባትም የአሰልጣኝ ማሔር ዳቪድስ የኋላ መስመርን እንደሚያረጋጋው ይገመታል።

👉 በላቀ ታታሪነት የመጀመሪያ ድሉን ያሳካው ሀዋሳ ከተማ

በመክፈቻ ሁለት ሳምንታት ባደረጓቸው ጨዋታዎች ከሙሉ የጨዋታ ብልጫ ጋር ለሰበታ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅ የሰጡት ሀዋሳ ከተማዎች በዚህኛው ሳምንት ብዙዎችን ባስደመመ መልኩ ከኢትዮጵያ ቡና ላይ ሙሉ ሦስት ነጥብን መውሰድ ችለዋል።

በ59ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ ያስቆጠራት ግብ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ በነበረችበት ጨዋታ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በሁለት ጨዋታ ብቻ ሰባት ግቦችን ያስተናገደውን የቡድናቸውን የመከላከል አደረጃጀት በማሻሻል ሀዋሳ ከተማ የኳስ ቁጥጥርን መሰረት አድርጎ የሚንቀሳቀሰው የካሳዬ አራጌውን ቡድን ተስፋ አስቆራጭ የጨዋታ ዕለት እንዲያሳልፍ አስገድደውታል።

እንደ ቡድን ይንቀሳቀስ የነበረው የሙሉጌታ ምህረት ስብስብ በተለይ የጨዋታውን አመዛኙን ክፍል ከኳስ ውጭ እንደማሳለፋቸው ሙሉ ተጫዋቾቻቸውን ከኳስ ጀርባ በማሰለፍ በላቀ ትጋት በኢትዮጵያ ቡናዎች በመስመሮች ብሎም መሀል ለመሀል የተቃጡባቸውን ጥቃቶች በሙሉ ለመመመከት ከፍተኛ ተጋድሎን በማድረግ ለቡድኑ ቀጣይ ጉዞ ቁልፍ መሆን የሚችል ትልቅ ሦስት ነጥብን ማግኘት ችለዋል።

👉 የመጀመሪያ ድላቸውን ያሳኩት ድሬዎች

አዝናኝ ባልነበረውና የተጫዋቾች ግላዊ ስህተቶች ጎልተው በወጡበት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች በአስቻለው ግርማ እና ጁኒያስ ናንጂቡ ግቦች ጅማ አባጅፋርን በመርታት የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸውን ፍጥነት ለመጠቀም ጥረት የሚያደርጉት ድሬዳዋ ከተማዎች ይህ ጥረታቸው በዚህ ሳምንት በአንፃራዊነት ፍሬያማ ነበር። የተግባቦትና የስልነት ችግር የሚስተዋልበት የድሬዳዋ ከተማ የፊት መስመር ተጋጣሚያቸው ከድሬዳዋ ከተማ በባሰ ደረጃ ያልተደራጀው ጅማ አባጅፋር ሆነ እንጂ በአጨራረስ ድክመታቸው እንዳለፉት ጨዋታዎች ሁሉ ወጋ በከፈሉ ነበር።

በመዲናይቷ ክለቦች ተከታታይ ሁለት ሽንፈቶችን አስተናግደው የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በዚህኛው ሳምንት ያገኙት የመጀመሪያ ድል ለቀጣይ ጨዋታዎች መነቃቃትን ይፈጥርላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ተፈትኖ ያሸነፈው ፋሲል ከነማ

በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመርያ 23 ደቂቃዎች ብቻ አራት ግቦችን ባስተናገደው የሳምንቱ አዝናኝ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ወላይታ ድቻን 3-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።

ፋሲል ከተማዎች በ4ኛውና በ13ኛው ደቂቃ ሙጂብ ቃሲም አከታትሎ ባስቆጠራቸው ግቦች ገና ከማለዳው 2-0 መምራት ቢጀምሩም ድቻዎች በ18ኛውና በ23ኛው ደቂቃ በስንታየሁ መንግሥቱና ፀጋዬ ብርሃኑ አከታትለው ባስቆጠሯቸው ግቦች ጨዋታው 2-2 መሆን ችሎ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ የአቻ ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደ በራሳቸው ሜዳ ያደሉት ድቻዎች ተደጋጋሚ ጫናዎችን ከተጋጣሚያቸው መጋበዛቸው አልቀረም። በዚህም በ72ኛው ደቂቃ ሰዒድ ሀብታሙ መስመሩን አስቀድሞ በመልቀቁ ለሁለተኛ ጊዜ ሙጂብ ቃሲም መትቶ ባስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ፋሲል ከነማዎች ድል ማድረግ ችለዋል።

ፋሲሎች ገና በጊዜ ባስቆጠሯቸው ተከታታይ ጎሎት መምራታቸው በቀሪው ደቂቃ ሊኖራቸው የሚገባውን የትኩረት ደረጃ እንዳጡ ተስተውሏል። ሁለት ጎሎች ከተቆጠረባቸው በኋላም ወደ ጨዋታው ቅኝት ለመግባት ሲቸገሩ በሚገባ ታይቷል። ዐጼዎቹ ለሊጉ ክብር ከታጩ ቡድኖች መካከል ቢገኙም በከፍተኛ የትኩረት ደረጃ ካለመጫወት በሚመነጭ በቀላሉ የሚያስተናግዷቸው ጎሎች በቀጣይ ውጤት ሊያሳጣቸው ይችላል።

👉 ከድል ጋር የታረቁት ወልቂጤ ከተማዎች

በመጀመሪያ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት መልካም የሚባልን እንቅስቃሴ አድርገው ነገር ግን በሙሉ ሦስት ነጥብ ማጀብ ያልቻሉት ወልቂጤ ከተማዎች ባሳለፍነው ሳምንት ወላይታ ድቻን በዚህኛው ደግሞ ጠንካራው ባህር ዳር ከተማን በመርታት ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

እንደ ሀዲያ ሆሳዕና ሁሉ እስካሁን ምንም ሽንፈት ያላስተናገዱት ወልቂጤ ከተማዎች ቶማስ ስምረቱ በ32ኛው ደቂቃ በግንባሩ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ከባህርዳር ከተማ ላይ ወሳኝ ሶስት ነጥብን ወስደዋል።

በተደጋጋሚ የተጫዋቾች ለውጥ ቢስተዋልበትም በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደው የኋላ ክፍል የቡድኑ ዋንኛ የውጤት መሠረት መሆን የቻለ ሲሆን በተሰጥኦ እና አማራጭ የተሞላው የአማካይ ክፍልም መልካም ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። ሆኖም በፊት መስመር ያለው ስል አልባነት እንዳለፉት ጨዋታዎች ሁሉ በዚህኛውም የጨዋታ ሳምንት ላይ የታየ ሲሆን የሚፈጠሩ የጎል እድሎችን እንደዋዛ ማምከን የቡድኑ መለያ ባህርይ የሆነ ይመስላል። የማጥቃት እንቅስቃሴውንም ሆነ የአጥቂዎችን ግላዊ ብቃት ማሻሻል የአሰልጣኝ ደግአረገ ቀጣይ የቤት ስራ ይሆናል።

👉 ምናባዊ ግምት እና ዕውነታው ያልተጣጣመላቸው ሲዳማ ቡናዎች

በ4ኛ የጨዋታ ሳምንት የማሳረጊያ ጨዋታ ለመግለፅ በሚያዳግት ሁኔታ እጅግ አሰልቺ በነበረው ጨዋታ ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ በሆነ ውጤት ተለያይተዋል።

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ በመክፈቻዎቹ ሁለት ጨዋታዎችን በመሸነፋቸው ሙሉ ሦስት ነጥብ በማስመዝገብ የውድድር ዘመኑን ጅማሯቸውን የማቃናት ግዴታ ውስጥ ሆነው ነበር ሲዳማ ቡናዎች ጨዋታውን ያደረጉት።

ከጨዋታው መጀመር አንስቶ ተጫዋቾች በሚያሟሙቁበት ብሎም ከጨዋታው መጀመር በፊት በመልበሻ ቤት የነበሩ ሁነቶች የሲዳማ ቡና ተጫዋቾቹ ተጋጣሚያቸው ዳግም ከምንም እየተገነባ የሚገኘውና ደካማ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው አዳማ ከተማ

እንደመሆኑ በከፍተኛ ደረጃ ጨዋታው እንደሚያሸንፉ የእርግጠኝነት ስሜት ይነበብባቸው ነበር።

ሜዳ ላይ የተመለከትነው እውነታ ግን የዚህ ተጋላቢጦሽ ነው። በብዙዎች የማሸነፍ ቅድመ ግምት አግኝተው የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ዝቅተኛ ግምት ከተሰጣቸው አዳማ ከተማዎች ጋር 0-0 በሆነ ውጤት ለመለያየት ተገደዋል። ጨዋታውም እግርኳስ በስብስብ ጥራት ወይንም ለረጅም ጊዜ አብሮ በመቆየት ሳይሆን በጨዋታ ዕለት ተጫዋቾች ሜዳ ላይ በሚሰጡት የ90 ደቂቃ እንደሚወሰን ያስታወሰ ጨዋታ ነበር። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ከፍ ባለ የመነቃቃትና የራስ መተማመን ደረጃ የነበሩት የሲዳማ ቡና ቡድን አባላት ሆነ አሰልጣኞችና ተጫዋቾች ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ ባለማመን ስሜት ውስጥ ሆነው የጨዋታውን ውጤት ለመቀበል ተቸግረው ተስተውሏል።

👉 ጊዜ እየቀደመው የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር

የዘንድሮው የውድድር ዓመት ዓይን ጨፍኖ የመግለጥ ያህል በፍጥነት እየተጓዘ ይገኛል። ገና ሊጉ ከተጀመረ 18 ቀናት ያክል ቀናት ተቆጥረው ሊጉ የአራት ሳምንታት ጨዋታዎች ተደርገዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ስህተትን ለማረም፣ አቅምን ለማሻሻል፣ ጉዳትን ለማስታገስ እና ከሽንፈት ለማገገም ዕድል የማይሰጠው መርሐ ግብር እንደ ጅማ አባ ጅፋር ላሉ ለውድድሩ በአግባቡ ተዘጋጅተው ላልመጡ ቡድኖች እጅግ ፈታኝ ነው።

ቢያንስ ሌሎቹ ቡድኖች ካለፈው ጨዋታቸው መነሻነት ስለ ቀጣዩ ጨዋታ ሲያስቡ አዳዲስ ችግሮች የማያጣው ጅማ አባ ጅፋር የሜዳ ውጪ ችግሮቹ ስለቀጣይ ጨዋታ እና ተጋጣሚ ብቻ እንዳያስብ እያደረገው ይገኛል።

አሰልጣኙም በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደሚመደመጡት እስካሁን በሊጉ ያደረጓቸው ውድድሮች እንደ ወዳጅነት ጨዋታዎች እየተጠቀሙ ቢገኝም ውድድሩ በጨዋታ ሳምንቶች መካከል ያለው የቀናት ልዩነት እጅግ የጠበበ ከመሆኑ አንፃር ጅማዎች በፍጥነት ነገሮችን ማስተካከል ካልቻሉ ፋታ አይሰጤው መርሃግብር ነገሮችን ሊያከብድባቸው ይችላል።


© ሶከር ኢትዮጵያ