የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በአራተኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትኩረት ሳቢ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና ዐበይት አስተያየቶችን እነሆ ብለናል።

👉”በማሸነፍ ውስጥም ስለመሻሻል ማሰብ” የአሰልጣኞቻችን በጎ ጅምር

በሀገራችን እግርኳስ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስፋት እየተለመደ በመጣው የአሰልጣኞች ድህረ ጨዋታ አስተያየቶች ውስጥ የተሸነፈው ቡድን አሰልጣኝ በዳኝነት፣ በተጫዋቾች ጉዳት፣ በሜዳውና መሰል ጉዳዮች ላይ ሽንፈቱን ማሳበብ በተቃራኒው የአሸናፊው ቡድን አሰልጣኝ ደግሞ ያሸነፈበት መንገድ በውል ባልተለየበት ሁኔታ በደስታ ስካር ቡድኑ ሙሉ እንደሆነና መሻሻል የሚገባቸው ነገሮችን ቸል ያለ ገራገር አስተያየት መስጠታቸው የተለመደ ነው።

በዘመናዊ የእግርኳስ አስተሳሰብ ውስጥ ቡድኖች በመረጡት የጨዋታ መንገድ ከፍፁም የበላይነት ጋር ጨዋታዎችን እያሸነፉ እንኳን አሰልጣኞቹ ግን ከተጫዋቾቻቸው “ፍፁማዊነት” ይጠብቁ ይመስል ሲረኩ አይስተዋልም።

ታድያ በሀገራችንም ምንም እንኳን በተግባር የተፈተነ ባይሆንም አሁን አሁን ግን እግርኳስን በጥልቀት ለመረዳት የሚጥሩ አንዳንድ አሰልጣኞች በሊጉ ብቅ ብቅ ማለታቸውን ተከትሎ በማሸነፍ ውስጥም ስለመሻሻል የሚናገሩ፣ በቀላሉ በቡድናቸው እንቅስቃሴ የማይረኩ አሰልጣኞች ቢያንስ በድህረ ጨዋታ አስተያየቶች ላይ መታዘብ ጀምረናል።

ለማሳያነትም በ4ኛ ሳምንት ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ድሬዳዋ ከተማ ጅማ አባጅፋርን ቢረታም፤ ፋሲል ከተማም ተፈትኖም ቢሆን ወላይታ ድቻን ከረታበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች ቢያሸንፉም ያልረኩባቸው ነገር ስለመኖራቸው አልሸሸጉም።

የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ፍሰሐ ጥዑመልሳን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ውጤቱ ራስ መተማመንን በማሳደግ ረገድ ከሚኖረው አስተዋጽኦ ባለፈ በጨዋታው አለመደሰቱን ሲገልፅ የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ደግሞ ውጤት ከማስመዝገባቸው በዘለለ ብዙ ክፍተቶች መኖሩን ሳይሸሽጉ እነዚህን ለማሻሻል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

👉የተጋጣሚ አጨዋወት ላይ የተመሰረተው የአሰልጣኞች አቀራረብ

በ4ኛ የጨዋታ ሳምንት ከተመለከትናቸው ጨዋታዎች መካከል ሙሉጌታ ምህረት ኢትዮጵያ ቡናን፣ ደለለኝ ደቻሳ ፋሲል ከነማን፣ ደግአረገ ይግዛው ባህር ዳር ከተማን በገጠሙባቸው ጨዋታች ላይ ቡድኖቻቸው ለወትሮ ከሚከተሏቸው አቀራረቦች በመጠኑም ቢሆን ለወጥ ያለን አቀራረብ አስመልክተውናል።

በተለይ ሙሉጌታ ምህረት ከጨዋታው ይዘውት የሚወጡት ነጥብን አስፈላጊነት ከግምት በማስገባት እጅግ ጥብቅ የመከላከል አጨዋወትን በቡናው ጨዋታ ላይ ተግብረዋል። በዚህም ቡናዎችን አላፈናፍን ብለው የረባ ጥቃት ከመሰንዘር አግደዋቸዋል። የማጥቃት ምርጫቸውን በተከላካዮች ጀርባ የሚጣል ኳስ ላይ በማድረግም ብቸኛዋን ጎል በብሩክ በየነ አማካኝነት አስቆጥረው ውጤት አግኝተውበታል። በተለይም የቡና ዋነኛ የማጥቃት መስመር የሆነው አቡበከር ነስር የተሰለፈበትን የቡድኑን የግራ ወገንም ሆነ አቤል ከበደ የነበረበትን የቀኙን ክፍል ሀዋሳዎች የተቆጣጠሩበት መንገድ አዋጭ ሆኖላቸዋል። የቡናን ቅብብሎች እንዳይከወኑ በራሱ ሜዳ ከማፈን ይልቅ የመስመር አጥቂዎች እና ተከላከዮቻቸውን በማቀራረብ እንዲሁም አማካዮችን ክፍተት በማሳጣት ሀዋሳዎች ተጋጣሚያቸው ወደ ሳጥናቸው እንዳይደርስ አድርገውት ውለዋል።

ደለለኝ ደቻሳ ከጨዋታ በፊት በሰጡት አስተያየት በፋሲል አጨዋወት ላይ የተመሰረተ አቀራረብ ይዘው እንደሚገቡ ገልፀው የነበረ ቢሆንም በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ጎሎች ተቆጥረውባቸው የመጀመርያ እቅዳቸው ያልተሳካ መስሎ ነበር። ሆኖም በፍጥነት ሁለት ጎሎች አስቆጥረው አቻ ከሆኑ በኋላ በአማካይ ክፍል ባሰለፏቸው ሁለት የተከላካይ አማካዮች የፋሲልን የማጥቃት እንቅስቃሴም ሆነ ተጫዋቾችን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት ቢያንስ አንድ ነጥብ ሊያስገኝላቸው ተቃርቦ ነበር። ከኃላ በሰሯቸው ክፍተቶች የተቆጠሩት ግቦች ዕቅዳቸውን ያፋልሰው እንጂ እንዳሰቡት የተጋጣሚያቸውን አማካይ ክፍል እንቅስቃሴ ቢገድቡ ፋሲሎች ክፍተት ፍለጋ በሚያደርጉት ጥረት እንደቡናው ጨዋታ ሁሉ ለድቻዎች የመልሶ ማጥቃት ዕድል ሊከፍቱ በቻሉ ነበር።

በተመሳሳይ ባህር ዳርን የገጠሙት አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የፋሲል ተካልኝን የአጨዋወት መንገድ የተረዱት የሚመስል መልኩ የአማካይ ተጫዋቾችን በማብዛት ቡድኑ በቅጡ ቅብብል እንዳያደርግ ገድበውታል። በዚህም የአማካይ እና የአጥቂ ክፍሉ እንዲሁም በአማካይ ተጫዋቾች መካከል የነበረውን የመገናኛ መንገድ ከመዝጋታቸው ባሻገር የጎል ምንጭ የሆነው ፍፁም ዓለሙ ድንገተኛ የማጥቃት ሩጫዎችንም ሰፊ ክፍተት ባለመስጠት ገድበውት ውለዋል። በሜዳው ቁመት ቡድኑ የነበረው ጥቅጥቅነትም የማጥቃት ባህሪ ያላቸው የባህር ዳር ተጫዋቾች እንቅስቃሴ በተጫዋቾቻቸው የቅርብ ርቀት ቁጥጥር እንዲደረገበት እንዲሁም ንክኪዎቻቸውን በቀላሉ ለማቋረጥ ቀላል አድርጎላቸዋል።

👉 የፋሲል ተካልኝ ቅድመ ጨዋታ አስተያየት

በዚህ ሳምንት ትኩረት ከሳቡ አስተያየቶች መካከል የባህር ዳሩ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የቡድናቸው ቁልፍ ተጫዋች የሆነው ፍፁም ዓለሙ ከጨዋታ ጨዋታ አቋሙ እየደበዘዘ ስለመምጣቱ ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ ነበር። ፍፁም የቡድኑ ወሳኝ የማጥቂያ መሳርያ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በጨዋታዎች ላይ በተጋጣሚ ተጫዋቾች ጥብቅ ትኩረት ሲደረግበት ይስዋላል። ይህን ተከትሎም አሰልጣኙ ተጫዋቾቹን ለማቆም አላስፈላጊ ጥፋቶች እየተሰሩበት ስለመሆኑ ገልፀው ዳኞች ለመሰል ተጫዋቾች ጥበቃ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልፀዋል።

” ፍፁም በመጀመርያ ቀን ሁሉም ሊያያቸው የሚወዳቸው አይነት ማራኪ ጎሎች ስላገባ በቀጣይ ጨዋታዎች ከእርሱ በጣም ስለተጠበቀ የደበዘዘ መሰለ እንጂ ከዛ በኋላም ጥሩ ሲንሳቀስ እና ተጋጣሚ ሲያስቸግር አይቻለሁ። ከሁሉም በላይ ግን ተጋጣሚዎቻችን እሱን ለማቆም አላስፈላጊ እና ከሚገባው በላይ ጉልበት እየተጠቀሙ ስለሆነ ዳኞች እንዲህ አይነት ተጫዋቾችን መጠበቅ ይገባቸዋል ብዬ አስባለሁ።” ብለዋል።

👉 ተስፋ ያልቆረጡት ጳውሎስ ጌታቸው

በውጤትም ሆነ በአስተዳደራዊ ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋርን እየመሩ የሚገኙት ጳውሎስ ጌታቸው ከጨዋታ በፊት እና በኋላ በሚሰጧቸው አስተያየቶች በቡድኑ ተስፋ እንደማይቆርጡ ሲገልፁ እየተስተዋለ ይገኛል።

በዚህኛው ሳምንት ምንም እንኳን ቡድኑ ሽንፈት ቢያስተናግድም አሰልጣኙ አሁንም ቢሆን ተስፋ እንደማይቆርጡ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። አሰልጣኙ ሲናገሩ “ብዙ ጨዋታዎች አሉ። ድጋፍ እስካለን ድረስ የሚደረገውን ነገር ለማድረግ እስከመጨረሻው ድረስ የጅማ አባ ጅፋር ደጋፊ እና ሕዝብ አደራ ስላለብኝ እታገላለሁ።”ሲሉ ተደምጠዋል።

ዐበይት ድሕረ ጨዋታ አስተያየቶች

👉 አብርሀም መብራቱ በተከላካዮች ስህተት ስለተቆጠረው ግብ…

“የምንፈልገውን የአጨዋወት ሒደት ተከትለን ስንሠራ እንደዚህ ዓይነት ስህተቶች ይሰራሉ። ያም ሆኖ ግን ያንኑ የአጨዋወት መንገዳችንን አልቀየርንም። ስለዚህ በቀጣይ እንደዚህ ዓይነት ስህተቶች እንዳይሰሩ እናደርጋለን እንጂ ይሄ ስህተት ተሰርቷል ብለን የአጨዋወት ፍልስፍናችንን አንቀይርም።”

👉ሙሉጌታ ምህረት ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ስላገኙት ድልና ስለተከተሉት መንገድ…

“ተከታታይ ሽንፈቶችን ካስተናገድን በኋላ ነጥብ ያስፈልገን ነበር። እርግጥ ከሰበታ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ማገኘት ይከብዳል። ምንም ቢሆንም ግን በራሳችን ላይ ህልውናችንን ወስነን ነበር የመጣነው። ነጥቡ እንደሚያስፈልገን አምነን ነበር፣ ይህም ተሳክቶልናል። በአጠቃላይ ግን ነጥቡ ስለሚያስፈልገን አጨዋወታችንን ገድበን ተጫውተናል።”

👉ካሳዬ አራጌ ስለ አማራጭ የጨዋታ ስልት…

“አንድ ቡድን መሐል ላይ ተከማችቶ ሲጫወት መስመሩን ይለቅልሃል። በዚህ ደግሞ መስመሩን በመጠቀም የግብ እድል መፍጠር አልያም መስመሩን በመጠቀም መሐሉን ማስከፈት ነው የምትችለው። ሌላው አማራጭ ተጋጣሚ የተከማቸበት ቦታ ላይ ረጅም ኳሶችን መጣል ነው። ሌላ የተለየ አማራጭ ግን አይኖርም። ግን በዝግ ቦታዎች ላይ ክፍተቶችን ፈልጎ ማግኘት የተጫዋች ብቃት ይጠይቃል።”

👉ሥዩም ከበደ ስለሙጂብ ቃሲም …

“ሙጂብ ሳጥን አካባቢ ያለው ነገር በሙሉ ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም የጎል ሰው ነው። ልምምድ ላይም እንደዛው ነው፤ ልምምድ ላይ የሚያደርጋቸውን ነገሮች እዚህም ያደርጋቸዋል። እንደውም ሦስት ብቻ አይደለም ቦታው ላይ እንደመገኘቱ አጥቃቀሙን የበለጠ ቢያስተካክል ኖሮ ደግሞ ደብል ሐት-ትሪክ መስራት የሚችልበት አቅም አለው። በጣም ተስፈኛ ነው። ወደፊትም ለሀገር ብዙ የሚጠቅም ነው። ብዙ ነገሮችን እያሻሻለ ይሄዳል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ።”

👉 ደለለኝ ደቻሳ ስለ ዳኝነት…

“በፍፁም ቅጣት ምቱ መሰጠት እና መደገም ሳይሆን ሊጋችን ላይ ለሁሉም ቡድን ዳኝነት እኩል ቢሆን ብዬ የግል አስተያየቴን እሰጣለሁ። አዳማን ባሸነፍንበት ጨዋታም የዳኞች ስህተቶች ነበሩ። በየጨዋታው የዳኝነት ስህተት ዋጋ እያስከፈለን ነው። ስለዚህ የሚመለከተው አካል ቡድኖችን በእኩል ዓይን ቢያይ ብዬ የግል አስተያየቴን እሰጣለሁ። ተጫዋቾቼ ማድረግ ያለባቸውን ነገር እያደረጉ ሳለ አላስፈላጊ ካርዶች ከጨዋታው ሪትም እንዲወጡ ያደረገበት ሒደት ስላለ ይታሰብበት ነው የምለው።”

👉ደግአረገ ይግዛው ስለአህመድ ሁሴን…

“አህመድ ሁሴን ገና እያደገ ያለ ተጫዋች ነው፤ የልምድ እጥረቶች አሉበት። ሆኖም ግን ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተጋጣሚ ተከላካይ ላይ ጫና የመፍጠር እንቅስቃሴው በጣም ጥሩ ነው። ጎል ላይ የሚገኝበትም መንገድ እንደተመለከታችሁት ነው። የመጨረሻ ንኪኪው ላይ ብዙ ስራ ይጠይቃል። ከጎል ስለራቀ እና ወደ ጎል ለመምጣት ያለው ጉጉት ከፍተኛ ስለሆነ አንዳንዴ ለማመን የሙያስቸግሩ ኳሶች ይሳታሉ። በሂደት ግን ይመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። እኛም በእሱ ተስፋ አንቆርጥም።”

👉ፋሲል ተካልኝ ተገቢ ነው ስላሉት የወልቂጤ ሽንፈት…

በመጀመሪያ ተጋጣሚዎችን እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። በመጀመሪያው አጋማሽ በተለይ ጎል ከገባብን በኋላ በአካልም በአዕምሮም ደክመን የታየንበት ነበር። እንደአጠቃላይ እንደ 90 ደቂቃ ጥሩ አልተጫወትንም። በቡድኔ ደስተኛ አይደለሁም። መሸነፋችን የሚጠበቅ ነው ፤ ጥሩ ካልተጫወትን። ግን ያው እግር ኳስ ነው እና ለሚቀጥለው ጨዋታ ራሳችንን አዘጋጅተን እንመጣለን።

👉ዘርዓይ ሙሉ የውጪ ተጫዋቾችን በጨዋታ ዕለት ስብስብ አለመካተታቸው ስላለው ተፅዕኖ…

“እጅግ በጣም ተፅዕኖ አለው። አንደኛ ከቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ሦስት ተጫዋቾች ጉዳት ላይ ይገኛሉ። ከውጪ ያመጣናቸው ተጫዋቾችም በየቦታው በድኑን ይጠቅማሉ ብለን ነው። ቢያንስ ከዋና ቡድኑ ወደ ሰባት ተጫዋቾች የሉንም ማለት ነው። በዚህ መንገድ ነው ሦስቱንም ጨዋታ ያደርገነው። ይሄ ሌላው ፈታኝ ነገር ነው የሆነብን። ለወልቂጤው ጨዋታም ይደርሱ እንደሆን አላውቅም።”


© ሶከር ኢትዮጵያ