የአራተኛ ሳምንት ዐበይት ጉዳዮችን የምናገባድደው በዚህ ሳምንት ትኩረት የሳቡ ሌሎች ጉዳዮችን በማንሳት ነው።
👉በሀዘን ውስጥ ሆነው ከክለባቸው ያልተለዩት አብነት ገ/መስቀል
ከጥቂት ቀናት በፊት እህታቸውን በሞት የተነጠቁትና ሀዘን ላይ የነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አብነት ገ/መስቀል ክለባቸው በዕለተ ሰኞ ሰበታ ከተማን 4-2 በረታበት ጨዋታ ግን ሀዘናቸውን ገታ አድርገው የክለባቸው ጨዋታ ለመታደም በስታዲየም ተገኝተው ነበር።
ክለባቸው በሜዳ ላይ ለሀዘናቸው መፅናኛ ይሆን ዘንድ ጣፋጭ ድልን አበርክቶላቸዋል። ይህ ድርጊታቸው በተለየ እንደው የእንጀራ ነገር ሆኖባቸው እንጂ ለእግርኳሱ የረባ ስሜት ሳይኖራቸው በተለያዩ የመንግስት ተቋማት በሚተዳደሩ ክለቦች ለተሰገሰጉ አንዳንድ አመራሮች ትምህርት የሚሰጥ ነው። እግርኳስ ከእንጀራነትም ባለፈ በላቀ የስሜት ትስስር የሚኖር የህይወት አካል ስለመሆኑ የአብነት ድርጊት ማሳያም ነው።
👉 ትኩረት የሚሻው የክለቦች የኮቪድ ምርመራ ውጤት
ከኮቪድ 19 ወረርሺኝ መከሰት ተከትሎ እግርኳሳዊ ውድድሮች ዳግም መካሄድ ከጀመሩበት ቀን አንስቶ የተሳታፊ ክለቦች የቡድን አባላት ከውድድሩ 72 ሰዓታትን አስቀድመው ወቅታዊ የኮቪድ ምርመራ ውጤታቸውን ለውድድሩ አስተዳዳሪ አካል የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው በውድድሮች ደንብ ላይ እንዲሰፍር ተደርጓል።
በዚህ መሰረት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ክለቦች የቡድን አባላቶቻቸውን በማስመርመር ውጤታቸውን ለአክስዮን ማኅበሩ እያቀረቡ ይገኛል። ሆኖም አንድ ክለብ በ4ኛው የጨዋታ ሳምንት ለአክስዮን ማኅበሩ ገቢ ያደረገው የምርመራ ሪፖርት ከዚህ ቀደም ለነበረው የ3ኛ የጨዋታ ሳምንት ያሰራውን የምርመራ ውጤት ስለመሆኑ ተሰምቷል።
እርግጥ ነው ምርመራው በራሱ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ እንደመሆኑ ክለቦች ላይ በፋይናንሱ ረገድ የሚፈጥረው ጫና በግልፅ የሚታወቅ ቢሆንም ከቫይረሱ የስርጭት ባህሪ አንፃር ምንም እንኳን በጨዋታ ሳምንታት መካከል ያለው የቀናት መቀራረብ ከግምት ገብቶ ሊሆን ቢችልም መሰል ቸልተኛ አካሄዶች መዘዛቸው የከፋ ሊሆን ስለሚችል ከወዲሁ የሚቀርቡ የምርመራ ውጤቶች አግባብነት ዙርያ የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል።
👉የመርሐ ግብሩ መጠቅጠቅ
ለወትሮም ቢሆን በአካል ብቃት የዝግጁነት ደረጃ በርካታ ጥያቄዎች በሚነሳበት የሀገራችን እግርኳስ የዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር ከሌላው ጊዜ በተለየ የተጨናነቀ ይመስላል።
ለማሳያነትም ባሳለፍነው አርብ ፍፃሜውን ካገኘው የ3ኛ ሳምንት በኃላ በሁለት ቀናት ልዩነት 4ኛ ሳምንት የተደረገ ሲሆን 5ኛ ሳምንት እንዲሁ ከአንድ ቀናት በኃላ ከአርብ እስከ እሁድ የሚካሄድ ይሆናል። ቀጣዩ የ6ኛ ሳምንት ጨዋታም እንዲሁ 5ኛ ሳምንት ከተጠናቀቀ ከአንድ ቀን በኃላ የሚካሄድ ይሆናል። ታድያ በዚህ የተጨናነቀ መርሃግብር ውስጥ ክለቦች በምንም መልኩ ይወጡት ይሆን የሚለው ነገር ጥያቄን ይፈጥራል።
በእግርጥ ውድድሩ በአንድ ቦታ ሰብሰብ ተብሎ የሚደረግ ከመሆኑ አንፃር የጉዞ ድካም አለመኖሩ ታሳቢ ተደርጎ አልያም ዘግይቶ በመጀመሩ ክረምት ከመድረሱ በፊት በቶሎ ለማጠናቀቅ እንዲረዳ የተቀረፀ መርሐ ግብር ሊሆን ቢችልም ከሳምንት ሳምንት ወጥ የሆነ እንቅስቃሴን የሚያሳዩ ክለቦች ብርቅ በሆነበትና መዋዠቅ መለያቸው በሆኑ ክለቦች በተሞላው ሊግ መሰል የመርሐ ግብር መጨናቀቆች ታክለውበት እንዴት ይሆናል የሚለው ይጠበቃል።
👉ጎሎች የበዙለት ሊግ
ያለ ጎል የሚጠናቀቁ ጨዋታዎች፣ የወረደ የማጥቃት ፍላጎት፣ አነስተኛ ጎሎች መለያው የነረው ሊግ ዘንድሮ ከወትሮው በተለየ በርካታ ጎሎች እያስተናገደ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በመጀመርያዎቹ የሊግ ጨዋታዎች ቡድኖች በሚገባ ወደ ቅኝት ለመግባት ከመቸገር የተነሳ እጅግ ጥቂት ጎሎች ሲስተናገዱ መመልከት የተለመደ ሲሆን ወደ ማገባደጃው ሲደርስ በድንገት በርካታ ጎሎች ሲቆጠሩ ይስተዋል ነበር።
ዘንድሮ በተለየ መልኩ በአራት ሳምንታት በተደረጉት 24 ጨዋታዎች 71 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን በአማካይ በጨዋታ ወደ ሦስት ጎሎች ይቆጠራሉ። ያለ ጎል የተጠኔቀቁ ጨዋታዎች ደግሞ ሁለት ብቻ ነው። ይህም ከሌሎች የውድድር ዓመታት የተሻለ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።
ለጎሎች መጨመር እንደምክንያትነት ሊጠቀሱ የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች የሚነሱ ሲሆን ጨዋታዎች የቴሌቪዥን ስርጭት እድል በማግኘታቸው ተጫዋቾች ራሳቸውን ለማሳየት የሚያደርጉት ጥረት መጨመሩ አልያም ጨዋታዎች ከረጅም እረፍት በኋላ ቶሎ ቶሎ እየተደረጉ በመሆናቸው የቡድን ውህደት ላይ ክፍትት መኖሩ ብሎም የተሟላ የአካል ብቃት ካለመኖሩ ጋር በተያያዘ በቀላሉ ግብ ማስተናገዳቸው እንደምክንያት ሊጠቀስ ይችላል።
© ሶከር ኢትዮጵያ