ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ4ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት በተደረጉት ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ብቃት አሳይተዋል ያልናቸውን ተጫዋቾች እና ዋና አሰልጣኝ በማካተት ተከታዩን ምርጥ ቡድን መርጠናል።

አሰላለፍ 3-2-3-2

ግብ ጠባቂ

ፍሬው ጌታሁን – ድሬዳዋ ከተማ

በሦስተኛው የጨዋታ ሳምንት በተጠባባቂነት ይዘነው የነበረው ፍሬው በዚህ ሳምንት ደግሞ ባሳየው ብቃት ወደ መጀመሪያ ተመራጭ አድርገን አምጥተነዋል። በሳምንቱ ግብ ሳያስተናግዱ ከወጡ አራት ግብ ጠባቂዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ፍሬው ጥሩ በራስ መተማመን ባሳየበት ጨዋታ ጥቂትም ቢሆኑ የተሞከሩበትን ኳሶች በማዳን ከስህተትም ነፃ የሆነ ጨዋታ አሳልፏል።

ተከላካዮች

ዘነበ ከድር – ሀዋሳ ከተማ

ሁለገቡ የመስመር ተጫዋች ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን በገጠመበት ጨዋታ በቀኝ መስመር ተከላካይነት ተሰልፏል። የበዛ የማጥቃት ተሳትፎ ባይኖረውም ቡድኑ ይዞት ከገባው የጨዋታ ዕቅድ አንፃር ከፊቱ ከነበረው ብርሀኑ በቀለ ጋር ጥሩ መናበብን በመፍጠር የቡናን የግራ መስመር ማጥቃት መቆጣጠር ችሏል። በዚህም በሦሰትት ተከላካዮች በተዋቀረው ምርጥ አስራ አንድ የቀኝ ክፍል ላይ አካተነዋል።

ምኞት ደበበ – ሀዋሳ ከተማ

የቀድሞው የደደቢት እና አዳማ ግዙፍ ተከላካይ ከጉዳት መልስ በሀዋሳ መለያ ሁለተኛ ጨዋታውን አድርጓል። ቡድኑ በከፍተኛ ተጋድሎ የመጀመሪያ ሦስት ነጥቦቹን ባሳካበት ጨዋታውም ሥራ በዝቶበት ቢያረፍድም የተከላካይ ክፍለን እየመራ አደገኛ ካሶችን በመቆጣጠር ሀዋሳ ግብ እንዳይቆጠርበት ወሳኝ ሚና ተወጥቷል።

አሚን ነስሩ – ወልቂጤ ከተማ

ዳግም ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ የተመለሰው አሚን ባለፈው ሳምንት ተቀይሮ በመግባት ከተጫወተበት የአማካይ መስመር ሚና ወደ መሐል ተከላካይነቱ ተመልሷል። ባደረገው እንቅስቃሴም የባህር ዳርን የማጥቃት ሂደት ፍሬ አልባ በማድረግ ውስጥ አጥቂዎች ወደ ሳጥን ዘልቀው እንዳይገቡ የድርሻውን መወጣት ችሏል። ከአጣማሪው ቶማስ ጋር የነበረው ጥምረትም ግሩም ነበር።

አማካዮች

ሀብታሙ ሸዋለም – ወልቂጤ ከተማ

ጥሩ ብቃቱ ላይ ሲገኝ በተጋጣሚ የኋላ ክፍተቶችን መፍጠር የማይከብደው የፍፁም ዓለሙው ባህርዳር በወልቂጤው ጨዋታ ይህን ማድረግ ተስኖት ታይቷል። ለዚህም ወሳኝ ሚና የተጫወተው የተከላካይ አማካዩ ሀብታሙ ብልጠት የተሞላበት አጨዋወት ከቡድን ጓደኞቹ ጋር በመሆን የተጋጣሙውን የማጥቃት አማካዮች እንቅስቃሴ መግታት ችሏል።

ጋብርኤል አህመድ – ሀዋሳ ከተማ

ጋናዊው የተከላካይ አማካይ ከቀድሞው ክለቡ ጋር በጀመረው የውድድር ዓመት የመጀመሪያውን ጥሩ አቋም አሳይቷል። በሦስተኛው ሳምንት ተቀይሮ ወጥቶ የነበረው አህመድ በዚህ ሳምንት ግን የኢትዮጵያ ቡና አማካዮችን ቅብብል በማምከን ከጀርባው ላሉ ተከላካዮች ጠንካራ ሽፋን መስጠት ችሏል። እንደ ቡድን እንዲንቀሳቀሱ የማስባበር ሚና ሲወጣም ተስተውሏል።

አስቻለው ግርማ – ድሬዳዋ ከተማ

ለአዲሱ ቡድኑ ሁለተኛ ጨዋታውን ያደረገው አስቻለው ግርማ ለቡድኑ ቀጣይ ጉዞ መሻሻል መፍትሄ መሆን እንደሚችል ፍንጭ የሰጠበትን ጊዜ አሳልፏል። የመስመር አጥቂው የትውልድ ከተማውን ቡድን በገጠመበት ጨዋታ የድሬዳዋን ቀዳሚ ግብ ሲያስቆጥር ቀጣይዋን ለጁኒያስ ናንጁቡ አመቻችቶ አቀብሏል። በጨዋታው የነበረው የታታሪነት ደረጃም ግሩም ነበር።

ፍሬው ሰለሞን – ወልቂጤ ከተማ

ወልቂጤዎች ታታሪነታቸውን ባሳዩበት የባህር ዳሩ ጨዋታ ፍሬው የቡድን ተጫዋችነቱን አሳይቷል። የሀሪስተን ሄሱን አቋቃም በማየት የመታት ቅጣት ምት ለቶማስ ስምረቱ ጎል መንስኤ ከመሄኗ ባለፈ የፍሬው እንቅስቃሴ የቡድኑ የቀኝ ወገን ጠጣር እንዲሆን ዋነኛውን ሚና ተወጥቷል። ጨዋታውን በቀኝ መስመር ቢያሳልፍም የአጥቂ አማካዩን በምርጥ አስራ አንድ ምርጫችን መሐለኛውን ቦታ እንዲይዝ አድርገነዋል።

አቤል ያለው – ቅዱስ ጊዮርጊስ

አቤል ያለው እና የምርጥ 11 ምርጫችን ደንበኝነቱ እንደቀጠለ ነው። ለሦስተኛ ተከታታይ ሳምንት ተመራጭ መሆን የቻለውና ከሌሎች የሊጉ ተጫዋቾት በወጥነት የላቀው የመስመር አጥቂው አቤል ጊዮርጊስ ሰበታን በገጠመበት ጨዋታ አንድ ጎል ሲያስቆጥር አንድ ግብ የሆነ ኳስም አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። ቡድኑ በሁለተኛ አጋማሽ አቻ ከመሆን በፍጥነት ወደ መሪነት እንዲሸጋገር የአቤል ጎል እና በጥሩ ሁኔታ ለጋዲሳ ያቀበለው ኳስ ወሳኝ ነበሩ።

አጥቂዎች

ጌታነህ ከበደ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በሦስተኛው ሳምንት ስብስባችን ውስጥ በተጠባባቂነት ይዘነው የነበረው ጌታነህ ከበደ ጊዮርጊስ ሰበታን በረታበት ጨዋታ የቡድን መሪነቱን ያሳየበትን ጊዜ አሳልፏል። አጥቂው ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር በአንደኛው ግብ ላይ በማቀበል ቀሪው ላይ ደግሞ የማጥቃት ሒደቱን በማስጀመር ተሳትፎ በማድረግ ደምቆ ውሏል።

ሙጂብ ቃሲም – ፋሲል ከነማ

ዐፄዎቹ ወላይታ ድቻን 3-2 በረቱበት ጨዋታ ግዙፉ የፊት አጥቂያቸው ሁለት በጨዋታ አንድ በፍፁም ቅጣት ምት በማስቆጠር ቡድኑን ባለድል አድርጓል። ሙጂብ የዓመቱን የመጀመሪያ ሐት-ትሪክ በመስራት የኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክሩን መምራት የጀመረበትን ሳምንት አሳልፏል።

አሰልጣኝ 

ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ

ደካማ የውድድር ዓመት የጀመረው ሀዋሳ ከተማ በዚህ ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ የአሸናፊነት ግምት ባይቸረውም የ 1-0 ድልን አሳክቷል። አሰልጣኝ ሙሉጌታም ቡድኑ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ የተለየ አቀራረብን ይዞ በመግባት እና ተጫዋቾቹ ሙሉ ጨዋታውን በትኩረት ተጫውተው እንዲጨርሱ በማድረግ ያልተጠበቀውን ውጤት በእጁ አስገብቷል።

ተጠባባቂዎች

ጀማል ጣሰው – ወልቂጤ ከተማ
ቶማስ ስምረቱ – ወልቂጤ ከተማ
ደስታ ዮሐንስ – ሀዋሳ ከተማ
ጋዲሳ መብራቴ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ኤልያስ ማሞ – ድሬዳዋ ከተማ
ብርሀኑ በቀለ – ሀዋሳ ከተማ
ብሩክ በየነ – ሀዋሳ ከተማ


© ሶከር ኢትዮጵያ