የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ልዩ የዝውውር ጊዜ አዘጋጀ

በትግራይ ክልል ክለቦች ለሚገኙ ተጫዋቾች የሚሆን ልዩ የዝውውር ጊዜ ማዘጋጀቱን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

የክለቦቹ ተጫዋቾች ውል ቢኖርባቸውም ወደ ሌሎች ክለቦች እንዲያመሩ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ገሚሶቹ ወደ ልሎች ክለቦች ሲያመሩ አመዛኞቹ ያለ ክለብ መቀመጣቸው የሚታወስ ሲሆን ይህን ተከትሎ ዛሬ ፌዴሬሽኑ በነበረው ስብሰባ ውሳኔ ሊያሳልፍ እንደሚችል መዘገባችን የሚታወስ ነው።

በዚህም መሰረት ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ዙርያ አዲስ ውሳኔ ማሳለፉን በተከታዩ መልኩ አሳውቋል:-

በትግራይ ክልል ባሉ ክለቦች ለመጫወት ውል ፈፅመው የነበሩ ተጫዋቾች በክልሉ በነበረው ሰላም የማስከበር ስራ ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የነበሩ በመሆኑ የዝውውሩን ጊዜ ጠብቀው መዛወር አልቻሉም።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ታህሳስ 22/2013ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ልዩ የዝውውር ጊዜ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ስላመነ፤ በትግራይ ክልል ክለቦች ይጫወቱ የነበረ የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ከታህሳስ 26 ቀን 2013ዓ.ም እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2013ዓ.ም ድረስ ብቻ በማንኛውም ሊግ ውስጥ ተመዝግበው እንዲጫወቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፈቀደላቸው መሆኑ ታውቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ