ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ሀዋሳ ከተማ

የጅማ እና ሀዋሳን ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተነዋል።

የጅማ አባ ጅፋር የውድድር ዓመት የሚቃናበት ጊዜ ቅርብ አይመስልም። ቡድኑ ከድሬዳዋው ጨዋታ በኋላ የተሟላ ልምምድ ሳይሰራ ለነገው ጨዋታ ደርሷል። ዛሬ ከሰዓትም በ10 ተጫዋቾች ብቻ ልምምድ ሰርቷል። በርከት ያሉ ተጫዋቾች ክለቡን ለመክሰስ ዛሬ ወደ ፌዴሬሽን አምርተው እንደነበርም ሰምተናል። በዚህ ዓይነት የቡድን መንፈስ ውስጥ ሆኖ ወደ ሜዳ መግባት እጅግ ከባድ ቢሆንም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጅማ በድሬዳዋው ጨዋታ መጠነኛ መሻሻል አሳይቶ ነበር። በጨዋታው ከባባድ ሙከራዎች ባያደርግም ቢያንስ በንፅፅር የተሻሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችሎ ነበር። ፊት መስመር ላይ ያለው ያለመግባባት ችግር ወደ ግብ የሚቀየሩ ቀላል ዕድሎችን እንደዘበት እንዲያልፉ ሲያደርግም ይታያል። ይህ የቡድኑ ደካማ ጎን በልምምዶች መሻሻል ሊያሳይ ቢችልም የቡድኑ ያልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ መገኘት የነገውን ጨዋታ እንዳያከብድበት ያሰጋዋል።

የሊጉን የመጀመሪያ ድል በከፍተኛ ተጋድሎ ያሳካው ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ከተጋጣሚው በተቃራኒ በጥሩ መንፈስ የነገውን ጨዋታ እየጠበቀ ይገኛል። በእርግጥ ሀዋሳ ነገ ከኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ የተለየ አቀራረብ እንደሚኖረው እሙን ነው። ሙሉ ለሙሉ ጥንቃቄ ላይ አተኩሮ ከነበረው የጨዋታ ዕቅዱ ወደ ራሱ አጨዋወት ተመልሶ በቅብብሎች ላይ የተመሰረተ የማጥቃት ሀሳብን ይዞ ጅማን እንደሚገጥም ይገመታል። በእርግጥ በዚህ አካሄድ ቡድኑ ለፊት አጥቂዎቹ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገር ተስተውሏል። በነገው ጨዋታ ላይ የሚኖረው ጫና ቀለል ሊለው ቢችልም በተጋጣሚዎች የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ የተዋጠባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ። ውጤቱን አጥብቆ ከመፈለግ አንፃር የጅማ አቀራረብ ወደ ኃላ አፈግፍጎ በጥንቃቄ መጫወት ከሆነም ሀዋሳ ለኢትዮጵያ ቡና በሰጠው ፈተና ውስጥ ራሱ አልፎ የግብ ማግቢያ አማራጬችን ፈልጎ የማግኘት ብቃቱ የሚታይ ይሆናል።

በቡድኑ ውስጥ ካለው ችግር ሌላ የመሐል ተከላካዩ ከድር ኸይረዲን ከጉዳት አለማገገም ብቸኛው የጅማ አባ ጅፋር የቡድን ዜና ሲሆን ሀዋሳ ከተማ አጥቂው መስፍን ታፈሰን አሁንም የማይመለስ ሲሆን የዮሀንስ ሴጌቦ መሰለፍም አጥራጣሪ ሆኗል። ከዚህ ውጪ ቅጣቱን የጨረሰው አለልኝ አዘነም ለነገ የሚደርስ አይመስልም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱን ሀዋሳ ሲያሸንፍ አንዱን ጅማ አሸንፎ በቀሪው አቻ ተለያይተዋል። ሀዋሳ 5 ፣ ጅማ 4 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-2-3-1)

ጄኮ ፔንዜ

ወንድምአገኝ ማርቆስ – መላኩ ወልዴ – ውብሸት ዓለማየሁ – ኤልያስ አታሮ

ንጋቱ ገብረስላሴ – ሱራፌል ዐወል

ሳምሶን ቆልቻ – ሙሉቀን ታሪኩ – ሳዲቅ ሴቾ

ብዙዓየሁ እንዳሻው

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ዳንኤል ደርቤ – ምኞት ደበበ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሃንስ

ወንድምአገኝ ኃይሉ – ጋብርኤል አህመድ – ኤፍሬም ዘካሪያስ

ብርሀኑ በቀለ – ብሩክ በየነ – ዮሀንስ ሴጌቦ


© ሶከር ኢትዮጵያ