ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ዕውነታዎች እና ቁጥሮች

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት መርሐ ግብሩን ከሰኞ እስከ ረቡዕ ከአናውኖ የተለያዩ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በዚህ ሳምንት በተከናወኑ ጨዋታዎች ዙርያ ያሉ ቁጥራዊ መረጃዎች እና ዕውነታዎችን እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።

– በአራተኛ ሳምንት በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች 15 ጎሎች ተቆጥረዋል። በአማካይ በጨዋታ 2.5 ጎሎች ያስተናገደው የዚህ ሳምንት መርሐ ግብር ካለፉት ሳምንታት ጨዋታዎች ጋር ሲነፃፀር ከሁለተኛው ሳምንት ጋር በጋራ ዝቅተኛ ጎል የተቆጠረበት ሆኖ ሲመዘገብ ካለፈው ሳምንት በስምንት ያነሰ ጎል አስተናግዷል።

– እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአራት ጎሎች በርካታ ጎሎች ያስቆጠረ ቡድን ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና፣ ባህር ዳር፣ አዳማ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋር ጎል ሳያስቆጥሩ የወጡ ቡድኖች ናቸው።

– በዚህ ሳምንት ከተቆጠሩት 15 ጎሎች መካከል ሦስት ጎሎች (ሙጂብ፣ ጌታነህ፣ ፍፁም) በፍፁም ቅጣት ምት ሲቆጠሩ ሁለት ጎሎች (ቶማስ እና ፀጋዬ) መነሻቸው ከቅጣት ምት የሆኑ ጎሎች አስቆጥረዋል። ቀሪዎቹ አስር ጎሎች ከክፍት ጨዋታ መነሻነት የተገኙ ናቸው።

– ከሳምንቱ 15 ጎሎች መካከል ሁለት (ቶማስ እና ሙጂብ) በግንባር በመግጨት ጎሎች ሲያስቆጥሩ ቀሪዎቹ በእግር ተመተው የተቆጠሩ ናቸው።

– አቤል ያለው ብቸኛው ከሳጥን ውጪ መትቶ ያስቆጠረ ተጫዋች ሲሆን ሌሎች ጎሎች ሳጥን ውስጥ ተመትተው የተቆጠሩ ናቸው።

– 12 ተጫዋቾች በሳምንቱ ጎሎች ላይ ተሳትፎ አድርገዋል። ሙጂብ ቃሲም በሦስት ጎሎች ከፍተኛውን ቁጥር ሲያስመዘግብ ጌታነህ ሁለት አስቆጥሯል። ቀሪዎቹ አስር ተጫዋቾች አንድ ጎል አስቆጥረዋል።

– ስምንት ተጫዋቾች በዚህ ሳምንት 15 ጎሎች ላይ በቀጥታ በማመቻቸት ተሳትፎ አድርገዋል።

– ለጎል በማመቻቸት እና በማስቆጠር ጥሩ ቀን ያሳለፉ ተጫዋቾች ጌታነህ ከበደ (ሁለት ጎል አንድ አሲስት)፣ አቤል (አንድ ጎል አንድ አሲስት)፣ ናንጄቦ (አንድ ጎል አንድ አሲስት) እና አስቻለው (አንድ ጎል አንድ አሲስት) ናቸው።

የመጀመርያ ሁነቶች

– በዚህ ሳምንት አዲስ ከተመዘገቡ የመጀመርያ ሁነቶች አንዱ የመጀመርያው ሐት-ትሪክ ነው። የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም ወላይታ ድቻ ላይ ሦስት ጎሎች አስቆጥሮ የ2013 የመጀመርያ ሐት-ትሪክ ሰሪ ሆኗል።

– በውድድር ዓመቱ ሌላው አዲስ የተመዘገበ አዲስ ሁነት የጅማ አባ ጅፋሩ ተከላካይ ኢዳላማን ናስር ያስመዘገበው ነው። ተጫዋቹ በግብ ጠባቂነት በመጀመርያው ሳምንት መሰለፉ የሚታወስ ሲሆን በዚህ ሳምንት ደግሞ በተከላካይ ስፍራ በመሰለፍ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ተጫዋች ሆኗል።

– እሱባለው ጌታቸው የአዲሱ የውድድር ዓመት አዲስ ሁነት ያስመዘገበ ሌላው ተጫዋች ነው። የሲዳማ ቡናው የመስመር ተጫዋች ከአዳማ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ ላይ በ19ኛው ደቂቃ ላይ በይገዙ ቦጋለ ተቀይሮ ገብቶ በሁለተኛው አጋማሽ 62ኛ ደቂቃ ላይ በተመስገን በጅሮንድ ተቀይሮ ወጥቷል።

ሌሎች ዕውነታዎች

– ሱራፌል ዳኛቸው በአራቱም ሳምንት ጨዋታዎች ቢጫ ካርዶችን የተመለከተ ብቸኛው ተጫዋች ነው።

– ፍሬው ጌታሁን እና ጀማል ጣሰው ሁለት ጨዋታ ጎል ሳይቆጠርባቸው በመውጣት ቀዳሚ ናቸው።

– አቤል ያለው በአራት ኳሶች በርካታ ጎሎችን በማመቻቸት ቀዳሚው ተጫዋች ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ