ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ሰበታ ከተማ

ነገ የሚጀምረው አምስተኛው ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ቀዳሚ ጨዋታን አስመልክተን ይህን ብለናል።

ኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያ ሽንፈቱን ካስተናገደ በኃላ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ ከሰበታ ጋር ይፋለማል። በሀዋሳው ጨዋታ ተቀዛቅዘው የታዩት ቡናዎች ውደ ቀደመው የቡድን መንፈሳቸው ተመልሰው በጥሩ መነሳሳት ወደ ጨዋታው እንደሚገቡ ይጠበቃል። ከሀዋሳ ጋር የማጥቃት ጥይታቸውን ጨርሰው የታዩት ቡናዎች ነገ ከተጋጣሚያቸው የመሳሳይ አቀራረብ ላይገጥማቸው ቢችልም ወደ ግብ መድረሻ መንገዶቻቸውን አበራክተው ካልገቡ ዳግም ችግር ላይ መውደቃቸው የሚቀር አይመስልም። የተቃራኒ ቡድንን የኃላ ክፍል የሚያሸንሩባቸው የመስመር አጥቂዎቻቸው እንቅስቃሴ ሲገደብ እና ከመስመር ተከላካዮቻቸው ጋር ያለው ግንኘነት የተዋጣለት ሳይሆን ሲቀር እነርሱን ነፃ ማድረግ የሚችሉባቸው ዕቅዶች በእጅጉ ያስፈልጓቸዋል። ነገ ግን ከሀዋሳ በተለየ ተጋጣሚያቸው ኳስ መስርተው ከመውጣታቸው በፊት ጫና ሊፈጥርባቸው ስለሚችል ያንን ሰብረው የመውጣት አቅማቸውን የሚፈትሽ ጨዋታ ሊገጥማቸው ይችላል። በዚህ ረገድም ቡድኑን ዋጋ የሚያስከፍሉ የኃላ ክፍል ስህተቶችን ማስተካከል ከቡናማዎቹ የሚጠበቅ ይሆናል። ከዚህ ውጪ አማኑኤል ዮሃንስ በሌለበት እንደነሱ ሁሉ ለኳስ ቁጥጥር ትኩረት የሚሰጠው ሰበታን አማካዮች በተደጋጋሚ ኳስ የማስጣል ፈተናም ይጠብቃቸዋል።

በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ደካማ የማይባል እንቅስቃሴ ያሳዩት ሰበታዎች ከደመወዝ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ለሁለት ቀናት ልምምድ ማቆማቸው ተሰምቷል። ይህም የተጫዋቾችን ተነሳሽነት በከፍተኛ ደረጃ ሊያወርደው ከመቻሉም በላይ ለጨዋታው ያላቸውንም ዝግጁነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ጉዳይ ሆኗል። በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ስንመለከተው ደግሞ ቡድኑ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ደጋግሞ ለመልሶ መጠቃት ሲጋለጥ መታየቱ የፈጣኖቹ የቡና መስመር አጥቂዎች ሰለባ እንዳይሆን የሚያሰጋው ነው። በጊዮርጊሱ ጨዋታ የጥልቅ አማካይነት ሚና ተሰጥቶት የነበረው ፉዓድ ፈረጃ በተወሰነው የጨዋታ ክፍልም ቢሆን ወደ ቀደመው ከቀኝ መስመር ወደሚነሳ የአጥቂ አማካይነት ሚና እንደሚመለስ በሚጠበቅበት የነገው ጨዋታ ቡድኑ የእስራኤል ደርቤ እና ቡልቻ ሹራን ታታሪነት የቡናን የኳስ ፍሰት በራሱ ሜዳ ላይ ለማፈኛነት ይጠቀምበታል ተብሎ ይታሰባል።

በጨዋታው የኢትዮጵያ ቡናው ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ካጋጠመው ጉዳት አገግሞ የሚመለስ ሲሆን በሀዋሳው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው አማኑኤል ዮሐንስ ከነገው ጨዋታ ውጪ እንደሆነ ሰምተናል። ከዚህ በተጨማሪ ሚኪያስ መኮንን እና ኢብራሂም ባዱም ለነገው ጨዋታ አይደርሱም። በሰበታ በኩል ብቸኛ ጉዳት ላይ የነበረው ዱሬሳ ሹቢሳ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ እና ሙሉ ስብስቡ ጤና እንደሆነ ቢሰማም የደመወዝ ጥያቄውን ተከትሎ የቡድኑ ልምምድ ማቆም ትልቁ ዜና ሆኗል። ከዚህ ውጪ የነገው ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላም ተጫዋቾች ወደ ሰበታ ላይመለሱ እንደሚችሉ ሰምተናል።

እርስ በርስ ግንኙነት 

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ስድስት ጊዜ ተገናኝተው ሰበታ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ቡና አንድ አሸንፏል። በሦስቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሰበታ 5፣ ቡና 4 ጎሎች አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ተክለማሪያም ሻንቆ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አሥራት ቱንጆ

ታፈሰ ሰለሞን – ዓለምአንተ ካሳ – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን

አቤል ከበደ – ሀብታሙ ታደሰ – አቡበከር ናስር

ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ፋሲል ገብረሚካኤል

ዓለማየሁ ሙለታ – አንተነህ ተስፋዬ – አዲስ ተስፋዬ – ያሬድ ሀሰን

 ዳዊት እስጢፋኖስ – መስዑድ መሐመድ

ፉዓድ ፈረጃ – ታደለ መንገሻ – ቡልቻ ሹራ

እስራኤል እሸቱ


© ሶከር ኢትዮጵያ