የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 3-2 ሰበታ ከታማ

ከቡና እና ሰበታ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።


አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ጨዋታው

ከእረፍት በፊት የእኛ ቡድን ጥሩ ነበር። ከእረፍት በኋላ ግን ጎሎች አስቆጠርን እንጂ ጨዋታውን መቆጣጠር አልቻልንም። በሁለተኛው አጋማሽ ቡድናችን ጥሩ ነበር ማለት አይቻልም። ያም ሆኖ ከውጤት አንፃር አሸንፈን ወጥተናል።

በሁለተኛ አጋማሽ መስተካከል ስለሚገባቸው ድክመቶች

ልክ ተጋጣሚ እኛ ላይ ሊያደርግ በሚፈልገው መንገድ የሚፈጠሩ ክፍተቶች አሉ። እነዛን ክፍተቶች ነው ያገኘነው። ወደ ጎል ሄደን የተሻሉ የጎል ዕድሎች ማግኘት የቻልነው። ግን እነሱን በቡድን ደረጃ ሰብስበን እዛ ውስጥ ማስገባት አልቻልንም። በእንቅስቃሴ ደረጃ ያ ችግር ነበር በሁለተኛው አጋማሽ። በተለይ ጎሎቹን ካገባን በኃላ ውጤቱን ይዘን ለመውጣት አንዳንዴ ተጫዋቾች የሚሄዱበት መንገድ አለ ፤ ምንአልባት ያም ሊሆን ይችላል።

ጨዋታው በጊዮርጊሱ ጨዋታ ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ

በአንድ በኩል በቂ ዕረፍት አለ ማለት ይቻላል። ሜዳው ጭቃማ ስለሆነ በጣም ነው የሚያደክመው ፤ ብዙ ጉልበት ስለሚጠይቅ። ከሁለት ከሦስት ቀናት በኋላ በመጫወታችን ያንን ድካም የምንቋቃምበትን መንገድ እናመቻቻለን። በተረፈ ግን ለሌላው ቡድን እንደምንመጣው ነው። ምንም የተለየ ነገር የለውም ለጊዮርጊስም የምንጫወተውም።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

ስለ ጨዋታው

ጥሩ ፉክክር የታየበት ጨዋታ ነበር ማለት እችላለሁ። በይበልጥ ግን ተጋጣሚያችን ቡና ከኛ በተሻለ ተንቀሳቅሷል። በተለይ ደግሞ በኳስ ቁጥጥሩ እና ወደ ግብ ቶሎ ቶሎ በመድረስ ከኛ የተሻሉ ነበሩ። ይህንን በሁለተኛ አጋማሽ ለማስተካከል ሞክረናል። ግን አሁንም በተከላካይ ክፍሉ ላይ ባሉ ጥቃቅን ስህተቶች ጎሎች ተቆጥረውብናል። በተረፈ ጥሩ ጨዋታ ነበር ማለት እችላለሁ።

የአዲስ አበባ ቆይታን በድል ስለማጠቀቅ

አዲስ አበባ ላይ የሚቀረን አንድ ጨዋታ ነው። ማክሰኞ የምናደርገውን ይህን ጨዋታ በድል አጠናቀን በጥሩ የሥነ ልቦና ዝግጅት ወደ ጅማ ለመንቀሳቀስ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ