ሪፖርት | ቡና ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ድል አሳክቷል

ረፋድ ላይ በተደረገው የአምስተኛ ሳምንት መክፈቻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ሰበታ ከታማን 3-2 አሸንፏል።

ለኢትዮጵያ ቡና ዊልያም ሰለሞን እና ሬድዋን ናስር ጉዳት ላይ በሚገኘው አምበሉ አማኑኤል ዮሐንስ እና ዓለምአንተ ካሳ ቦታ ወደ ሜዳ ሲገቡ በሰበታ ከተማ በኩል በተደርገው ለውጥ ደግሞ በታደለ መንገሻ ምትክ ፍፁም ገብረማርያም ጨዋታውን ጀምሯል።

የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለማግኘት ብርቱ ፉክክር የተደረገበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ግቦችን ሲያስተናግድ ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችንም አሳይቶናል። በተለይ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ ኳሱን መያዝ የቻሉት ቡናዎች አብዛኛውን ደቂቃ በሰበታ ሜዳ ላይ አሳልፈዋል። በአጫጭር ቅብብሎቻቸው ሳጥን ውስጥ የተገኙባቸው አጋጣሚዎችም በቁጥር ጥቂት አልነበሩም።

የተጋጣሚያቸው አጨዋወት አልፎ አልፎ ወደ ቀጥተኛነት እንዲያደሉ ያስገደዳቸው የሚመስሉት ሰበታዎች በበኩላቸው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ ሙከራዎችን አድርገዋል። ፍፁም ገብረማርያም ከእስራኤል ተቀብሎ ከሳጥን ውስጥ የሞከረው እና ከፉዓድ ተሻግሮለት በግንባሮ አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ የተባለበት በዚህ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። 14ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ከግብ ክልሉ በረጅሙ ያራቀውን ኳስ ተቆጣጥሮ በጥሩ ሁኔታ ይዞ በመግባት እስራኤል እሸቱ ሰበታን ቀዳሚ አድርጓል።

በኳስ ቁጥጥር የበላይነቱ የገፉበት ቡናዎች የተጋጣሚያቸውን አማካዮች ኳስ በማስጣል በተደጋጋሚ ግብ አፋፍ ላይ እየደረሱ 25ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ከታፈሰ ሰለሞን የተነሳውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ በግራ መስመር ይዞ በመግባት ሞክሮት ፋሲል ገብረሚካኤል ቢመልስበትም በድጋሚ አግኝቶት ወደ አቡበከር ናስር አሻግሮት አቡበከር ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ከግቡ በኋላም በተመሳሳይ አኳኋን የቀጠሉት ቡናዎች አደገኛ ሙከራ ማድረግ ይሳናቸው እንጂ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሰንዝረዋል። ሆኖም ከባዱ ሙከራ ታፈሰ ሰለሞን 41ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥኑ መግቢያ አካባቢ መትቶት ፋሲል ያወጣው ነው። በሌላው የግቡ ወገን ቡድኖቹ ወደ ዕረፍት ሊያመሩ ሲሉ በጥሩ የማጥቃት ሽግግር እስራኤል ከግብ ጠባቂ ጋር ያገናኘውን ኳስ አግኝቶ ከግራ መስመር ይዞ ቢገባም በማይታመን መልኩ ወደ ላይ ልኮታል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ሰበታዎች የተሻለ ተነቃቅተው ሲጀምሩ ወደ ቡና የግብ ክልል ተጠግተው ታይተዋል። ሆኖም በሙከራ እና በግቦች ቡናዎች የበላይነቱን ወስደዋል። በመጀመሪያ በፈጠሩት ለግብ የቀረበ ዕድል 50ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ከበደ በቀኝ ይዞ የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ልኮለት አቡበከር ለጥቂት ሳያገኘው ቀርቷል። ከአራት ደቂቃዎች በኃላም ሀብታሙ ታደሰ ከግራ መስመር የማዕዘን መምቻ አካባቢ አሥራት ቱንጆ የወረወረውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ አክርሮ መትቶ በማራኪ ሁኔታ ወደ ግብነት ተቀይሯል። በመቀጠል 65ኛው ደቂቃ ላይ መሀል ለመሀል ሰብረው የገቡት ቡናዎች ታፈሰ ሰለሞን ለአቡበከር ባመቻቸለት እና አምበሉ በቀላሉ ባስቆጠረው ኳስ መሪነታቸውን አስፍተዋል።

ከግቦቹ ባሻገር ባለቀላቸው የግብ ዕድሎች በተደጋጋሚ ከግብ አፋፍ የደረሱት ቡናዎች ልዩነቱን ማስፋት የሚችሉባቸውን ዕድሎች አምክነዋል። የሰበታው ግብ ጠባቂ ፋሲል ገብረሚካኤል ከአቡበከር፣ ታፈሰ እና ሀብታሙ ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘባቸውን አጋጣሚዎች አምክኖ በድኑን በሰፊ ጎል ከመመራት ታድጓል።


ከኃላ ብዙ ክፍተት ትተው ለተደጋጋሚ ሙከራ ተጋልጠው ግብ ፍለጋ ሲጥሩ የነበሩት ሰበታዎች 76ኛው ደቂቃ ላይ ሆኖላቸዋል። ቢያድግልኝ ኤልያስ በረጅሙ ወደ ጎል የጣለውን ኳስ ተክለማርያም በአግባቡ ባለመቆጣጠሩ ተቀይሮ በገባ 30 ሰኮንድ ብቻ ቃልኪዳን ዘላለም የመጀመርያ ንክኪው ወደ ጎልነት ተቀይሮታል። ያም ቢሆን የሰበታዎች ጥረት ከፉዓድ ፈረጃ የ85ኛ ደቂቃ የርቀት ሙከራ ሌላ ተጨማሪ ዕድል ሳይፈጥርላቸው ቡናዎች የመጨረሻ ደቂቃ ጫናዎችን ተቋቁመው በ 3-2 ውጤት ጨዋታውን ፈፅመዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ