ኢትዮጵያዊው አጥቂ ጌታነህ ከበደ ዛሬ ቀትር ላይ በተደረገ የአብሳ ፕሪምየርሺፕ ጨዋታ ለፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ግቡን ቺፓ ዩናይትድ ላይ አስቆጥሯል፡፡ ጨዋታውን ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ትግል እያደረገ የሚገኘው የፕሪቶሪያው ክለብ 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል፡፡
ለፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያውን ግብ ናሚቢያዊው ዊለም ሞዲሃንጋ በግንባር ገጭቶ በ35ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ታቦ ሞሳዲ ሁለተኛውን ግብ በ61ኛው ደቂቃ አክሏል፡፡ የዋሊያዎቹ የፊት መስመር ተሰላፊ ጌታነህ በ70ኛው ደቂቃ የቺፖ ግብ ጠባቂ ዳንኤል አክፒ የተፋውን ኳስ በመጠቀም የፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲን ማሸነፍ ያረጋገጠች ግብ አስቆጥሯል፡፡
ጌታነህ በውድድር ዘመኑ ለክለቡ ለመጀመሪያ ግዜ ያስቆጠራት ግብ ስትሆን ከዚህ ቀደም ሁለት ግብ የሆኑ ኳሶችን ማቀበል ችሏል፡፡
ለአማተክስ ይህ በውድድር ዘመኑ ያስመዘገቡት አራተኛ ድላቸው ሲሆን የቀድሞው የባፋና ባፋና ኮከብ ሾን ባርትሌት በክለቡ ከተሾመ በኃላ ያሳካው የመጀመሪያ ድል ሆኖለታል፡፡
ፕሪቶርያ ዩኒቨርሲቲዎች አሁንም በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ድሉን ተከትሎ 14ኛ ደረጃ ላይ ካለው ጆሞ ኮስሞስ በአንድ ነጥብ ብቻ መለያየት ችለዋል፡፡ በሊጉ ግርጌ ከፕሪቶሪያው ክለብ አራት ነጥብ የሚያንሰው ማርቲዝበርግ ዩናይትድ ተቀምጧል፡፡