“እንዲህ ያለ ነገር በእግርኳስ ያጋጥማል” – ምኞት ደበበ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር ከሀዋሳ ከተማ አንድ አቻ ሲለያዩ በሁለቱም በኩል ጎሎችን ያስቆጠረው ምኞት ደበበ ነበር። በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ሀዘን እና ደስታ የፈጠሩ ክስተቶችን ካስተናገደው ምኞት ጋር ቆይታ አድርገናል

በእግርኳስ ከሚከሰቱ አስገራሚ ገጠመኞች መካከል አንዱ የሆነው ክስተት ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተከስቷል። የጅማ አባ ጅፋሩ ኤልያስ አታሮ ከግራ መስመር ያሻማውን የቅጣት ምት የሀዋሳው ምኞት ደበበ ለማውጣት ሲሞክር እግሩን ጨርፎ ጅማን ቀዳሚ ያደረገች ጎል በራሱ ላይ አስቆጥሯል። ሆኖም ሀዋሳዎች ባለቀ ሰዓት ተሸናፊ ከመሆን የታደጋቸውንም ጎል ያገኙት በአስገራሚ ሁኔታ ከምኞት ደበበ ሆኗል። ይህን ገጠመኝ አስመልክቶ ከጉዙፉ ተከላካይ ምኞት ጋር በዕለቱ ስለተፈጠረው ነገር እንዲነግረን ጠይቀነው ነበር። እርሱም በዕለቱ የተፈጠረውን ነገር በዚህ መልኩ አጋርቶናል።

” የዛሬው ጨዋታ እንደጠበቅነው አይደለም ያገኘነው። ለእኛ ጥሩ ጨዋታ አልነበረም። ለማሸነፍ ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። ሆኖም ሜዳ ላይ ስንገባ የተፈጠረብን ነገር ሌላ ነው የሆነብን። በዚህም ትንሽ ግር ብሎን ነበር። እንዳውም መጨረሻ ላይ ባለቀ ሰዓት ጭራሽ ልንሸነፍ ሁሉ ነበር።

“ቅጣት ምት ኳሱ ሲመታ ለማውጣት ነበር ሀሳቤ፤ እንዳጋጣሚ ሆኖ መጋጫዬን አላሰርኩትም ነበር። ኳሱ መጋጫዬን ጨርፎ ተቆርጦ ጎሉ ሊቆጠር ችሏል። ጎሉ ሲቆጠርብን በጣም ነበር ያዘንኩት። ማሸነፍ እያለብን እኛ ላይ ጎል ሲቆጠር እና እኔ ራሴ ላይ ጎል ሳስቆጥር በጣም ነው የተሰማኝ። ሆኖም ዳኛው የጭማሪ ደቂቃ ካሳየ በኃላ ቡድናችንን ከሽንፈት የታደገ ጎል ራሴ መልሼ በማግባቴ ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ። ያው እንዲህ ያለ ነገር በእግርኳስ የሚያጋጥም ገጠመኝ ነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ