የነገውን የመጀመሪያ ጨዋታ በዳሳሳችን ተመልክተነዋል።
ወላይታ ድቻ ብርቱ ፉክክር ካደረገበት የፋሲሉ ጨዋታ መልስ ወደ ድል ለመመለስ ድሬዳዋን ይፋለማል። በፋሲሉ ጨዋታ አማኑኤል ተሾመ እና በረከት ወልዴን በማጣመር መሀል ሜዳ ላይ ጥንቃቄ ተኮር አቀራረብ የነበራቸው ድቻዎች በነገው ጨዋታ አራት የማጥቃት ባህሪ ያለቸው አማካዮችን ወደሚጠቀሙበት የጨዋታ ዕቅድ እንደሚመለሱ ይታሰባል። በማጥቃቱ ረገድ እንደከዚህ ቀደሙ የቡድኑ ዋነኛ የጨዋታ አቀጣጣይ የሆነው እንድሪስ ሰዒድን በነፃነት የመጠቀም ችግር የተስተዋለበት ድቻ ነገ ከተጨዋቹ የመጨረሻ ኳሶች ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕቅድ እንደሚኖረው ይገመታል። ቡድኑን ዋጋ የሚያስከፍሉት የኃላ መስመር መዘናጋቶችም በነገው ጨዋታ መቀረፍ የሚገባቸው ሲሆን ግብ ከማስቆጠር ባለፈ በተከላካይ መስመር ፊት በእንቅስቃሴ መሻሻል ያሳየው የስንታየሁ መንግስቱም የተሻለ አስተዋፅዖ ያስፈልገዋል። ከዚህ ውጪ ድቻዎች ከመስመር የሚነሱት የማጥቃት አማካዮቻቸው እንቅስቃሴ ከኋለኞቹ መስመር ተከላካዮች ጋር የሚኖረው መናበብ የተጋጣሚያቸውን የግራ እና ቀኝ የሜዳ ክፍል ለመስበር በሚጠብቀው ፉክክርም የሚፈተን ይሆናል።
ብርቱካናማዎቹ በጅማ ላይ ያሳኩትን የመጀመሪያ የሊግ ድላቸውን ለመድገም ወደ ሜዳ ይገባሉ። በዚያ ጨዋታ ላይ ጎልተው የወጡ ጥንካሬዎቻቸውም ለነገው ግጥሚያ ወሳኝ እንደሚሆኑ እሙን ነው። በተለይም በድኑ በፈጠራው ረገድ በኤልያስ ማሞ ላይ ተመርኩዞ የነበረበት ሒደት በአስቻለው ግርማ መታገዝ መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ነው። አስቻለው ከጁኒያስ ናንጁቡ ጋር ያሳየው መናበብ ከጅማ ጋር ሁለት ግቦችን እንዳስገኘ ሁሉ ነገም ተመሳሳይ ግልጋሎት ይጠበቅበታል። በዚህም አስቻለው ከመስመር ወደ መሀል እያጠበበ በሚገባባቸው እንቅስቃሴዎች በተለይም ከበረከት ወልዴ ጋር የሚገናኝባቸው ቅፅበቶች እጅግ ወሳኝ ይሆናሉ። የድቻ የኋላ መስመር ባለፈው ጨዋታ ተዳክሞ ከመታየቱ አንፃርም የጁኒያስ ናጁቡ እና ኢታሙና ኬይሙኒ ፍጥነት ከአማካይ ክፍሉ ከሚነሱት ኳሶች ጋር ከተጣጣመ ከተከላካይ ጀርባ በመግባት ጥቃት የማድረስ ዕድሉ ሰፊ ይሆናል። የድሬ መስመር ተከላካዮች የተዳከመ የማጥቃት ሂደት ግን ለተጋጣሚ ከሁለቱ ክንፎች ለሚነሱ አማካዮች ወደ ፊት የመግፋት ነፃነት እንዳይሰጥ የሚያሰጋው ነጥብ ነው።
የወላይታ ድቻው ፊናስ ተመስገን ዳግም ጉዳቱ አገርሽቶበት ዕረፍት ላይ ሲሆን በጅማው ጨዋታ በህመም ያልነበረው ኤልያስ አህመድ ልምምድ እየሰራ ቢሆንም የመሰለፉ ነገር እርግጥ አልሆነም። በተመሳሳይ የብሽሽት ጉዳት የገጠመው አናጋው ባደገም ወደ ልምምድ መመለሱን ሰምተናል። በድሬዳዋ ከተማ በኩል በሁለት ቢጫ ምክንያት የጅማው ጨዋታ ያመለጣቸው ዳንኤል ደምሴ እና በረከት ሳሙኤል ወደ ሜዳ የሚመለሱ ሲሆን ባለፈው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው ፍቃዱ ደነቀ እና ከሜዳ ርቆ የቆየው ሄኖክ ኢሳይያስ በነገወሰ ጨዋታ የማይኖሩ ይሆናል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ8 ጊዜያት ተገናኝተዋል። በዚህም ድሬዳዋ አራት ጊዜ አሸንፎ በአራቱ አቻ ሲለያዩ እስካሁን ወላይታ ድቻ ድል ማስመዝገብ አልቻለም። ድሬ 8፤ ድቻ 3 ጎሎችንም አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)
ሰዒድ ሀብታሙ
ፀጋዬ አበራ – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – መሳይ አገኘሁ
በረከት ወልዴ
ፀጋዬ ብርሀኑ – ኤልያስ አህመድ – እንድሪስ ሰዒድ – ቸርነት ጉግሳ
ስንታየሁ መንግሥቱ
ድሬዳዋ ከተማ (4-1-3-2)
ፍሬው ጌታሁን
ዘነበ ከበደ – ያሬድ ዘድነህ – በረከት ሳሙኤል –ምንያምር ጴጥሮስ
ዳንኤል ደምሴ
ሱራፌል ጌታቸው – ኤልያስ ማሞ – አስቻለው ግርማ
ጁኒያስ ናንጂቡ – ኢታሙና ኬይሙኒ
© ሶከር ኢትዮጵያ