ሦስቱ ወንድማማቾችን ያገናኘው የሰበታ እና ቡና ጨዋታ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት መክፈቻ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከሰበታ ከተማ ጋር ያገናኘው ጨዋታ ሦስቱን ወንድማማቾችን በተለያዩ ክለቦች አገናኝቷል።

አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ሾላ “ጉቶ ሜዳ” አካባቢ ከአባታቸው ናስር ተገኝተዋል። ታላቅ ወንድማቸው ጅብሪል ናስር ይባላል። በተለያዩ የከፍተኛ ሊግ ቡድኖች የአማካይ ስፍራ ተጫዋች በመሆን የእግርኳስ ህይወቱን እየመራ ቢቆይም በተፈለገው መጠን እንደነበረው አቅም እንደ ታናናሽ ወንድሞቹ እድገቱን መጠበቅ ሳይችል ቀርቷል። በአሁኑ ወቅትም ለሰበታ ከተማ እየተጫወተ ይገኛል። አቡበከር ናስር ሁሉም እንደሚያቀው በተስፋ ፍሬ፣ ሐረር ቢራ እና በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ቡና እየተጫወተ የሚገኝ ምርጥ አጥቂ ነው። ታናሹ ሬድዋን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ተጫውቶ በማሳለፍ ከታላቅ ወንድሙ አቡበከር ጋር በኢትዮጵያ ቡና እየተጫወተ ይገኛል። ሦስቱ የአቶ ናስር ልጆች ከአንድ ቤተሰብ ተገኝተው በእግርኳሱ የራሳቸውን ስም እየተከሉ ይገኛል። በዛሬ ዕለት በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ሲካሄድ ሦስቱን ወንድማማቾች ማገናኘቱን ተከትሎ (ምንም እንኳ ጂብሪል ሜዳ ገብቶ መጫወት ባይችልም) ለተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ጅብሪል ናስር

ከአንድ ቤተሰብ ሦስት ተጫዋቾች መገኘት ስሜቱ እንዴት ይገለፃል ?

በጣም ደስ የሚል ስሜት አለው። የቤቱ ታላቅ እኔ ነኝ። ከቤታችን አጠገብ እንደሚታወቀው ሜዳ አለ። ቤተሰብም እግርኳስን እንድንጫወት ከፍተኛ ፍላጎት ያለው በመሆኑ እዚህ ደርሰናል። ይህም የሆነው የእግርኳስ ተስዕጦ ስላለን ይሆናል።

እንደ ወንድሞችህ የእግርኳስ እድገትህ ለምን ከፍ አላለም ?

ያው በደደቢት፣ ጅማ እና ሻሸመኔ ተጫውቼ አሳልፌያለው። ሆኖም ለተወሰኑ ጊዜያት ጉዳት እንዳሰብኩት እንድጫወት አላደረገኝም። በዚህ ምክንያት እድገቴ ትንሽ ቆም ብሎ ነበር። አሁን ሰበታ መጥቻለው። ከፈጣሪ ጋር ራሴን ለማሳየት እሞክራለው።

ወደፊት ከወንድሞችህ ጋር አብሮ በአንድ ክለብ የመጫወት ሀሳቡ አለህ ?

አዎ የማይቀር ነው። ሦስታችን በአንድ ክለብ በእርግጠኝነት ወደ ፊት እንጫወታለን።

እናንተ ስትጫወቱ ቤት ውስጥ ቤተሰቦቻችሁ ጋር ያለው ስሜት እንዴት ነው ?

በጣም ደስተኛ ናቸው። በተለይ እናታችን እግርኳስ በጣም ነው የምትወደው። ከእኛ በላይ እግርኳሱን በጣም ነው የምትከታተለው። ተጫውተን አሸንፈን ስንመጣ በጣም ነው የምትደሰተው።

አቡበከርን እንዴት ትገልፀዋለህ ?

አቡኪ በሀገራችን ካሉ ምርጡ ተጫዋች መካከል አንዱ ነው። በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ። በጣም ልባም፣ ሜዳ ውስጥ ምንም የማይፈራ፣ ጎበዝ፣ ከዕድሜው በላይ የሚያስብ ተጫዋች ነው። እዚህ ደረጃ በመድረሱም በጣም ነው ያስደሰተኝ።

ሬድዋን ናስር

ከወንድምህ ጋር በአንድ ክለብ የመጫወት ስሜቱ እንዴት ነው?

ከወንድሜ ጋር በአንድ ማልያ አብሮ መጫወት በጣም ነው የሚያስደስተው። በተለይ በምወደው በኢትዮጵያ ቡና ማልያ አብረን መጫወታችን ስሜቱ ከፍ ያለ ነው። እንዲህ ያለ እድል ከስንት አንዴ የሚገኝ ነው። ከወንድሜ ጋር አብሬ በመጫወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ወንድምህ አጥቂ ነው። አንተ እንዴት የተከላካይ አማካይ ሆንክ?

ሦስታችንም መሐል ላይ ነበር የምንጫወተው። ሆኖም አሰልጣኞቼ የኔ አጨዋወት ወደ ተከላካይ አማካይነት ስለሚያደላ ወደ ኃላ ለመጫወት አለብህ ስላሉኝ ነው ወደ ኃላ የምጫወተው።

ከአንተ እና ከአቡበከር ማን ይበልጣል ?

(እየሳቀ) ኧረ አቡበከር ይበልጣል፤ ይህ ግልፅ ነው። እርሱ አሳምሮ ይበልጠኛል። እርሱ ከእኔ ብዙ የተሻለ ነገር አለው።

ከአቡበከር ምኑን ታደንቅለታለህ ?

ትልቁ ነገሩ ቦታ አያያዙ ነው፤ በጣም ነው የማደንቅለት። ከዚህ ውጭ የጎል አጨራረስ ብቃቱ እንዲሁም እርጋታው በጣም አደንቅለታለው። ሌላው በአዕምሮው አስቦ የሚጫወት መሆኑን በጣም ነው የምወድለት።

በአንድ ክለብ ተጫውታችኋል። በብሔራዊ ቡድንም እንጠብቅ ?

ከትንሽ ጊዜ በኋላ በብሔራዊ ቡድን ጠብቁን አብረን እንጫወታለን። አቡኪ ያው በዋናው ብሔራዊ ቡድን እየተጫወተ ነው። እኔም በታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ተጫውቼ አልፌያለው። በቅርቡ ወደ ዋናው ብሔራዊ ቡድን አብሬው እጫወታለው ብዬ አስባለው።

አቡበከር ናስር

ያው ከወንድም ጋር አብሮ መጫወት በጣም ያስደስታል። ምክንያቱም አንድ ስጋ ሆነህ ቡናን በሚያክል ትልቅ ክለብ መጫወት በጣም ትልቅ አጋጣሚ ነው።

እንደ ወንድምህ አማካይ ሆነህ መጫወትን ለምን አልቀጠልክም ?

ያው አስቀድሜ አማካይ ነበርኩኝ። ሆኖም አሰልጣኞች ያለኝን አቅም ተረድተው ወደፊት ሄጄ እንድጫወት አድርገውኛል።

ከሬድዋን እና ከአንተ ማን ይበልጣል ?

ያው እርሱ የራሱ አቅም አለው። እኔ እርሱ ቦታ ሄጄ ለመጫወት ባስብ በጣም እቸገራለው። እርሱም እኔ ቦታ ለመጫወት ቢያስብ ሊከብደው ይችላል። ስለዚህ ብዙም የአቅም ልዩነት የለንም።

ከሬድዋን የምታደንቅለት ምንድነው ?

እግሩ የገቡ ኳሶችን ለቡድን አጋሩ በትክክል ነው የሚያቀብለው። ከዚህ በተጨማሪ የአየር ላይ ኳስ ሲያቀብል በጣም እወድለታለው። እንደዚሁ ሜዳ ላይ ምንም ነገር ቢፈጠር አይረበሽም ተረጋግቶ የሚጫወት መሆኑ በጣም አደንቅለታለው።

እናንተ ስትጫወቱ የቤተሰብ ስሜት እንዴት ነው ?

በእኛ ቤተሶቻችን በጣም ነው የሚደሰቱት። እንኳን ቤተሰብ ከሩቅ ያለ ሰው በእኛ እንደሚደሰት አስባለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ