ቅድመ ዳሰሳ | ባህርዳር ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

ተጠባቂውን ጨዋታ የተመለከትንበት ዳሰሳችንን እነሆ ብለናል።

ጠንካራ ስብስብ እና ጥሩ መዋቅር ካላቸው ቡድኖች ውስጥ የሚጠቀሱት ባህርዳር እና ፋሲል የሚገናኙበት ጨዋታ ከሳምንቱ መርሐ ግብሮች ውስጥ ከፍ ያለ ግምት የተሰጠው ግጥሚያ ሆኗል።

በእስካሁኑ ጨዋታዎቹ ሁለት ድል እና ሁለት ሽንፈት የገጠመው ባህር ዳር ከተማ ሞቅ ቀዝቀዝ የሚለው አካሄዱ ለነገው ጨዋታ የሚመጣበትን አኳኋን አጠራጣሪ ያደርገዋል። በእርግጥ በሀዲያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ጠንካራ የመከላከል አቅም ተፈትኖ ሲዳማ እና አዳማ ላይ መበርታቱ በማጥቃት ሀሳብ ወደ ሜዳ ከሚገቡ ቡድኖች ጋር የተሻለ አቋም እንደሚያሳይ ፍንጭ ይሰጣል። በመሆኑም በነገው የፋስል ጨዋታ የተነቃቃውን ባህርዳርን የምናይበት ዕድል ሰፊ ነው። በዚህም የማጥቃት ተሳትፎ የሚኖራቸው የመስመር ተከላካዮች እና ከተጋጣሚ ተከላካይ ክፍል ፊት ያለውን ቦታ ለመጠቀም የሚለፉ የማጥቃት አማካዮች እንቅስቃሴን ከቡድኑ ልንመለከት እንችላለን።

በዋነኝነት የባህር ዳር የማጥቃት መሰረት የሆነው ፍፁም ዓለሙ ከፋሲሉ ይሁን እንዳሻው ጋር የሚኖረው ፍልሚያ እጅግ ተጠባቂ ይሆናል። ቀዝቅዝ ብሎ የታየው የባዬ ገዛኸኝ ከአማካዮች ጋር የመቀናጀት ሂደትም እንደነገው ባለ ጨዋታ ላይ ከተመለሰ ለአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድን ተጨማሪ ጉልበት ይሆነዋል። ከሁሉም በላይ ባህርዳር የሳምሶን ጥላሁን በቡድኑ አለመኖር የተረጋጋ የተከላካይ ሽፋን እና ጥቃትን የማስጀመር ሂደት አሳጥቶት መታየቱ በነገው ጨዋታ የሚጠበቀው ፈተና ነው። እንዳለፈው ጨዋታ የሀሪሰን ሄሱ ዓይነት ስህተት ከተሰራም በሙጂብ ቃሲም የሚመራው የፋሲል የፊት መስመር ይምረዋል ተብሎ አይታሰብም።

ለሦስተኛ ተከታታይ ድል ወደ ሜዳ የሚገቡት ፋሲሎች የመጨረሻው ጨዋታቸውን በቀላሉ አልነበረም ያሸነፉት። እስካሁን ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች በሦስቱ ግብ ያስተናገዱት ፋሲሎች የኋላ ክፍላቸውን ነገር ነገ አስተካክሎ መቅረብ የግድ ይላቸዋል። ያ ካልሆነ ግን እንደ ባህርዳር ጥሩ የመጨረስ አቅም ካለው ቡድን ጋር እንደ ድቻው ጨዋታ ቀድሞ ያገኙትን የመምራት ዕድል አሰልፎ ከመስጠት ባለፈ ቀድሞ ግብ የማስተናገድ ዕጣም ሊገጥማቸው ይችላል። ይህን መሰል ሁኔታ ሲፈጠር እና ቡድኑ ሙሉ አቅሙን ማጥቃት ላይ ሲያደርግ ምን ያህል ሊቸገር እንደሙችል ደግሞ የቡናው ጨዋታ አሳይቶን አልፏል።

በሌላ በኩል የሙጂብ ቃሲም ከሦስት ጎሎች በኋላ መመለስ የአጥቂውን በራስ መተማመን ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል። በመናፍ ዐወል እና ሰለሞን ወዴሳ ጥምረት ማሀል ሙጂብ የሚያሳልፈው ቀንም ተጠባቂ ይሆናል። ሌላው የፋሲል ቁልፍ ተጫዋች ሱራፌል ዳኛቸው አምስተኛ የቢጫ ካርድ ሳያስተናግድ መጨረስ ባለበት ጨዋታ ከእነ ፍቅረየሱስ ዓለሙ ጋር የሚኖረው ፍልሚያ አጓጊ ይሆናል። የሽመክት ጉግሳ በታታሪነት የተሞላ እንቅስቃሴም የማጥቃት ሂደት ላይ ተሳተፊ ከሆኑት የባህር ዳር መስመር ተከላካዮች እና መሀል ተከላካዮች መካከል የሚኖረው እንቅስቃሴ ለፋሲል ውጤታማነት ቁልፍ እንደሆነ ይታመናል።

በጨዋታው የባህር ዳሮቹ ሳምሶን ጥላሁን እና አቤል ውዱ ከነበረባቸው ጉዳት እያገገሙ ቢሆንም ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ሲሆን በወልቂጤው ጨዋታ ተጎድቶ የወጣው ዜናው ፈረደም እንዲሁ ቡድኑን አያገለግልም። በፋሲል ከነማ በኩል የመስመር ተከላካዩ ሰዒድ ሁሴን አሁንም ጉዳት ላይ ሲሆን ከጉዳቱ እንዳገገመ የተሰማው ሀብታሙ ተከስተ የጨዋታ ዝግጁነትም እርግጥ አልሆነም። በሌላ በኩል ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔም በሀዘን ምክንያት በስብስቡ ውስጥ የማይገኝ መሆኑን ሰምተናል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– የዓምናውን (የተሰረዘ) የውድድር ዘመን ሳይጨምር ቡድኖቹ 2011 ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ሲገናኙ በመጀመርያው ዙር ባህር ዳር ላይ ያለ ጎል አቻ ተለያይተው ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ 4-0 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ሀሪሰን ሄሱ

ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – በረከት ጥጋቡ

ምንይሉ ወንድሙ – ፍፁም ዓለሙ – ግርማ ዲሳሳ

ባዬ ገዛኸኝ

ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)

ሚኬል ሳማኬ

እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ይሁን እንዳሻው – ሳሙኤል ዮሐንስ

በረከት ደስታ – ሱራፌል ዳኛቸው – ሽመክት ጉግሳ

ሙጂብ ቃሲም


© ሶከር ኢትዮጵያ