ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ የዓመቱ ሁለተኛ ድሉን አሳክቷል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ ረፋድ ላይ ወላይታ ድቻን የገጠመው ድሬዳዋ ከተማ 2-1 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድል አስመዝግቧል።

ወላይታ ድቻዎች በፋሲል ከነማ ከተረታው ስብስብ ውስጥ ግብጠባቂ ቦታ ላይ መክብብ ደገፉን በሰዒድ ሀብታሙ ሲተኩ ከጉዳት እና ቅጣት የተመለሱት አናጋው ባደግ እና እዮብ በቀታም በአንተነህ ጉግሳ እና ፀጋዬ አበራ ቦታ በቀዳሚነት ጨዋታውን ጀምረዋል።

በአንፃሩ ጅማ አባ ጅፋር ከረታው የድሬዳዋ ከተማ ስብስብ አምስት ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም ፍቃዱ ደነቀ፣ ዘነበ ከበደ፣ አስጨናቂ ሉቃስ፣ ጁኒያስ ናጂቡ ኢታሙና ኬይሙኒን አስወጥተው በምትካቸው በረከት ሳሙኤል ፣ ዳንኤል ደምሴ ፣ ኩዌኩ አንዶህ ፣ ሙኸዲን ሙሳ እና ሪችሞን ኦዶንጎን በመተካት ጨዋታውን ጀምረዋል።

ተመጣጣኝ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ እንቅስቃሴ ሁለቱም ቡድኖች ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች የግብ እድሎችን በተለይ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ለመፍጠር ሞክረዋል።

በ9ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ ከቅጣት ምት የግቡ አግዳሚ በመለሰበት ኳስ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በ13ኛው ደቂቃ በረከት ሳሙኤል የመታው የቅጣት ምት ኳስ በድቻ ተጫዋቾች ሲመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው አስቻለው ኳስ ከመረብ በማዋሃድ ድሬዳዋ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው ወዲህ ፊት ላይ ለብቻው ተነጥሎ የነበረውን አጥቂያቸውን ወደ ኃላ በመመለስ የእንቅስቃሴዎች አካል ለማድረግ ያደረጉት ጥረት ፍሬ አፍርቶ በ33ኛው ደቂቃ ስንታየሁ መንግስቱ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ፀጋዬ ብርሃኑ ከቀኝ የሳጥን ክፍል ሰብሮ በመግባት በጥሩ አጨራረስ ለድቻ የአቻነቷን ግብ አስቀርተዋል።

ነገርግን ጨዋታው በአቻነት መዝለቅ የቻለው ለሶስት ደቂቃዎች ያክል ነበር። በ36ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ በተከላካዮች መሀል ያሿለከለትን ኳስ ተጠቅሞ ሙህዲን ሙሳ የድቻው ግብ ጠባቂ መክብብ ደገፉን አልፎ በተረጋጋ አጨራረስ ባስቆጠራት ግብ የመጀመሪያው አጋማሽ በድሬዳዋ ከተማዎች መሪነት ሊጠናቀቅ ችሏል።

ወላይታ ድቻዎች ከፍ ያለ የማሸነፍ ፍላጎት አሳይተው በጀመሩት የሁለቱ ቡድኖች ሁለተኛ አጋማሽ ወላይታ ድቻ የተሻለ የጨዋታ ቁጥጥር ቢኖራቸውም የድሬዳዋ ከተማን የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ግን እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። አዩብ በቀታ በ68ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ሞክሮ ፍሬው ጌታሁን ካዳነው እና በ75ኛው ደቂቃ እዮብ ዓለማየሁ ካመከነው ነፃ የግንባር ኳስ ውጭ ተጠቃሽ የግብ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ በመልሶ ማጥቃት በሱራፌል ጌታቸውና ሙህዲን ሙሳ እድሎችን ቢያገኙም የድቻው ግብ ጠባቂ መክብብ ደገፉ የሚቀመስ አልሆነም።

ጨዋታውም ተጨማሪ ግቦችን ሳያስተናግድ በድሬዳዋ ከተማ የ2-1 የበላይነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ