በድሬዳዋ ከተማ 2-1 የበላይነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።
ደለለኝ ደቻሳ – ወላይታ ድቻ
ስለ ጨዋታው
“ጨዋታውን ተቆጣጥረን ለመጫወት ሞክረናል ፤ በሁለቱም አጋማሾች ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች በጉጉት የተነሳ መጠቀም ሳንችል ቀርተናል።በዋነኝነት የተከላካዮች ስህተት ዋጋ አስከፍሎናል።
የአንተነህ ጉግሳ አለመኖር ስለፈጠረው ተፅዕኖ
“እንደተመከታችሁት አዩብ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ያለመረጋጋት ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን መጠነኛ መሻሻሎች ነበሩ።በመጀመሪያው አጋማሽ ከኃላ የነበረብን ክፍተት ለመድፈን ስንሞክር ፊት ላይ ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች አለመጠቀማችን ዋጋ አስከፍሎናል።”
ስለ ስንታየሁ መንግሥቱ ጉዳት
” አሁን ላይ በእርግጠኝነት ስለጉዳቱ መናገር አልችልም። የስንታየሁ መውጣት በእርግጥ ጎድቶናል። ከእሱ መውጣት በኃላ ረጃጅም ኳሶችን ትተን አጫጭር ኳሶችን ለመጫወት ሞከረናል። ለመጫወት በፈለግነው መንገድ መንቀሳቀስ ብንችልም ሳጥን ውስጥ ግን የሚቀሩን የተወሰኑ የተግባቦት ችግሮች ዋጋ አስከፍሎናል።”
ፍሰሀ ጥዑመልሳን – ድሬዳዋ ከተማ
ቀደም ባሉ ጨዋታዎች ይታይበት ስለነበረው ብስጭት
ቡድኔ እየተስተካከል ነው ያለው። ዞሮ ዞሮ ግን ሁሌ ወደ መጨረሻ ላይ ጫና የሚፈጥርብን የምንስታቸው ኳሶች ናቸው። መጀመሪያ ላይ መጨረስ ስንችል ብዙ ጎል ሳትን። እነኚህ ነገሮች ሊቀረፉ አልቻሉም። ያው አሁንም እነሱ ላይ እንሰራለን በውጤቱ ግን ደስተኛ ነኝ።
ሙኸዲን ሙሳ የዕለቱ ብቃት
ሙኸዲን እንግዲህ ከፕሮጀክት ጀምሮ አብረን ነው ያለነው ፤ እኔም ነኝ ያሳደግኩት። እዚህ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ህፃን ልጆች እኔ ያሳደግኳቸው ናቸው። እሱም ከእኔው ጋር ነው የኖረው። እና ልጁ ፈጣን ነው ፤ እንደውም ተጫወተ ማለት አይቻልም። ያለውን አቅም ገና አላወጣም። ትንሽ እንደቅዝቃዜም ያመው ስለነበር እያፈነው ነው የሚወጣው። ወደ ፊት ግን ከዚህ የተሻለ ነገር ያሳያል ብዬ አስባለሁ።
በጎል ረገድ የደረገውን ስለማግኘቱ
ቅድም እንዳልኩት ነው አላገኘሁም። ብዙ ኳሶች ስተናል። ራሱ ሙኸዲን ሁለት ኳስ ነው የሳተው። ያው አንግሉ ደግሞ በየጨዋታው ኮከብ ተጫዋች ይባላል። ኮከብ መሆን ያለበት አግዳሚው እና ቋሚው ነው ይመስለኛል። እስካሁን ወደ 13 ኳስ ነው አግዳሚ እና ቋሚ የመታብን። እና በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው። ይሄ ደግሞ ከምን የመጣ ነው የምለው የምንሰራበት መላው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የልምምድ ሜዳ ጎላቸው በዘፈቀደ የተሰራ ነው። እግር ወይደለም ኳስ የሚመታው ጭንቅላት ነው። እዛ ላይ ተለማምደው ይመጣሉ እዚህ ስህተት ይሰራሉ። ይሄ ነገር ራሱ ቢታሰብበት ደስ ይለኛል።
ሌላው ኮቪድን የተመለከተ የምሰጠው ሀሳብ አለኝ። ወላይታ ድቻን ለመውቀስ አይደለም። ይሄ የህይወት ጉዳይ ነው። ተማርምረን እንመጣለን። የተመረመርንበት ወረቀት እና ቴሴራ ሊተያይ ይገባል። ዛሬ አሁን ቼክ ስናደርግ ከእነሱ ሁለት ያልተመረመረ አግኝተናል። እንዲህ ዓይነት ችግር ስላለ አወዳዳሪው አካል ጥንቃቄ ቢያደርግ ጥሩ ነው፤ የህይወት ጉዳይ ስለሆነ።
© ሶከር ኢትዮጵያ