ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ በአሸናፊነቱ ቀጥሏል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን አራተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ ቀጥሎ መከላከያ አዲስ አበባ ከተማን 3 ለ 1 ረቷል፡፡

ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ ቢታይም አጋጣሚዎችን በተደጋጋሚ በመፍጠሩ ረገድ ግን መከላከያዎች የበላይነቱን ይዘው አርፍደዋል። በሁለቱም መስመሮች ወደ ሴናፍ ዋቁማ በሚጣሉ በርከት ያሉ ኮሶች ዕድሎችን በማግኘት ጥቃት መሰንዘራቸው የቀጠሉት እንስቶቹ የአዲስ አበባ ከተማን የቅብብል ሒደት በማቋረጥም የተዋጣላቸው ሆነው ታይተዋል፡፡ አዲስ አበባ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹን አስር ደቂቃዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ አጥቂዋ ቤተልሄም ታምሩ ፊት ለፊት ከታሪኳ በርገና ተገናኝታ ያመከነችሁ ንፁህ ዕድል ማሳያ እንደነበር ማየት ይቻላል፡፡ ይሁንና እና ቀስ በቀስ የጨዋታ ቅርፅ እየያዙ የመጡት መከላከያዎች ጎል አስቆጥረዋል፡፡ 14ኛው ደቂቃ በግራ በኩል ኳስን በማሻገር ወደ ግብ ክልል በመላኩ የተዋጣላት መሳይ ተመስገን የሰጠቻትን ኳስ ልማደኛዋ አጥቂ ሴናፍ ዋቁማ ወደ ግብነት ለውጣ ቡድኗን መሪ አድርጋለች፡፡

በመስመር አጨዋወትም ሆነ በመሐል ሜዳው ላይ ብልጫን እየወሰ የመጡት መከላከያዎች በህይወት ረጉ፣ ሴናፍ ዋቁማ እና መዲና ዐወል ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ጫናዎችን አሳድረዋል፡፡30ኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸው ሰምሮ ሁለተኛ ጎል ከመረብ አዋህደዋል፡፡ አሁንም በግራ በኩል መሳይ ተመስገን ባደረገችው አብዶ ወደ ግብ ክልል ስትልክ ሴናፍ ዋቁማ በድጋሚ ለራሷም ሆነ ለቡድኗ ሁለተኛ ግብ አግብታ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ብርቱ ፉክክር ለማድረግ ጥረት ያደረጉት አዲስ አበባ ከተማዎች ኳስን በሚይዙበት አጋጣሚ ሊጠቀም የሚችል ወይንም አጥቂዋ ቤተልሄምን ሊረዳት የሚችል አጋዥ ተጫዋች ባለመኖሩ የተገኙ ዕድሎች በቀላሉ ሲመክኑ ተመልክተናል፡፡ በአንፃሩ ከግብ ጋር ቁርኝት የነበራቸው መከላከያዎች በዚህኛውም አጋማሽ በሴናፍ ዋቁማ መሳይ ተመስገን እና መዲና ዐወል ያለቀላቸውን ዕድሎች አግኝተዋል፡፡መልሶ ማጥቃት ላይ ትኩረት በማድረግ ከረጃጅም ከሚጣሉ ኳሶች ግብን ለማግኘት የታተሩት አዲስ አበባ ከተማዎች 52ኛው ደቂቃ በረጅሙ ትርሲት መገርሳ የሰጠቻትን በአግባቡ ተቆጣጥራ ቤተልሄም ታምሩ ወደ ግብ በመለወጥ አዲስ አበባን ወደ 2 ለ 1 አሸጋግራለች፡፡

ግብ ካስቆጠሩ በኃላ ተነሳሽነት ይኖራቸዋል ተብሎ ቢጠበቅም የተቀዛቀዙት የአሰልጣኝ ሙሉጎጃም እንዳለ ቡድን አዲስ አበባ 82ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ ስታሻግር የአዲስ አበባ ግብ ጠባቂ ቤተልሄም ዮሐንስ ጨርፋው ስታልፋት መሳይ ተመስገን በግንባር ገጭታ አስቆጥራባቸው መከላከያ 3 ለ 1 አሸናፊ ሆኗል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የመከላከልያዋ አማካይ ህይወት ረጉን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራም ለተጫዋቿ ሽልማቱን አበርክተዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ