ሪፖርት | በመገባደጃው የተጋጋለው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ

ባህር ዳር እና ፋሲልን ያገናኘው የአምስተኛው ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ በክስተቶች ተሞልቶ 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በጨዋታው ባህር ዳር ከተማ በወልቂጤ ከተማ ከተረታው ቡድን የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ጉዳት የገጠመው ዜናው ፈረደ ፣ በረከት ጥጋቡ እና ግርማ ዲሳሳን በወሰኑ ዓሊ ፣ ሔኖክ አወቀ እና የመጀመሪያ ጨዋታውን ባከናወነዉ አፈወርቅ ኃይሉ ተክተዋል። በአንፃሩ ወላይታ ድቻን የረታው ፋሲል ከነማ ምንም ለውጥ ሳያደርግ ጨዋታውን ጀምሯል።

ከጅምሩም የተጠበቀውን ያህል ያልነበረው ቀዳሚው አጋማሽ ይበልጥ እየተቀዛቀዘ የሄደ ነበር። በጨዋታው መጀመሪያ ደቂቃዎች ኳስ ይዘው ይታዩ የነበሩት ባህር ዳሮች የተጋጣሚያቸውን የኋላ ክፍል ለማስከፈት ያረጉት የነበረው ጥረት እምብዛም ውጤት አላመጣላቸውም። ይልቁንም 9ኛው ደቂቃ ላይ እንየው ካሳሁን ከቀኝ መስመር ባሻማው እና ሙጂብ ቃሲም በግንባር በገጨው ኳስ ፋሲሎች የመጀመሪያውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። ወደ ሳጥን ውስጥ በመግባት ይሻሉ የነበሩት ፋሲሎች 16ኛው ደቂቃ ላይ መናፍ ዐወል ሙጂብ ቃሲም ላይ በሰራው ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተውም ራሱ ሙጂብ አስቆጥሮ ፋሲልን መሪ አድርጓል።

ግጭቶች እየተበራከቱ በሄዱበት ጨዋታ በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ጥፋሮችን የሰራው የባህር ዳሩ ወሰኑ ዓሊ 26ኛው ደቂቃ ላይ በሁለተኛ ቢጫ የወጣበት ቅፅበት ጨዋታውን ለባህር ዳር ይበልጥ ከባድ አድርጎታል። ወሰኑ ሜዳውን ለቆ በሚወጣበት ወቅት እንዲሁም በተመልካች መቀመጫ ላይ ሆኖ በእንባ ሀዘኑን ሲገልፅ ተስተውሏል።

ከቀይ ካርዱ ክስተት በፊት ከቅጣት ምት በተነሳ ኳስ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ ሚካል ሳማኬ ካዳነበት ኳስ በኋላም ቡድኑ እስከ 40ኛው ደቂቃ የባዬ ገዛኸኝ የሳጥን ውጪ ሙከራ ድረስ ሌላ ዕድል አልፈጠረም። ፋሲሎችም ቢሆኑ ያገኙትን የቁጥር ብልጫ ተጠቅመው ጠንካራ ጥቃቶችን ሳይሰነዝሩ ጨዋታው በመሀል ሜዳ እንቅስቃሴዎች ተገድቦ ቡድኖቹ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በጀመረባቸው ደቂቃዎች ከባባድ ሙከራዎች ተደርገዋል። ተቀይሮ የገባው የባህር ዳሩ ግርማ ዲሳሳ 48ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ሁለተኛው ቋሚ ላይ የጣለውን የቅጣት ምት መናፍ ዐወል ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። በፋሲሎች በኩል ደግሞ 50ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከግራ መስመር ይዞ በመግባት አክርሮ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ከዚህ በኃላ ጨዋታው ያለሙከራዎች ለረጅም ደቂቃዎች ቀጥሏል። ፍፁም ዓለሙ እና ባዬ ገዛኸኝን ከፊት አድርገው በፈጣን ሽግግር ጎል ላይ ለመድረስ ጥረት ያደርጉ የነበሩት ባህር ዳሮች የተሻለ ታታሪነት ሲታይባቸው ፋሲሎች ከሳጥን ውጪ ሙከራዎች ከማድረግ ውጪ ተቀዛቅዘው ታይተዋል።

በተለይ 74ኛው ደቂቃ ላይ ከባህር ዳር የማዕዘን ምት በኋላ በመልሶ ማጥቃት አምስት ለአንድ ሆነው ግብ ላይ የደረሱት ፋሲሎች ያመከኑት ኳስ የመዘናጋታቸው ምልክት ነበር። በአንፃሩ አጥቂው ምንይሉ ወንድሙን ጭምር በማስገባት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚን ሲያነፈንፉ የነበሩት ባህር ዳሮች ውጤቱን መቀልበስ ችለዋል። 75ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ በቀኝ መስመር ገብቶ የመታውን ኳስ ሚካል ሳማኬ ሲተፋው ባዬ ገዛኸኝ አግኝቶ ቡድኑን አቻ አድርጓል። 81ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ምንይሉ ወንድሙ በከድር ኩሉባሊ የተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብነት ለውጦታል።

ነገር ግን ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ባህር ዳሮች ያገኙትን የመምራት ዕድል ያሳጣቸውን ክስተቶች አስከትሏል። የሁለተኛው ግብ ባለቤት ምንይሉ መለያ በማውለቁ ቀጥሎም ሽመክት ጉግሳ ላይ በሰራው ጥፋት በደቂቃዎች ልዩነት ከሜዳ ለመሰናበት ተገዷል። ለሁለተኛ ጊዜ ቡድኑን ዋጋ ያስከፈለው ሀሪስተን ሄሱም ከቅጣት ምት የተነሳውን ኳስ በአግባቡ መቆጣጠር ሳይችል ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ 85ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል ነጥብ እንዲጋራ ያስቻለችውን ግብ እንዲያስቆጥር ምክንያት ሆኗል። ሁለት ተጫዋቾችን በቀይ ያጡት ባህርዳሮች አንዷን ነጥብ ለማስጠበቅ በቀሩት ደቂቃዎች የነበረውን የፋሲሎችን ጫና ለመከላከል ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው በመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ የተጠባቂነቱን ያህል በውጥረት የተሞላው ጨዋታ 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ