የአሠልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 2-2 ባህር ዳር ከተማ

በድራማዊ ክስተቶች ከተሞላው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።


ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ተጋጣሚ ቡድን 2 ተጫዋቾችን በቀይ ካርድ አጥቶ ቡድኑ ጨዋታውን ስላለመቆጣጠሩ

ጅምራችን ጥሩ ነበር። ነገርግን ተጋጣሚያችን ተጫዋች ካጣ በኋላ መቀዛቀዞች ነበሩብን። ተጋጣሚ የፈለገ በጎዶሎ ተጫዋቾች ቢጫወትም የውስጥ መነሳሳት ከሌለ በስተቀረ ምንም አይመጣም። እረፍት ላይም የቁጥር ብልጫውን ለመጠቀም ተነጋግረን ነበር። ግን ሜዳ ላይ በተነጋገርነው ልክ አላገኘሁም። ከኋላ መስመራችን አካባቢ የነበረብንን ስህተቶች ተጨምሮ ነገሮችን አክብዶብን ነበር። በአጠቃላይ ግን የዛሬው ውጤት ለእኛ እጅግ የሚያስከፋ ነው። በቀጣይ ያሉብንን ክፍተቶች ለማስተካከል እንሞክራለን።

ቡድኑ ስለታየበት የመነሳሳት ችግር

የመጫወት ፍላጎት ማጣት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ያለህን ነገር መስጠት መቻል አለብህ። ተጋጣሚህ ዘጠኝም ሆነ ስምንት የመነሳሳት ስሜት በውስጡ ካለ ቡድኑ ብዙ ነገር ማድረግ ይችላል። ግን እኛ ይህንን የመነሳሳት ስሜት አተነው ነበር። የተጋጣሚ የተጫዋቾች ቁጥሩ አንሷል እና እንችላለን ብሎ ማሰብ ሳይሆን ለማድረግ መጣር ነበረብን። ይህ ነገር ነበር ያቃተን። ወደፊት ግን ይህንን ችግር ለማስተካከል እንሞክራለን።

ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ

ከጨዋታው በፊት ቡድኑ ላይ ስለነበረ ጫና እና ስለ ጨዋታው

ካለፉት ጨዋታዎች ነጥብ መጣላችን የተለየ ጫና አላሳደረብንም። በዛሬው ጨዋታ ግን ተጫዋቾቼ ጨዋታውን ለማሸነፍ ከልክ ያለፈ ፍላጎት ስለነበራቸው በመጀመሪያው አጋማሽ እንደምንፈልገው አልተጫወትንም። በዚህ ላይ ደግሞ የፍፁም ቅጣት ምቱ እና ቀይ ካርዱ ሌላ ያልጠበቅነው ነገር ይዞብን መጣ። ከዛም ጨዋታውን እንዴት መወጣት እንዳለብን ስናስብ ቆይተን በሁለተኛው አጋማሽ የራሳችንን መንገድ ለመከተል ሞክረናል። በአጠቃላይ ግን ተጫዋቾቼ ደጋፊያቸውን ለማስደሰት ላደረጉት ተጋድሎ ላመሰግናቸው እወዳለው።

ስለ ሁለቱ ቀይ ካርዶች

ስለዚህ ጉዳይ ባላወራ ደስ ይለኛል። ስለ ቀይ ካርዶቹ ካወራሁ ብዙ ነገር ስለምነካካ ጉዳዩን ማንሳት አልፈልግም። እንደ ሁል ጊዜው ማንም ላይ ጣታችንን አንጠቁምም። ስህተታችንን ለማረም ግን ጠንክረን እንሰራለን። ግን ቀይ ካርዶቹ የጨዋታ እቅዳችንን አበላሽቶብናል። አሁንም በድጋሜ ተጫዋቾቼ ላሳዩት ተጋድሎ ያለኝን ክብር መግለፅ እፈልጋለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ