ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ አዳማ ከተማ

የውድድር ሳምንቱ የመጨረሻውን ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እነሆ።

በዝውውር መስኮቱ በመካከላቸው በነበረው የተጫዋቾች ፍልሰት መነሻ እና መድረሻ የሆኑት ቡድኖች በሚያደርጉት ጨዋታ አምስተኛው ሳምንት ይጠቃለላል። ሰባት የሚደርሱ የሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋቾች በአዳማ ከተማ ተጫውተው ማሳለፋቸውም ለጨዋታው ልዩ ትርጉም ያሚሰጥ እንደሚሆን ይታሰባል።

ከስምንት ቀናት በኋላ ወደ ውድድር የተመለሱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች የተራዘመው ዕረፍት የነበሩበትን የማሸነፍ መንፈስ እንዳያቀዘቅዘው ከሚጭረው መጠነኛ ስጋት ውጪ የሚያመጣው በረከት ከፍ ያለ ነው። በዚህ ረገድ ሦስት ጨዋታዎችን አድርጎ በማሸነፍ ሰፊ ራሱን የማሻሻያ ጊዜ ያገኘው ቡድኑ በተለይ በአካል ብቃት ረገድ ይበልጥ ተሻሽሎ የሚቀርብበትን ዕድል ያገኛል። ከዚህ ውጪ ዳዋ ሆቴሳ በሌለበት የቡድኑ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች ያሳዩት ብቃት ከዳዋ መመለስ ጋር ተጨምሮ ሆሳዕናን ከባድ ተጋጣሚ ያደርገዋል። በተለይም የካሉሻ አልሀሰን በቂ ሽፋን ከሚሰጡት አማካዮች ፊት መሰለፍ የተጫዋቹን የማጥቃት ሚና የሚያጎላው ሆኗል። ይህ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ከተከላካይ መስመሩ ጠጣርነት እና ከፊት መስመሩ የሦስትዮሽ ጥምረት በግብ አስቆጣሪ ሰንጠረዥ ውስጥ መካተት አንፃር ስናየውም ደካማ የውድድር ዓመት እያሳለፈ ለሚገኘው አዳማ ጨዋታው ቀላል እንደማይሆን ማሰብ ቀላል ነው።

የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስብስብ ያለምንም የጉዳት ዜና የነገውን ጨዋታ የሚያደርግ ሲሆን በሲዳማ ቡናው ጨዋታ የቀይ ካርድ ሰለባ የሆነው ግብ ጠባቂው መሀመድ ሙንታሪ ብቻ ጨዋታው ያመልጠዋል።

በአራተኛው ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር ያለግብ የተለያየው አዳማ ከተማ ከመክፈቻው ጨዋታ በኃላ ነጥብ አስክቶ መውጣቱ ካልሆነ ሌላ ከጨዋታው የሚወስደው መልካም ነገር ያለ አይመስልም። ኳስ ይዞ ለመጫወት ሀሳቡ ያለው የሚመስለው አዳማ የተሳኩ ቅብብሎችን ለመከወን ሲቸገር እና ኳሶች ሲቆራረጡበት ይታያል። ይህ ደግሞ እንደነገ ተጋጣሚው ጉልበታም እና ፈጣን አጥቂዎች ካሉት ቡድን ጋር ሲገናኝ አደጋ ላይ ሊጥለው የሚችል ደካማ ጎኑ ነው። በማጥቃት ሂደቱም ላይ ባተጋጣሚ የተከላካይ ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች በቁጥር መበለጥ ወደ ፊት የሚሄድባቸውን አጋጣሚዎች አቅም ሲያሳጣቸው ሲታይ ከርቀት የሚደረጉ የቡድኑ ሙከራዎችም ግብ ጠባቂዎችን የሚፈትኑ አልሆኑም። አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል ሁሉንም የቡድኑም ድክመቶች በአንዴ ለማስተካከል የሚቸግራቸው ቢሆንም የፊት መስመሩን ችግር መቅረፍ ውጤት ሊያስገኝላቸው እንደሚችል ግን መናገር ይቻላል። በተለይ አብዲሳ ጀማል ሙሉ ጤና ላይ ከተገኘ እና አዳማ ግብ ማግኘት ከቻለ ሰሞኑን በሌሎች ቡድኖች እያየነው እንዳለነው ውጤት አስጠብቆ ለመውጣት እንደሚጥር ይታሰባል።

አዳማ ከተማ ወሳኝ አጥቂው አብዲሳ ጀማል ከጉዳቱ ያገገመለት ሲሆን ቀለል ያለ ልምምድ መስራት የጀመረው ፍሰሀ ቶማስ መሰለፍ ግን አጠራጣሪ ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪ የቡድኑ የመጀመሪያ አምበል ሱለይማን መሀመድ አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኝ በመሆኑ የቀድሞው የቡድን ጓደኞቹን በተቃራኒው የማይገጥም ይሆናል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለሁለት ጊዜያት ተገናኝተው ሁለቱንም አዳማ ከተማ አሸንፏል። አዳማ 4 ጎሎች ሲያስቆጥር ሆሳዕና አንድ አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ዳንኤል ተሾመ

ታፈሰ ሰረካ – ደስታ ጌቻሞ – ትዕግስቱ አበራ – እዮብ ማቲያስ

ሙጃይድ መሀመድ – ደሳለኝ ደባሽ

የኋላእሸት ፍቃዱ – በቃሉ ገነነ – ጀሚል ያዕቆብ

አንዲሳ ጀማል

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

ደረጄ ዓለሙ

ሱለይማን ሀሚድ – እሴንዴ አይዛክ – ተስፋዬ በቀለ – ሄኖክ አርፌጮ

ካሉሻ አልሀሰን – ተስፋዬ አለባቸው – አማንኤል ጎበና

ቢስማርክ አፒያ – ሳሊፉ ፎፋና – ዳዋ ሆቴሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ