በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን አራተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አቃቂ ቃሊቲን 6 ለ 0፤ ሀዋሳ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 4 ለ 1 ድል አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የስራ አስፈፃሚ እና የሴቶች ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሶፊያ አልማማው ታታሪነት በሚገባ እየተካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር በሀዋሳ ዛሬም በሁለት ጨዋታዎች ቀጥለው ሲደረጉ በተካሄዱትም መርሀ ግብሮች አስራ አንድ ግቦች የተቆጠሩበት ነበር፡፡
ረፋድ 4:00 ሲል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከ አቃቂ ቃሊቲ ያገናኘው ጨዋታ ቀዳሚው የዕለቱ መርሀ ግብር ነው፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አቃቂ ቃሊቲዎች መሀል ሜዳ ላይ ያመዘነ የጨዋታ መንገድን ቢከተሉም የንግድ ባንክ የአንድ ሁለት የመሀል ሜዳም ሆነ ከመስመር ከሚነሱ ዕድሎች ግቦችን ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ገና በጊዜ ተሳክቶላቸው ግብ እና መረብን አገናኝተዋል፡፡ 6ኛው ደቂቃ ላይ መሀል ሜዳው አጋማሽ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት ገነሜ ወርቁ ከርቀት አክርራ በመመታት የአቃቂዋ ግብ ጠባቂ ገነት አንተነህ ስህተት ታክሎበት ግብ አስቆጥራለች፡፡
አቃቂ ቃሊቲዎች ኳስን በሚይዙበት ወቅት ጨራሽ የሚባል አጥቂ በቡድኑ ውስጥ ባለመኖሩ ያገኙትን ኳስ ከርቀት ሲሞክሩ ተመልክተናል፡፡ አማካይዋ አሰናቀች ትቤሶ ከርቀት ያደረገቻት ብቻኛዋ ኢላማዋን የጠበቀችዋ አጋጣሚ ነበረች፡፡9ኛው ደቂቃ በድጋሚ ሁለተኛ ግብ የአቃቂን የመከላከል ስህተት ተመልክተው ባንኮች አስቆጥረዋል፡፡ ሰናይት ቦጋለ በቀጥታ መታ ገነት ስትመልስ አየር ላይ እያለች ረሂማ ዘርጋው በግንባር ገጭታ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጋለች፡፡ 34ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ በቀኝ በኩል ተከላካዮችን አልፋ በቀጥታ የመታቻት ኳስ ከመረብ አርፋለች አሁንም ፋታ የለሽ ጥረት ተጨማሪ ግብ ለማከል ትግል ያደረጉት የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ልጆች 40ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ቦጋለ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ አስደናቂ ግብ በማስቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል ክለቦቹ አምርተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታ ለመመለስ አቃቂ ቃሊቲዎች ታታሪነት ቢታይባቸውም ህይወት ደንጊሶን ቀይሮ በማስወጣት ወደ ኃላ እመቤት አዲሱን ስቦ በሚጫወተው ንግድ ባንክ በሚገባ በዚህም አጋማሽ ተቆጣጥሮ በመጫወት የግብ ዕድልን ሲፈጥሩ ታይቷል፡፡ 69ኛው ደቂቃ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ያሻገረችሁን ኳስ ረሂማ ዘርጋው በግንባር በመግጨት አሁንም የአቃቂዋን ግብ ጠባቂ ስህተት ተጠቅማ ለራሷ ሁለተኛ ለክለቧ አምስተኛ ግብነት አግብታለች፡፡75ኛው ደቂቃ ላይ ልማደኛዋ አጥቂ ሎዛ አበራ አስገራሚ ግብ አክላ ጨዋታው በንግድ ባንክ 6 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ልሳን የሴቶች ስፖርት ሎዛ አበራን የጨዋታው ምርጥ በማለት ሸልሟታል፡፡
ቀን 10፡00 ላይ የቀኑ ሁለተኛ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ መካከል ተደርጓል፡፡ እስከ 30ኛው ደቂቃ ድረስ በጥብቅ መካከል ከዛም ባለፈ በመልሶ ማጥቃት ሁለቱ ክለቦች ለመጫወት የቻሉ ቢሆንም በሂደት ረጃጅም ኳሶችን ቀስ በቀስ ወደ መጠቀሙ የገቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ኳስን ይዞ በመጫወት አስከፍቶ ለመግባት በሚሞክሩት ሀዋሳዎች ለመበለጥ ተገደዋል፡፡ 35ኛው ደቂቃ ላይም መሳይ ተመስገን በቀኝ በኩል በድንቅ ብቃቷ ታግዛ ወደ ሳጥን ይዛ ከገባች በኃላ መሬት ለመሬት ስትልከው ረድኤት አስረሳኸኝ በግራ እግሯ አስቆጥራው ሀዋሳን መሪ አድርጋለች፡፡ ድሬዳዋ ከተማዎች እንደ ቡድን በመንቀሳቀሱ ረገድ ደካማ ቢሆንም የመሐል ሜዳዋ ጥበበኛ ማዕድን ሳህሉ ኳሶችን ግን አደገኛ ነበሩ ሆኖም አማካዩዋ ኳስን ስትይዝ ወደ ግብነት የሚለውጥ ተጫዋች ባለመኖሩ ሁለተኛ ግብ በተቃራኒው ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ 45ኛው ደቂቃ ላይ መቅደስ ማሞ በድሬዳዋ ተከላካዮች መሀል የሰነጠቀችሁ ኳስ መሳይ ጋር ደርሶ በቀኝ እግሯ አስቆጥራው ወደ 2 ለ 0 ቡድኗን አሸጋግራ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽም መቀመስ ያልቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች በርከት ያሉ የጠሩ ዕድሎችን በአጥቂዎቻቸው ፈጥረውዋል፡፡ ገና ከአረፍት ከተመለሱ ሁለት ደቂቃ እንደተቆጠረ ረድኤት አስረሳኸኝ ጣጣውን የጨረሰ ኳስ አቀብላት መሳይ ተመስገን በድንቅ አጨራረስ ወደ ሳጥን ውስጥ ገብታ በማስቆጠር አሁንም የሀዋሳን ግብ ከፍ አድርጋለች፡፡ በፊት መስመር ላይ ግልፅ ክፍተት እንዳለባቸው የተረዱት የአሰልጣኝ ብዙአየው ጀምበሩ ስብስብ ሀሳቤ ሙሶን ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት አምጥተው ለማጫወት ተገደዋል፡፡ይሁን እንጂ የሀዋሳን አጥቂ መቋቋም ሲሳናቸው የታዩት ሀዋሳዎች 56ኛው ደቂቃ የመጨረሻ ግባቸውን አግኝተዋል፡፡ መሳይ ተመስገን የግል አቅሟን ያሳየችበትን ጎል ከመረብ አሳርፋ ሀትሪክ ሰርታለች፡፡ ጨዋታውሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው ሀሳቤ ሙሶ ከእታለም አመኑ የተገኘን የቅጣት ምት ኳስ በግንባር ገጭታ በማስቆጠር ድሬዳዋ ካለግብ እንዳያጠናቅቅ አድርጋ ጨዋታው በሀዋሳ 4 ለ1 አሸናፊነት ፍፃሜውንአግኝቷል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት ለሀዋሳ ሀትሪክ የሰራችሁን መሳይ ተመስገንን የጨዋታው ኮከብ ብሎ ሸልሟታል
© ሶከር ኢትዮጵያ