ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ወልቂጤ ከተማ

የአምስተኛ ሳምንቱን የመጨረሻ ቀን መክፈቻ ጨዋታ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

እጅግ በተዳከመ አቅም ከሦስተኛ ጨዋታው አንድ ነጥብ ያሳካው ሲዳማ ቡና የውድድር ዓመቱን የሚያስተካክልበትን ሌላ ዕድል ነገ የሚሞክር ይሆናል። አሰላለፉ ላይ ተደጋጋሚ ለውጦች ሲያደርግ የሚታየው ቡድኑ ያለበት የውህደት ችግር በግልፅ የሚታይ ሆኗል። መናበብ የማይታይበት የመሀል ክፍሉ ጥቂት ዕድሎችን ብቻ ሲፈጥር ፊት መስመር ላይም ከጉጉት የመነጨ የሚመስል አለመረጋጋት በጉልህ ይታይበታል። በርካታ ችግሮች ያሉበት የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ቡድን በመንፈስ ጠንክሮ ለመመለስ በየትኛውም መንገድ ይሁን የሚገኝ ድል በእጅጉ አስፈላጊው ነው። በመሆኑም በነገው ጨዋታ ቀጥተኛነትን የቀላቀለ አቀራረብ እና ሆኖለት ግብ ካስቆጠረም ወደ ጥንቃቄው የሚያመዝን የጨዋታ ዕቅድ እንደሚኖረው ይገመታል።

ሲዳማ ቡና የወሳኝ ተጫዋቹ ጫላ ተሺታ እና በአዳማው ጨዋታ የተጎዳው አጥቂው ይገዙ ቦጋለን ግልጋሎት የማግኘቱ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ለቡድኑ እጅግ መልካም የሆነው ዜና ግን የውጪ ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾቹን በከፊል የመጠቀም ፍቃድ ያገኘ መሆኑ ነው።

ባልተጠበቀ የተጫዋቾች ምርጫ በመታገዝ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ያሳካው ወልቂጤ የውድድሩ ኮስታራ ተፎካካሪ መሆኑን ለማሳየት የነገውን ጨዋታ ያደርጋል። እንደተጋጣሚያቸው ሁኔታ ተለዋዋጭነት ያለው አቀራረብን ይዘው ሲገቡ የሚታዩት ወልቂጤዎች ነገ የተሻለ የማጥቃት ዕቅድ እንደሚኖራቸው ይታሰባል። ያለፈው ጨዋታ ቡድኑ ውጤት የማስጠበቅ እና በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን የመፍጠር አቅም እንዳለው ከማሳየቱ ባለፈ የአጨራረስ ችግሩንም ያጋለጠ በመሆኑ ቡድኑ በዚህ ረገድ ተሻሽሎ ለመቅረብ እንደሚሞክር ከጨዋታው የሚጠበቅ ሌላው ጉዳይ ይሆናል። ከዚህ ውጪ የፍሬው ሰለሞን እንቅስቃሴን መሰረት ያደረገው የቡድኑ የቀኝ መስማር ጥቃት የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር አንፃር ከሲዳማ የግራ ወገን ጋር የሚኖረው ፍልሚያ የሚጠበቅ ነው።

ወልቂጤ ከተማዎች ሙሃጅር መኪ እና ሄኖክ አየለ ከጉዳት ያገገሙላቸው ሲሆን አዳነ በላይነህ እና ዳግም ንጉሴ ግን በጉዳት ሳቢያ ለጨዋታው ብቁ አለመሆናቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ከዚህ ውጪ በአዳማው ጨዋታ የቀይ ካርድ የተመለከተው አሳሪ አልመሀዲም ጨዋታው ያልፈዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ሁለቱ ቡድኖች በተሰረዘው የውድድር ዓመት ላይ በተጫወቱ ወቅት ሲዳማ 1-0 ማሸነፍ ችሎ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

አማኑኤል እንዳለ – ሰንደይ ሙቱኩ – ፈቱዲን ጀማል – ግሩም አሰፋ

ያስር ሙገርዋ – ግርማ በቀለ – ዬሴፍ ዮሃንስ

ተመስገን በጅሮንድ –ሀብታሙ ገዛኸኝ – አዲሱ አቱላ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

ስዩም ተስፋዬ – ቶማስ ስምረቱ – አሚን ነስሩ – ረመዳን የሱፍ

ያሬድ ታደሰ – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ

ፍሬው ሰለሞን – ሄኖክ አየለ – አሜ መሀመድ


© ሶከር ኢትዮጵያ