ረፋድ ባቱ ላይ የተጀመረው የ2013 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 9:00 ላይ ቀጥሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክን የገጠመው መከላከያ 2-0 አሸንፏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ሲሆን የጠራ የግብ እድሎችን ባያስመለክትም ኳስን መሰርት ያደረገ እንቅስቃሴ አሳይቶናል። በ8ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ተጋጣሚው የግብ ክልል በአቤል ታሪኩ አማካይነት የመጀመሪያው የግብ ሙከራ ማድረግ የቻለው የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናው ኤሌኬትሪክ የመጀመሪያውን 15 ደቂቃ በኳስ ቁጥጥር የበለጠ ቢሆንም የጠራ የግብ ማስመልከት አልቻለም። በዚህም በ28ኛው ደቂቃ አደም አባስ የፈጠረውን ጥሩ አጋጣሚ ጃፋር ደሊል ቀድሞ በመውጣት ካዳነበት ውጪ የተሻለ እድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል።
በተቃራኒው የዮሐንስ ሳህሌ ቡድን መከላከያ ቀስ በቀስ የተወሰደበትን የእንቅስቃሴ ብልጫ ለማስመልስ የቻለ ሲሆን ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ ከርቀት በሚሻገሩ ኳሶች ተፅዕኖ ለመውሰድ ያደረጉት ጥረት ፍሬም ባያፈራም በተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል ላይ ኳስን በሁለቱ መስመሮች በማሻገር ጫና ፈጥረዋል። በ25 ኛው እና በ38 ኛው ደቂቃ በግራ እና ቀኝ መስመር በተሻሙ ኳሶች ሁለት ሙከራዎች በማድረግ ለግብ ቀርበውም ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ መከላካዮች እጅግ ብልጫን ወስደው መጫወት የቻሉ ሲሆን በተቃራኒው ኤሌክትሪኮች ኳስን መስርተው በቅብብል ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል ለመድረስ ያረጉት ጥረት ቶሎ ቶሎ የሚቆራረጥ ነበር ።
47ኛው ደቂቃ ካርሎስ ዳምጠው መሬት ለመሬት አክርሮ የመታት ጠንካራ ኳስ የግቡን ቀኝ አግዳሚ ታካ በመውጣት የሁለተኛ አጋማሽ የመጀመሪያ ሙከራ ነበረች። የኤሌክትሪክን ተከላካዮች በሁለተኛው ግማሽ ሲያስጨንቅ የነበረው ካርሎስ ሁለት ለግብ የተቃረቡ ሙከራዎችን ካደረገ ባኋላ በ67ኛው ደቂቃ በግምት 30ሜትር ላይ የግብ ጠባቂውን አቋቋም በመመልከት የመታው ኳስ ከመረብ ተገናኝቶ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል።
ከግቡ መቋጠር በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ የተጫኑት ኤሌክትሪኮች በአቤል ታሪኩ፣ ፍራኦል መንግሥቱ እና አዳም አባስ አማካኝነት ወደፊት በመሄድ ያደረጉት ጥረት ሳይሰምር ቀርቷል። መከላካዮች ደግሞ ምንም እንኳን ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ቢከላከሉም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ፍጥነት የታከለበት ሽግግር በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። በዚህም በ73ኛው ደቂቃ ኤሌክትሪኮች ትተውት የሄዱትን ሜዳ በመጠቀም በመልሶ ማጥቃት ፍቃዱ ወርቁ እና አቤል ነጋሽ አድርገው መክኖባቸዎል።
መደበኛ ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ በካርሎስ ዳምጠው ተቀይሮ የገባው መሐመድ አበራ ከመስመር ይዞት የገባው ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሰለሞን ሀብቴ ወደ ግብነት በመለወጥ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። ጨዋታውም በመከላካ ሁለት ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ