ከፍተኛ ሊግ ሀ | ደሴ ከተማ ወልዲያን አሸንፏል

የ2013 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ ባቱ ላይ 4:00 በተደረገ የምድብ ሀ ሁለተኛ ቀን ጨዋታ ቀጥሎ ወልዲያን የገጠመው ደሴ ከተማ ረጅም ደቂቃዎች በጎዶሎ ቁጥር ተጫውቶ 2-1 አሸንፏል።

የወልድያ ቡድን የተጫዋቾች መታወቂያ (ቲሲራ) በሰዓቱ ይዞ ባለመገኘቱ ምክንያት ተጋጣሚያቸው ደሴ ሜዳ ውስጥ ለሀያ አምስት ደቂቃ ሲያሟሙቅ ቆይቶ ቲሲራ ይዞ በመምጣቱ በመምጣቱ ጨዋታው ተካሄዷል።

ንኪኪዎች የበዙበት እና ረዥም ኳሶች ባስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ በ8ኛው ደቂቃ ከደሴ የግብ ክልል በረጅሙ የተሻገረችውን ኳስ የወልዲያ የተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ አዳነ ተካ ቢሞክረውም የግብ ጠባቂው ምናለ በቀለ ያዳነበት የመጀመርያ ሙከራ ነበር። ወልድያዎች በኩል ኳስን ይዞ ለመጫወት ቢያስቡም ቅብብሎቻቸው ስኬታማ ስላልነበሩ የማጥቃት ክፍላቸው ላይ ይቆረጥባቸው ነበር። በዚህም ምክንያች ጫና ከመፍጠር ተገድበዋል። በ40ኛው ደቂቃ ውስጥ እጅጉን ለግብ የቀረበ የግብ ሙከራ ማድረግ የቻሉትም በቀፀላ ፍቅረማርያም አማካኝነት ብቻ ነበር።

ደሴ ከተማ የፊት አጥቂያቸው ሳሙኤል አባተ እና አኩዌር ቻሞ ላይ ያተኮረ ረጃጅም ኳሶችን ሲጫወቱ ተስተውለዋል። በግራ መስመር ጥሩ እንቅስቃሴን በማድረግ ኳሶችን ወደ ሳጥን እየጣሉ የተቃራኒ ተከላካይ ክፍል ሲረብሽ የነበሩት ደሴዎች በ28ኛው ደቂቃ አብዱልአዚዝ ዳውድ በምንያህል ይመር ላይ በሰራው ጥፋት ከሜዳ ተውግዶ ቀሪዎችን ረጅም ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫውተዋል። ሆኖም ከርቀት በሚደርጉት የግብ ሙከራዎች ከተጋጣሚያቸው ተሽለው ነበር። በተለይም አንሷር መሐመድ እና አኩየር ቻሞ ያደረጉት የግብ ሙከራ ተጠቃሽ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ደሴ ከተማዎች የመጀመሪያው 30 ደቂቃ እጅግ ብልጫን ወስደው መጫወት የቻሉ ሲሆን ወልድያዎች ግን የተከላካይ ቁጥራቸውን በዛ በማድረግ በረጃጅም ኳሶች ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። በዚህም በ58ኛው ደቂቃ በምንያህል ይመር ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ፍፁም ደስይበለው ወደ ግብነት በመለወጥ ወልዲያን መሪ ማድረግ ችሏል።

በሁለተኛው ግማሽ ሲያስጨንቅ የነበረው አኳየር ቻም በ67ኛው ደቂቃ ሉዑልሰገድ አስፋው ያቀበለውን ኳስ በግሩም አጨራረስ የደሴ ከተማን አቻ የሚደርገውን ግብ አስቆጥሯል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴን ያለስመለከተን ጨዋታ ደሴ ከተማ የረጅጅም ኳሶችን ጥቃቶችን ሲዘነዝር በተቃራኒው ወልድያ ኳስን አደራጅቶ ወደፊት ቢጠጉም የተጋጣሚ የግብ ክልል በቀላሉ ሰብሮ ማግባት ተስኗቸዋል። በመከላከሉ ጥሩ የነበሩት ደሴዎች በለስ ቀንቷቸው በ80ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ዮሴፍ ደንገቶ በማስቆጠር ደሴን ወደ መሪነት አሸጋግሯል።

ከግቡ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ወደኃላ ያፈገፈጉት ደሴዎች ጥቃቶች አስተናግደዋል። በ82ኛው ደቂቃ ወሰኑ ማዜ በጭንቅላቱ ገጭቶ እንዲሁም ቴዎድሮስ ብርሃኑ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ በወልድያ በኩል ለግብ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። ጨዋታውም በዚህ መልኩ በደሴ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በበሪሶ በለንጉ በጥሩ ብቃት በተመራው ጨዋታ የወልዲያው አሰልጣኝ መኮንን ወልደ ዮሐንስ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያው ቢጫ ካርድ የተመለከቱ አሰልጣኝ ሆነዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ