“ሁሌም ለሁለቱ ዝግጁ ነኝ” – ዱላ ሙላቱ

በሀዲያ ሆሳዕና ያለመሸነፍ ጉዞ ውስጥ ተቀይሮ በመግባት በቡድኑ ውጤት ማማር ላይ አበርክቶው ከጎላው ዱላ ሙላቱ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ነቀምት ተወልዶ ያደገው ዱላ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለው ቁርኝት የጀመረው ከ2007 በፊት ነው። በቀድሞ አጠራሩ ብሔራዊ ሊግ በሚባልበት ዘመን ሀዲያ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ከቴዎድሮስ መንገሻ እና ተዘራ አቡቴ ጋር የነበራቸው ጥምረት የማይዘነጋ ነው። ዱላ ከሀዲያ በመቀጠል በተለይ በደቡብ ፖሊስ በነበረው ቆይታ ጥሩ የውድድር ዓመት ከማሳለፉ በተጨማሪ ዳግመኛ ደቡብ ፖሊስ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግ ማድረግ ችሏል። አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ወደሚመሩት አዳማ ከተማ አምርቶ የነበረው ዱላ ዘንድሮ አሰልጣኙን ተከትሎ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሶ እየተጫወተ ይገኛል። አምስተኛ ሳምንት በደረሰው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በሀዲያ ሆሳዕና ያለመሸነፍ ጉዞ ውስጥ ተቀይሮ በመግባት አንድ ጎል በማስቆጠር እና ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል በቡድኑ ውጤት ማማር አበርክቶው ከጎላው ዱላ ሙላቱ ጋር ከዛሬው ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ቆይታ አድርገናል።

” በመጀመርያ ፈጣሪዬን አመሰግናለው። ጥሩ የውድድር ዓመት ጅማሮ እያደረኩ ነው። ቡድናችንም አሁን ጥሩ አቋም ላይ ይገኛል። ወደ ፊት ከዚህ የተሻለ ደረጃ ቡድናችን ይሄዳል።

” ሀዲያ ለኔ ባለ ውለታዬ ክለብ ነው። ቡድኑን ከዚህ ቀደም ሳገለግል ቆይቻለው። በድጋሚ መጥቼ በመጫወቴ ደስተኛ ነኝ። ያለፉት ዓመታት በክለቡ ውጤት ዙርያ የተወሰኑ መንገዳገዶች ነበሩ። አሁን ግን ከባለፈው ትምህርት በመውሰድ ጠንካራ ቡድን ተገንብቷል። የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ሁሉንም በማሸነፍ ነጥብ መሰብሰብ ችለናል። የመጨረሻውም ከፈጣሪ ጋር ከባለፉት ዓመታት የበለጠ ጥሩ ነገር እናሳያለን።

“ሁሌም ቢሆን ቋሚም ሆንኩ ተጠባባቂ ለሁለቱም ዝግጁ ነኝ። ራሴን አዘጋጅቼ ነው የምገባው። ምንም የምመርጠው ነገር የለም። አሰልጣኙ ያመነበትን ማድረግ ብቻ ነው ከኔ የሚጠበቀው። ጥሩ ነገርም ሰርቼ የምወጣው አዕምሮዬን ንፁህ አድርጌ ተዘጋጅቼ ስለምገባ ነው። ከዚህ በኋላም ብዙ ነገር ስለሚጠብቀን ያንን ለመወጣት ጠንክረን እንሰራለን።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስለ ዱላ ተቀይሮ በመግባት ለቡድኑ እየሰጠ ስላለው ግልጋሎት ይህን አስተያየት ሰጥተዋል።

“ዱላ ሙላቱን ያለምክንያት አይደለም የምጠቀምበት። በወሳኝ ጨዋታዎች ውጤታማ የሚያረገኝ ነው። ያ የእኔ የአሰራር ስልት ነው። ልጁን የምጠቀምበት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አለ። እንደ አስፈላጊነቱ ከመጀመሪያም ልጠቀም የምችልባቸው ሁኔታዎች አሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ