ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በአምስተኛው ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተስተዋሉ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና የአሰልጣኞች ዐበይት አስተያየቶችን እንደሚከተለው አጠናቅረናል።


👉ሽቅርቅሮቹ አሰልጣኞች

በኢትዮጵያ እግርኳስ ለትጥቅ እና ተያያዥ ጉዳዮች ያለው ደካማ አረደዳ ሰፋ ሲልም በአሰልጣኞቻችን ላይ የሚስተዋል እውነታ ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ የሀገራችን ሁኔታ የተገላቢጦሽ ሆነ እንጂ በአለም አቀፍ ሊጎች የቱታ አሰልጣኞች እንዲሁም ሙሉ ልብስ ለባሽ አሰልጣኞች በሚል በጥቅሉ አሰልጣኞች ሲከፋፈሉ ቢስተዋልም ሌሎች ባለ መደበኛ እና ቅይጥ የአለባበስ መንገዶች የሚከተሉም አይጠፉም።

እርግጥ ነው ይህ አለባበስ ነው የተሻለው የሚለው በግላዊ ዕይታ የሚመሰረት ቢሆንም በሀገራችን አሁን አሁን ብቅ እያሉ የመጡ አዳዲስ አሰልጣኞች አዲስ የፋሽን ባህልን እያስተዋወቁ ይመስላል። በዘንድሮ የውድድር ዘመን የመጀመሪያውን የዋና አሰልጣኝነት ኃላፊነቱን በሀዋሳ ከተማ የተረከበው ሙሉጌታ ምህረት በጨዋታዎች ወቅት በሜዳው ጠርዝ በሙሉ ልብስ መታየትን ምርጫው ያደረገ ይመስላል። በተመሳሳይ የቀድሞው የሙሉጌታ ምህረት መምህር የሆኑትና የወቅቱ የሰበታ ከተማ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱም በተመሳሳይ በሙሉ ልብስ እንዲሁም በመደበኛ አለባበስ መታየት ምርጫቸው ሲያደርጉ በመደመበኛ አለባበሱ የሚታወቀው ፋሲል ተካልኝ በዚህኛው ሳምንት ደግሞ በተለየ መልኩ በሰደርያ በከረባት ሽክ ብሎ ተስተውሏል።

በስታዲየም ጨዋታዎችን የሚከታተሉ ሰዎች ለዓመታት ተለዋጭ አልባሳት የሌላቸው እስኪመስል ድረስ በተመሳሳይ አለባበስ በሜዳው ጠርዝ ሲንጎራደዱ ለምንመለከታቸው አሰልጣኞች “የአዲሱ ትውልድ” አሰልጣኞች የተለየ የፋሽን ምልከታን ይዘው የመጡ ይመስላል።

👉የርዕሰ ዜናው ሰው – ፍሰሀ ጥዑመልሳን

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ድሬዳዋ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት እየመራ የሚገኘው ፍሰሀ ጥዑመልሳን በየጨዋታ ሳምንቱ በድህረ ጨዋታ ቃለ መጠይቆቹ በሚሰጣቸው ሀሳቦች ርዕሰ ዜና መፍጠሩን ቀጥሏል።

ለወትሮም ቢሆን ትችቶች ከአስተያየቶቹ የማይለዩት አሰልጣኙ በዚህ ሳምንት ደግሞ ስለ ሀገራችን የግብ ቋሚና አግዳሚዎች ስሪት የሰጠው አስተያየት ደግሞ የዚህኛው ሳምንት አነጋጋሪው ሀሳቡ ነው።

“በየጨዋታው ኮከብ ተጫዋች ይባላል ፤ ኮከብ መሆን ያለበት አግዳሚው እና ቋሚው ነው ይመስለኛል። እስካሁን ወደ 13 ኳስ ነው አግዳሚ እና ቋሚ የመታብን። እና በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው። ይሄ ደግሞ ከምን የመጣ ነው የምለው የምንሰራበት መላው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የልምምድ ሜዳ ጎላቸው በዘፈቀደ የተሰራ ነው። እግር አይደለም ኳስ የሚመታው ጭንቅላት ነው። እዛ ላይ ተለማምደው ይመጣሉ እዚህ ስህተት ይሰራሉ። ይሄ ነገር ራሱ ቢታሰብበት ደስ ይለኛል።” ሲል ተደምጧል።

እርግጥ ያነሳው ሀሳብ እውነታነት አለው የለውም የሚለው ነገር ጥናትን የሚፈለግ ቢሆንም ይህ አመክንዮ ለሁሉም ክለቦች እንጂ ለድሬዳዋ ከተማ ብቻ የሚሰራ አለመሆኑን ሊረዱ ይረገባል።

👉ጫና ውስጥ የነበረው ዘርዓይ ሙሉ

በተከታታይ ውጤት ማጣቶች እና በተጫዋቾች ተገቢነትና ጉዳት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብቶ የነበረው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በተጫዋቾቹ ተጋድሎ የመጀመሪያውን ድል በማስመዝገብ በተወሰነ መልኩ ከነበረበት ጫና ተንፈስ ያለ ይመስላል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ በተለያየበት ጨዋታ የፊት አጥቂያቸውን ይገዙ ቦጋለን ገና በማለዳ በጉዳት ያጡት አሰልጣኙ በወልቂጤውም ጨዋታ በተመሳሳይ ወጣቱን የመስመር አጥቂ አዲሱ አቱላ ባጋጠመው ጉዳት ተቀይሮ እንደሚወጣ በተረዱበት ወቅት በሜዳው ጠርዝ የነበረውን የቁሻሻ መጣያ ፕላስቲክ በእግራቸው የጠለዙበት መንገድ በወቅቱ የነበረባቸው ጫና የሚያሳይ ነበር።

በስብስባቸው ያካተቷቸውን የውጭ ዜጋ ተጫዋቾች ከስራና መኖርያ ፍቃድ ጋር በተያያዘ ጉዳይ በቅጡ መጠቀም ያልቻሉት አሰልጣኙ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከሳሳው የአጥቂ መስመራቸው ላይ ሁለቱን አጥቂዎችን በተከታታይ ጨዋታዎች ማጣታቸው የተፈጠረባቸው ብስጭት ከዚሁ መነሾ ነው።

ታድያ ምስጋና ለዳዊት ተፈራ በመጀመሪያው አጋማሽ ላስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምትና የቡድኑ ተጫዋቾች በተቀሩት ደቂቃዎች ላሳዩት ጥረት ይግባና ለጊዜውም ቢሆን እፎይ እንዲል አስችለውታል።

👉”ጉዳት ፣ ጉዳት ፣ ጉዳት” ተደጋጋሚው የአስቻለው ኃይለሚካኤል አስተያየት

ሊጉ አምስተኛ ሳምንቱ ላይ ደርሷል ፤ የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል እስካሁን ካደረጓቸው አምስቱም ጨዋታዎች መጠናቀቅ በኃላ በሚሰጧቸው ድህረ ጨዋታ አስተያየቶች ላይ ስለ ጉዳት እና ተጫዋቾች ከጉዳት ሲመለሱ የተሻለ ነገር እንመለከታለን የሚል አስተያየት በተደጋጋሚ ሲሰጡ ይደመጣል።

እርግጥ ነው በጉዳት ምክንያት እስካሁን ያልተጠቀሙበት ባለ ልምዱ የቡድኑ አምበል ከሆነው ሱሌይማን መሀመድ ውጪ ያሏቸውን ተጫዋቾች ምንም እንኳን አሰልጣኙ ከነጉዳታቸው ነው ይበሉ እንጂ እስካሁን እየተጠቀሙባቸው ይገኛል።

ለዓመታት ጠንካራ የነበረው አዳማ ከተማ አሁን ላይ ከስያሜው በስተቀር ተጫዋቾቹ ሆነ አሰልጣኙ የሉም። ታድያ አሰልጣኝ አስቻለው ስያሜው ብቻ የተረከቡትን ቡድን በአነስተኛ በጀት ዳግም አዋቅረው በሊጉ ተፎካካሪ ለማድረግ ከባዱን ፈተና እንደተጋፈጡ ግልፅ ነው። ከስብስብ ጥራት እና ሜዳ ላይ ያላለቁ እግርኳሳዊ ስራዎች ባሉበት ሁኔታ ግን ከወዲሁ የተጫዋቾች ጉዳትን እንደ ምክንያትነት ለመጠቀም በሚመስል መልኩ እየሰጧቸው የሚገኙት አስተያየቶች ምን ያህል ሊያስጉዛቸው እንደሚችል ጊዜ የሚያሳየን ሲሆን ከተራዘመ የዕረፍት ጊዜ በኋላ በጀመረው እና ተደራራቢ ጨዋታዎች እየተደረጉ ባሉበት የዘንድሮው ውድድር የጉዳት መደራረብ በሌሎችም ቡድኖችም ላይ እየታየ ያለ ችግር መሆኑ ግን ሊታወቅ ይገባል።

ዐበይት አስተያየቶች

👉ጳውሎስ ጌታቸው ስለተጫዋቾች ተነሳሽነት…

“ፊሽካ ከተነፋ ጀምሮ ያላቸው እልህ ከዚህ በፊትም እንደተመለከትነው ነው። እንደዚህ ዓይነት ቡድኖች በመስራት ነው የምታወቀውም ፤ ልጆቹ ፍላጎት እንዲኖራቸው ነው። አሁንም ብዙ ቀሪ ጨዋታዎች አሉ። ምንም አልተራራቅንም አንደኛው እኮ አስር ነው ፤ እኛ ሁለት ነን። ከሀያ በላይ ጨዋታዎች አሉ። ስለዚህ ብዙ ነገር ማድረግ ይቻላል። ከተጋገዝን ከተባበርን ጥሩ ነገር መስራት ይቻላል። ወጣቶችም የተደባለቁበት ቡድን ነው። ከአሁን በኋላ ለሚኖረውም እንደእግዚያብሔር ፍቃድ ጥሩ ነገር ለመስራት እንታገላለን።”

👉ሥዩም ከበደ ቡድኑ ስለታየበት የመነሳሳት ችግር…

“የመጫወት ፍላጎት ማጣት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ያለህን ነገር መስጠት መቻል አለብህ። ተጋጣሚህ ዘጠኝም ሆነ ስምንት የመነሳሳት ስሜት በውስጡ ካለ ቡድኑ ብዙ ነገር ማድረግ ይችላል። ግን እኛ ይህንን የመነሳሳት ስሜት አጥተው ነበር። የተጋጣሚ የተጫዋቾች ቁጥሩ አንሷል እና እንችላለን ብሎ ማሰብ ሳይሆን ለማድረግ መጣር ነበረብን። ይህ ነገር ነበር ያቃተን። ወደፊት ግን ይህንን ችግር ለማስተካከል እንሞክራለን።”

👉ፋሲል ተካልኝ ስለ ሁለቱ ቀይ ካርዶች…

“ስለዚህ ጉዳይ ባላወራ ደስ ይለኛል። ስለ ቀይ ካርዶቹ ካወራሁ ብዙ ነገር ስለምነካካ ጉዳዩን ማንሳት አልፈልግም። እንደ ሁል ጊዜው ማንም ላይ ጣታችንን አንጠቁምም። ስህተታችንን ለማረም ግን ጠንክረን እንሰራለን። ግን ቀይ ካርዶቹ የጨዋታ እቅዳችንን አበላሽቶብናል። አሁንም በድጋሚ ተጫዋቾቼ ላሳዩት ተጋድሎ ያለኝን ክብር መግለፅ እፈልጋለው።”

👉ፍሰሀ ጥዑመልሳን ስለ ሙኸዲን ሙሳ የዕለቱ ብቃት እና ኮቪድ 19…

ሙኸዲን እንግዲህ ከፕሮጀክት ጀምሮ አብረን ነው ያለነው ፤ እኔም ነኝ ያሳደግኩት። እዚህ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ህፃን ልጆች እኔ ያሳደግኳቸው ናቸው። እሱም ከእኔው ጋር ነው የኖረው። እና ልጁ ፈጣን ነው ፤ እንደውም ተጫወተ ማለት አይቻልም። ያለውን አቅም ገና አላወጣም። ትንሽ እንደቅዝቃዜም ያመው ስለነበር እያፈነው ነው የሚወጣው። ወደ ፊት ግን ከዚህ የተሻለ ነገር ያሳያል ብዬ አስባለሁ።

ሌላው ኮቪድን የተመለከተ የምሰጠው ሀሳብ አለኝ። ወላይታ ድቻን ለመውቀስ አይደለም። ይሄ የህይወት ጉዳይ ነው። ተማርምረን እንመጣለን። የተመረመርንበት ወረቀት እና ቴሴራ ሊተያይ ይገባል። ዛሬ አሁን ቼክ ስናደርግ ከእነሱ ሁለት ያልተመረመረ አግኝተናል። እንዲህ ዓይነት ችግር ስላለ አወዳዳሪው አካል ጥንቃቄ ቢያደርግ ጥሩ ነው፤ የህይወት ጉዳይ ስለሆነ።”

👉ዘርዓይ ሙሉ ከድል ስለታረቁበት ጨዋታ…

“ከሽንፈት ለመውጣት ከባድ ቡድን ነበር። እንቅስቃሴው ጥሩ ነው እንደተጨነቅነው ግን አይደለም። ዛሬ ተጫዋቾቼ ከፍተኛ መስዕዋትነት ነው የከፈሉት። በጨዋታው እያንዳንዱ ቦታ ላይ ሁሉም የሚችለውን ነው ያደረገው። ዛሬ ሦስት ነጥብ በጣም ያስፈልገን ስለነበር ብዙ ችግር የነበረው አዕምሮ ላይ ነው ፤ እሱ ላይ ነበር የሰራነው። ዞሮ ዞሮ ሦስት ነጥብ አግኝተናል መጀመሪያ ባስቆጠርነው ጎል። ጎሉንም ጠብቀን በእንቅስቃሴም ብልጫውን ወስደን አሸንፈናል።”

👉ደግአረገ ይግዛው በሲዳማ ቡና ስለተሸነፉበት ጨዋታ…

“ወደ ሜዳ ስንገባ ኳሱን ተቆጣጥረን በተለይ ደግሞ መሀል ሜዳ ላይ ብልጫ ወስደን የመጫወት ፍላጎት ነው የነበረን። ሲዳማዎች የነበራቸው ተነሳሽነት በጣም ደስ ይል ነበር። በዚህ አጋጣሚ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። እኛ ጋር ደግሞ ጨዋታውን እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ነበሩ ተጫዋቾቻችን። ያ ከልክ ያለፈ እርግጠኝነት ሜዳ ላይ የምንፈልገውን ነገር እንዳንከውን አድርጎናል። በተለይ በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ የሚገጥሙን ነገሮች የጨዋታውን ውጤት የሚቀይሩ ውሳኔዎች ልጆቻችንን ከእንቅስቃሴ እያስወጡ ነው እና ይህን አወዳዳሪው አካል በትኩረት ቢመለከተው ደስ ይለኛል።”

👉አሸናፊ በቀለ በርካታ ተጫዋቾች ካመጡበት ከአዳማ ጋር ስለመግጠማቸው…

“ከቤተሰብ ጋር እንደመጫወት ነው። አዳማ ለእኔ ሁሉ ነገሬ ነው። ከህዝብ ጋርም ከአመራር ጋርም የነበረኝ ግንኙነት መልካም ነው። አዳማ ሁሌም መልካም ነገር እንዲገጥመው እመኛለሁ። በተከታታይ ዓመታት ለሜዳሊያ ያበቃሁት ቡድን ነው። ባለው የፋይናንስ ችግር ምክንያት ነው ሁላችንም ለመውጣት የተገደድነው እንጂ ጠልተነው አይደለም።”


© ሶከር ኢትዮጵያ