ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የአምስተኛ ሳምንት ዐበይት ጉዳዮችን የምንዘጋው ሌሎች ሊጠቀሱ የሚገባቸው ጉዳዮችን በአራተኛ ክፍል በማንሳት ነው።


👉ችላ የተባለው የጤና ሚኒስትር ማስጠንቀቂያ

የኮቪድ 19 ወደ ሀገራችን መግባት እና መዛመት በእግር ኳሱ ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳረፉ የታወቀ ነው። የዓምናው የውድድር ዓመት እንዲቋረጥ የዘንድሮውም መዘግየቱ እና በተለየ መንገድ እንዲካሄድ መሆኑ በዚሁ የኮቪድ ምክንያት የመጣ ጣጣ ነው።

ዘንድሮ ውድድሩ ዘግይቶ ለመጀመሩ ዋነኛ ምክንያት የነበረው ደግሞ በተገደበ የሰዎች ቁጥርም ቢሆን ውድድሩን ለማከናወን ጉዳዩ የሚመለከተው የጤና ሚኒስተርን ይሁንታ ለመግኘት የተደረገው ጥረት ዋናው ጉዳይ ነበር። በመጨረሻም መንግሥት ፍቃዱን ሰጥቶ እንደ ቅድመ ምርመራ ፣ በዝግ መከናወን ፣ ጥቂት አካላት ሜዳ ውስጥ መገኘት የመሳሰሉ በበርካታ ቅድመ ሁኔታዎች ተቀምጠውለት ሊጉ እስከ አምስተኛው ሳምንት መድረስ ችሏል።

ሆኖም ሲጀመር የነበረው ቁጥጥር እና ስርዓት ከሳምንት ወደ ሳምንት እየላላ ሄዶ ነገር ዓለሙ ወደመረሳቱ ላይ እንዳይደርስ ያሰጋል። ወትሮም ቢሆን ሞቅ ብሎ ጀምሮ እየቀዘቀዘ የሚሄደው የስታዲየም በር ላይ ቁጥጥር አላስፈላጊ እንግልትን ባያስቀርም ሥርዓት ባለው መንገድ ሲሄድ ያለመታየቱ ነገር ዘንድሮም አልቀረም።

የዘንድሮው ግን የህይወት እና የሞት ጉዳይ በመሆኑ በፍፁም በቸልታ ሊታለፍ አይገባም። ይህንን ነጥብ ያነሳነውም በአንድ አንድ ጨዋታዎች ላይ በትሪቡን መቀመጫዎች ላይ በርካታ ሰው ሲታደም በመመልከታችን ነው። የጤና ሚኒስትር ሦስተኛው ሳምንት ላይ ሁኔታዎችን ገምግሞ ማስጠንቀቂያ መስጠቱም ቸል የተባለ ይመስላል። ደጋፊዎች እና ከሚዲያ መቀመጫው ውጪ በቦታው የሚገኙ ጋዜጠኞች ፣ ብዛት ያላቸው የክለብ አመራሮች ፣ ቁጥራቸው የበዙ የጥበቃ አካላት ፣ የሌሎች ቡድኖች የአሰልጣኝ ቡድን አባላት እንዲሁም ሌሎች ግለሰቦች መቀመጫውን ወደ መሙላቱ መቃረባቸው ለትዝብት የሚጥል ሆኖ አይተነዋል። ጉዳዩ ጨዋታዎች የቀጥታ የቴሌቪዥን ሽፋን በሚያገኙበት ሰዓት የታየ መሆኑ ደግሞ ኮቪድ ያልመለሰው ግርግር ወዳጅነታችንን ያሳየ ሆኗል። በመሆኑም ጉዳዩ የመንግሥትን ሊጉን እስከማቋረጥ የሚደርስ ጣልቃ ገብነት ሳያስከትል አወዳዳሪው አካል ሀይ ሊለው ይገባል።

👉በቴሌቪዥን ስለተላለፈ ብቻ ተዐምር የመጠበቅ ዝንባሌ

የሀገራችን እግርኳስ ያለበትን ደካማ ነባራዊ ሁኔታ ሁላችንም የምንረዳው ሀቅ ነው ፤ ይህም እውነታ በአንድ ጀምበር የሚለወጥ እንዳልሆነም እንዲሁ።

በሀገራችን የክለቦች ውድድር ታሪክ የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በከፍተኛ ገንዘብ የሊጎን ስያሜ መብት ብሎም ከሰሃራ በታች ባለው የአፍሪካ ክፍል የተሻለ ተደራሽነት ባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ ሽፋንን ያገኘ ውድድር ነው። ታድያ የስያሜው መብት ስለተሸጠ አልያም በቴሌቪዥን ስለተላለፈ ብቻ በቀደሙት ዓመታት ስንመለከተው ከኖርነው ውድድር ፍፁም የተለወጠ ውድድርን መጠበቅ የዋህነት ነው።

እርግጥ ነው ከላይ የተጠቀስናቸው አዳዲስ ስምምነቶች ለሊጉ ብሎም ለእግርኳሳችን በጥቅሉ ይዘውት የሚመጡት በጎ ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ፤ ነገርግን ያለንበት ነባራዊ ሁኔታን ግን ጠንቅቆ መረዳት ይሻል።

ሊጋችን ፣ ተጫዋቾቻችን ፣ ዳኞቻችን ብቻ ብዙ ብዙ ነገሮቻችን ደካማ ናቸው። ታድያ ደካማ የሙያተኝነት አስተሳሰብ በሰፈነበት እግርኳሳችን በቴሌቪዥን ስለተላለፈ ብቻ ተዓምራዊ ለውጥ መጠበቅ ተገቢ አይደለም።

በኢትዮጵያ ቡናና ሰበታ ጨዋታ ላይ የተከሰተው የዳኝነት ስህተት የዚሁ ነፀብራቅ ነው። የዳኞቻችን አቅም በማሳደግ ረገድ በቂ ሥራዎች ባልተሰሩበት ጊዜው ፈቅዶ የዳግም ምልሰታ ምስሎች የማየት እድሉ ስለተፈጠረ ብቻ ዳኞቻችን ላይ የትችት ናዳ ማውረዱ ትክክል ነው ብሎ ለመውሰድ ይቸግራል።

ይህ እንዳለ ሆነ እጅግ የተሻሉ በሀገር አቀፍ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ውድድሮችን በላቀ ብቃት የሚዳኙ ጥቂት ምስጉን ዳኞች የመኖራቸውን ያህል የረዳት ዳኞች ብቃት ላይ ጥያቄ የሚያስነሱም በመኖራቸው ዳኝነቱን በበላይነት የሚመራው አካል ልብ ሊለው ይገባል። ያም ቢሆም የዳኞች ደካማ ጎኖች ላይ ብቻ የማተኮሩ ልምድም ጥሩ ቀን ያሳለፉ ዳኞችን ጥረት የሚሸፍን ተግባር ነው። በዚህ ሳምንት እንኳን የኢንተርናሽናል አርቢትር በዓምላክ ተሰማ ቆፍጣና የጨዋታ አመራር እና የኢንተርናሽናል አርቢትር ሊዲያ ታደሰ ንቃት የተሞላው ዳኝነት ተጠቃሽ ነው።

👉የተጠባባቂ ተጫዋቾች መቀመጫ ጉዳይ

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ የተጫዋቾችን አካላዊ ጥግግት ለመቀነስ በማሰብ ተጠባባቂ ተጫዋቾች ለወትሮው ከሚቀመጡበትና ከአሰልጣኝ ቡድና አባላት ጋር ከሚጋሩት የሜዳው ክፍል ይልቅ በተመልካቾች መቀመጫ ላይ ዘር ዘር ብለው እንዲቀመጡ ሲደረግ ሰንብቷል።

ነገርግን በዚህኛው ሳምንት በውል ባልታወቀ ምክንያት ለወትሮው ሲቀመጡበት ከነበሩት የተመልካቾች መቀመጫ ስፍራ ወደ ቀደመው የሜዳው ጠርዝ እንዲወርዱ የተደረጉባቸው ጨዋታዎች ነበሩ። ይህም አስገራሚ የነበረ የሳምንቱ ክስተት ነበር።

👉የልጅ አባቱ አሰልጣኝ

ከቀናት በፊት ሦስተኛ ልጁን ያገኘው የድሬዳዋ ከተማው ዋና አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን ቡድኑ ወላይታ ድቻን በረታበት ጨዋታ የመጀመሪያዋ የአስቻለው ግርማ ግብ መቆጠሯን ተከትሎ የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች የአሰልጣኛቸውን ደስታ በማሰብ ያሳዩት የደስታ አገላለጽ ለየት ያለ የሳምንቱ ክስተት ነበር።

👉 የስታዲየም ውስጥ መረጃ አስተላላፊዎች ጉዳይ

በእግር ኳሳችን ውስጥ ካሉ ችግሮች አንዱ ጥቃቅን ለሚመስሉ ጉዳዮች የሚሰጠው አነስተኛ ግምት ነው። በጨዋታ ቀናት በድምፅ ማጉያ የሚተላለፉ መረጃዎች ወጣ ገባነትም ከዚህ ውስጥ ይጠቀሳል። ከዚህ ቀደምም ሞቅ ባሉ የደጋፊን ትኩረት በሚስቡ ጨዋታዎች ላይ ብቻ የሚሰማው የአሰላለፍ ፣ የግብ አግቢዎች እና የተቀያሪዎችን መረጃ ለተመልካቹ የማስተላለፍ ሂደት ዘንድሮም አልፎ አልፎ እየተሰማ በሌላ ጊዜ ደግሞ እየተረሳ ይታያል። በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ሊኖር የሚገባው ይህ ክንውን በአምስተኛው ሳምንት አንድ ጨዋታ ላይ የተዘለለበት ሂደት ደግሞ አግራሞትን የሚጭር ነበር።

ወልቂጤ ከተማ እና ሲዳማ ቡና የተገናኙበት ጨዋታ ሊጀመር ቡድኖች ዕጣ ተጣጥለው ወደ ደረሳቸው የሜዳ ክፍል ይበተናሉ ተብሎ ሲጠበቅ በሜዳው አጋማሽ ላይ ለህሊና ፀሎት ክብ ሰሩ። የዳኛውን ፊሽካ ተከትሎም ስለጉዳዩ መረጃው የሌላቸው በስታዲየሙ የተገኙ ግለሰቦች አብረው የህሊና ፀሎቱ አካል ሆነዋል። ፀሎቱ በምን ጉዳይ እና ለማን እንደተደረገ ግን የሚታወቅ ነገር ግን አልነበረም። ይህ ቸልተኝነት ፈፅሞ ሊደገም የማይገባ ተግባር ሲሆን በሁሉም ጨዋታዎች በወጥነት አስተዋዋቂዎች ተመድበው መረጃዎች መተላለፍ ይገባቸዋል።

በዕለቱ የህሊና ፀሎት የተደረገላቸው በክብር ስማቸው የዌ ደማም ዘርፉ ወልዴ ተብለው ይጠሩ ለነበሩት የሀገር ሽማግሌ ነበር። ለወልቂጤ እግርካስ ክለብ እና ለከተማው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ዕድገት ከፍተኛ የማስተባበር ስራ ሲሰሩ የነበሩት ግለሰቡ የጉራጌ ዞን የባህል ምክር ቤት ሰብሳቢም ነበሩ።


© ሶከር ኢትዮጵያ