ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

ሰበታን ከጅማ በሚያገናኘው ጨዋታ ዙሪያ ቀጣዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በሁለቱ የአዲስ አበባ ክለቦች ተከታታይ ሽንፈት የደረሰበት ሰበታ ወደ ድል ለመመለስ ከጅማ አባ ጅፋር ይገጥማል። በየጨዋታው ግቦችን እያስቆጠሩ የሚገኙት ሰበታዎች በሁለተኛው አጋማሽ የሚያሳዩት መቀዛቀዝ ለሽንፈት እየዳረጋቸው ይገኛል። የነገ ተጋጣሚያቸው ጅማ አብዛኛውን ደቂቃ በራሱ ሜዳ ሊቆይ መቻሉም በቶሎ ግብ ካላገኙ ክፍተትን ፍለጋ የሚያወጡት ጉልበት ኋላ ላይ መልሶ ማጥቃትን ለመቆጣጠር እክል እንዳይሆንባቸው ያስጋቸዋል። የቡድኑ ኳስን ተቆጣጥሮ የመጫወት ምርጫ እና የያዛቸው ተጫዋቾች ባህሪ በብዙ ቅብብሎች ተጋጣሚን ሰብሮ የመግባት ብቃቱን የሚፈትንም ጨዋታ ይጠብቀዋል። በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ያስቆጠረው እስራኤል እሸቱ ፍጥነት እና ጉልበትም በዚህ ሂደት ውስጥ ሰበታን ተጠቃሚ ለማድረግ ለጅማ ተከላካዮች ፈተና ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

ጅማ አባ ጅፋር የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ነጥብ ካሳካ በኋላ ከሰበታ ጋር የሚገናኝ ይሆናል። ሀዋሳ ከተማን እስከመጨረሻ ደቂቃዎች አላፈናፍን ብለው የዋሉት ጅማዎች ለዚህ ከባድ ጊዜ መላ ያገኙለት ይመስላል። በቡድኑ ሙሉ መዋቅር ድጋፍ እየተደረገለት ተጋጣሚውን ይዞ መቆየት እንደሚችል ያሳየው የኋላ ክፍላቸው ራሱን ከስህተት ከጠበቀ ነገም ተመሳሳይ ስኬት ሊያገኝ ይችላል። በእርግጥ የቆሙ ኳሶችን በመከላከሉ ከታየበት ድክመት በተጨማሪ የሰበታ አማካይ ክፍል ተሰላፊዎች የበሰሉ መሆን ያለቀላቸውን ኳሶች በድንገት አድርሰው የጅማን ተከላካይ ክፍል ሊያስቸግሩ መቻላቸው እሙን ነው። ከዚህም በላይ ለጅማ ከባድ ሆኖ የታየው ግን የማጥቃት ሂደቱ ነው። ቡድኑ በርካታ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ቢያገኝም መጠቀም አለመቻሉ በመከላከሉ ብቻ እንዲተማመን አያደርገውም። በመሆኑም ነገ የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ወደ ማጥቃት በሚደረግ ሽግግር ላይ የሚኖራቸው መናበብ ለአባ ጅፋር እጅግ ወሳኝ ይሆናል።

ሰበታ ከተማ የመስመር ተከላካዩ ኃይለሚካኤል አደፍርስን በጉዳት ሲያጣ ሙሉቀን ታሪኩን ከጉዳት መልስ የሚያገኘው ጅማ መሀል ተከላካዩ ከድር ኸይረዲን አልደረሰለትም። ከዚህ በተጨማሪ በሰበታው ጨዋታ ጉዳት የገጠመው እአጥቂው ብዙአየሁ እንዳሻው መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– አምና ሰበታ ከተማ 3-1 ያሸነፈበትን የተሰረዘ ጨዋታ ከግምት ሳናስገባ ሁለቱ ቡድኖች ነገ የመጀመሪያ የሊግ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ፋሲል ገብረሚካኤል

ጌቱ ኃይለማርያም – አንተነህ ተስፋዬ – አዲስ ተስፋዬ – ያሬድ ሀሰን

ፉዓድ ፈረጃ – መስዑድ መሐመድ– ዳዊት እስጢፋኖስ

ቡልቻ ሹራ –እስራኤል እሸቱ – ፍፁም ገብረማርያም

ጅማ አባ ጅፋር (4-2-3-1)

ጃኮ ፔንዜ

ወንድምአገኝ ማርቆስ – መላኩ ወልዴ – ኤልያስ አታሮ – ተመስገን ደረሰ

ጀይላን ከማል – ንጋቱ ገብረስላሴ

ሱራፌል ዐወል – ሙሉቀን ታሪኩ – ሳዲቅ ሴቾ

ሳምሶን ቆልቻ


© ሶከር ኢትዮጵያ