አንጋፋው የእግርኳስ ዳኛ ዓለም ንፀበ ማን ናቸው?

ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ዳኝነት ታሪክ ውስጥ ጨዋታ ከመምራት አንስቶ የጨዋታ ታዛቢ በመሆን እና በርካታ ዳኞችን አስተምሮ በማብቃት የሚታወቁት ብርቱዉ ሰው ዓለም ንፀበ ማን ናቸው?

ኢንስትራክተር ዓለም ንፀበ አባዲ ከአባታቸው አቶ ንፀበ አባዲ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ሙሉ ደስታ በኤርትራ አስመራ ከተማ መጋቢት 16 ቀን 1939 ተወለዱ። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሐድሽ ዓዲ የመጀመሪያ እና የመለስተኛ ደረጃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን ትምህርታቸው ገዛ ከንሻ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል። ሥራ የጀመሩት በአስመራ አዱሊስ ማተሚያ ቤት ሲሆን እስከ 10 ዓመት ከሠሩ በኋላ ወደ አዲስ አበበባ በመዘዋወር ከታህሳስ 14 ቀን 1984 ዓ/ም እስከ 2000 ዓ/ም ሰርተው በጡረታ ተሰናብተዋል።

ኢንስትራክተር ዓለም ከሥራቸው ውጪ የእግርኳስ ፍቅር ስለነበራቸው በ1965 ዓ/ም የሁለት ደረጃ ዳኝነት ኮርስ በመውሰድ ወደ እግርኳሱን ተቀላቀሉ። በየደረጃ እድገታቸው እና ዕውቀታቸውን በማሳደግም በአንደኛ እና በፌደራል በኢንተርናሸናል ዳኝነት እስከ 1988 ዓ/ም አገልግለዋል።

በዳኝነት ዘመናቸው በትጋት እና በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት በማትረፍ በሀገር ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ጨዋታዎችን በብቃት የዳኙት ጋሽ ዓለም ከሀገር ውጭ ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን የሴካፋ ውድድሮችን፣ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎችን የአፍሪካ የክለቦች ውድድሮች በከፍተኛ ሀላፊነት በመምራት ይታወቃሉ።

ዳኝነትን ካቆሙ በኋላ በተለያዩ የእግርኳስ አመራርነት አገልግለዋል። ከ1989-1990 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ በዳኞች ኮሚቴ አባልነት እና ታዛቢነት አገልግለዋል። ከ1991-1995 በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ አባል እና ታዛቢ (ኮሚሽነር)፣ ከ1996-2009 ህመም እስካደረሰባቸው ጊዜ ድረስ በውድድሮች ታዛቢነት (ኮሚሽነርነት) በድምሩ ለ44 ዓመታት ሙያዊ እና ሀገራዊ ግዴታቸውንን በከፍታኛ ትጋት እና ታማኝነት ተወጥተዋል።

ኢንስትራክተር ዓለም በዚህ ሙያ ሲያገለግሉ ለኢትዮጵያ ዳኞች ከጀማሪነት እስከ ኢንተርናሽናል ዳኝነት ያደረሱ እና ዳኛን የማብቃት አቅማቸው ከፍተኛ የነበረ በመሆኑ ያፈሯቸው ዳኞች በተለያዩ ውድድር ምስጉን ዳኞች እንዲሆኑ በአህጉር አቀፍ እና በዓለም አቃፍ ታዋቂ እንደሆኑ ካሉ የሙያ ጓደኞቻቸው በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ እና ለሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ትልቅ ማስታወሻ ሆነው በዳኞች ባለሙያዎች የሚዘከሩ ናቸው።

የካፍ ኢንስትራክተር የሆኑት አንጋፋው ባለሙያ ጋሽ ሽፈራው እሸቱ ስለ ዓለም ንፀበ ይህን ምስክርነት ሰጥተዋል። ” ጋሽ ዓለምን የማውቀው ከደሴ ከመጣሁበት 1965 ጀምሮ ነው። በፌደራል እና ኢንተርናሽናል ዳኝነት አብረን ሰርተናል። ጋሽ ዓለም በህዝብ ዘንድ አመኔታ የነበረው፣ በጨዋታ ላይ ችግር የማይፈጠርበት፣ ሰውነቱ ትንሽ ወፈር ያለ ቢሆንም የአካል ብቃቱ ጥሩ የነበረ፣ የሚፈለግበትን ውሳኔ በሚፈለግበት ቦታ ላይ ደርሶ ውሳኔ የሚሰጥ ከህዝቡ ከበሬታ የነበረው፣ በሙያው ላይ ቀልድ የማያውቅ ቆራጥ የሆነ ሰው ነው። ዳኝነት ካቆመ በኃላ የጨዋታ ታዛቢ በመሆን አውቀዋለው። እከሌን ብሎ የሚያደርገው ነገር የሌለ “ሥራው ያውጣው” በማለት ትክክለኛ ሪፖርት በማቅረብ የሚታወቅ ነው። ወደ አመራርነቱ ከገባ በኃላ ከኔ ጋር ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ በመሆን አሁን የሚገኘውን አደረጃጀት በማዘመን የእርሱ አስተዋፆኦ የጎላ ነው። በተለይ ዳኞችን ከነ አያታቸው እና ትውልድ ስፍራቸው ለይቶ በማወቅ ይታወቃል። እንደዚሁ ሁሉ ወደ ፊት በኢንተርናሽናል ዳኛ ይሆናሉ ብሎ ያሰባቸውን እንዲታዩ በማድረግ ያቀረበው ሀሳብ በእርግጥም እንደተናገረው የነበረው አቅም ያላቸውን ዳኞች ሆነው እስከ ኢንተርናሽናልነት ሲደርሱ ተመልክተናል። ጋሽ ዓለም ቀልድ አዋቂ፣ ታጋሽ ለሙያው ታማኝ የነበረ በሙያው ለሀገሩ አንድ ነገር አበርክቶ ያለፈ ነው። ፈጣሪ የፈቀደውን አድርጓል። ነፍሱን በገነት ያኑረው ነው የምለው።” በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ኢንስትራክተር ዓለም ንፀበ ለአራት ዓመታት በህመም ሲሰቃዩ ከቆዩ በኋላ በታህሳስ 25 ቀን 2013 እኩለ ሌሊት በ74 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ኢንስትራክተር ዓለም በቤተሰብ ህይወታቸውም የሁለት ወንዶች እና የሦስት ሴቶች አባት ነበሩ።


© ሶከር ኢትዮጵያ