“የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ለደጋፊዎቻችንም ለቡድናችንም ትልቅ ዋጋ አለው” ሙሉዓለም መስፍን

በሳምንቱ ተጠባቂ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ነገ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና ከመጫወታቸው አስቀድሞ ሙሉዓለም መስፍን ይናገራል።

ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመጣባቸው ያለፉትን ሦስት ዓመታት ወዲህ እንደርሱ በሸገር ደርቢ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ጎል ማስቆጠር የቀናው ተጫዋች የለም። ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ ነገ ሲጀምር ሁለቱ የአዲስ አበባ ተቀናቃኝ ቡድኖችን በሚያገናኘው ጨዋታ ዙርያ ሙሉዓለም መስፍንን ከጨዋታው አስቀድመን የተወሰኑ ጥያቄዎችን ጠይቀነው ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።

በደርቢ ጨዋታ ጎል እያስቆጠርክ ነው…

ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመጣው ሦስት ዓመት ሆኖኛል። በመጣሁበት ዓመት ጎል አስቆጥሬ ነበር። በተጨማሪም ዓምና በኮሮና በተቋረጠው የውድድር ዓመት አንድ ጎል በድምሩ ሁለት ጎል አስቆጥሬያለው።

ለነገው ጨዋታ ዝግጅት?

የተለየ ዘግጅት አላደረግንም። እንደማንኛውም ቡድን እንደምንዘጋጀው ተዘጋጅተናል። ቡድናችን የማሸነፍ ሙድ ላይ ስለሆነ ለነገው ጨዋታ በጥሩ ሞራል የመነሳሳት መንፈስ ላይ ነው የሚገኘው።

በነገውም ጨዋታ ጎል እንጠብቅ

ጎል ለማስቆጠር የምችለውን ነገር አደርጋለው። ያው እርግጠኛ መሆን አትችልም። ምክንያቱም እኔ አጥቂ አይደለሁም። ሆኖም ግን ጎል ለማስቆጠር የሚቻለኝን ነገር ሁሉ አደርጋለው።

የሸገር ደርቢን ማሸነፍ ምን ትርጉም አለው ?

እንደሚታወቀው ጨዋታው ደርቢ ነው። ምንም እንኳን በተለያዩ ውጤቶች የማይገናኙ የማይፎካከሩ ቡድኖች ቢሆኑም ሁለቱም ብዙ ደጋፊ ያላቸው የአዲስ አበባ ቡድን በመሆናቸው ጨዋታው ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ነው። በዚህ መልኩ ከሌሎች ጨዋታዎች የኛ ደጋፊ በእነርሱ መሸነፍ አይፈልግም። የእነርሱም በተመሳሳይ ነው። ስለዚህ ይህን ጨዋታ አሸንፎ መውጣት በብዙ ትርጉም ትልቅ ዋጋ አለው። የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ለደጋፊዎቻችንም ለቡድናችንም ትልቅ ዋጋ አለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ