ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ድሬዳዋ ከተማ ከመቐለ ሦስት ተጫዋቾችን አስፈረመ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ላይ ደካማ የውድድር ወቅትን እያሳለፈ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ሦስት ተጫዋቾችን አስፈረመ፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ባዘጋጀው የተለየ የዝውውር ህግ መሠረት በትግራይ ክልል ሲጫወቱ የነበሩ ተጫዋቾች በዚህ ዓመት ወደየትኛውም ክለብ ሄደው መጫወት ይችላሉ የሚል ደንብ ማውጣቱ የሚታወስ ሲሆን ይህንንም ደንብ በመከተል በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ እየተደረገ ባለው ውድድር ላይ ሦስት ጨዋታ ተሸንፎ አንድ አቻ በመለያየት አንድም ድል ማድረግ ያልቻለው ድሬዳዋ ከተማ ክፍተት አለብኝ ባለው ቦታ ላይ ሦስት ተጫዋቾችን ከመቐለ 70 እንደርታ በዛሬው ዕለት አስፈረመ፡፡

ብርሃን ኃይለስላሴ የክለቡ አዲስ ፈራሚ ነች፡፡ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቿ ከወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከተገኘች በኃላ በቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመቐለ 70 እንደርታ ተጫውታ አሳልፋለች፡፡ የቀድሞዋ የቅድስት ማርያም እና አቃቂ ቃሊቲ ተከላካይ ፍሬወይኒ አበራ እና በጌዲኦ ዲላ እና ዓምና ደግሞ በአቃቂ ቃሊቲ በመጫወት ያሳለፈችውና ከሰሞኑ ከክለቡ ጋር አብራ የምትገኘው ትንቢት ሳሙኤል ሦስተኛ የክለቡ ፈራሚ በመሆን ወደ ምስራቁ ክለብ ተጉዛለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ