“በሸገር ደርቢ የመጀመርያ ጎሌን አስቆጥሬ እወጣለው” – አቡበከር ናስር

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ነገ ረፋድ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያገናኛል። ከዚህ ተጠባቂ ጨዋታ አስቀድሞ አቡበከር ናስርን አንዳንድ ጥያቄዎች ጠይቀነው ምላሽ ሰጥቶናል።

በታዳጊ እድሜው ኢትዮጵያ ቡናን በመቀላቀል በየጊዜ በሚያሳየው ዕድገት እና ከፍተኛ መሻሻል የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች በመሆን በአንበልነት እስከመምራት ደርሷል። ነገ በሚደረገው በብዙ መልኩ ከወዲሁ የሁሉንም የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ የሳበ ጨዋታ ላይም ከሚጠበቁ ተጫዋቾች ሆኗል። አቡበከር ምንም እንኳ በነጥብ ጨዋታ እስካሁን በሸገር ደርቢ ላይ ጎል አያስቆጥር እንጂ በነገው ጨዋታ ላይ ጎል በማስቆጠር ስሙን ለመፃፍ ያልማል። በአምስት ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ እስከ አሁን አምስት ጎል አስቆጥሮ ለከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ክብር እየተፎካከረ የሚገኘው አቡበከር ናስር ከነገው ጨዋታ አስቀድመን አግኝተነው በጨዋታው ዙርያ ተከታዩን ሀሳቡን አካፍሎናል።

በሸገር ደርቢ ያስቆጠርከው ጎል አለህ ?

እስካሁን የለኝም። በሆነ ወቅት በወዳጅነት ጨዋታ ይሁን በገቢ ማሰባሰቢያ ጨዋታ ላይ የቱ እንደሆነ አላስታውስም ሁለት ለዜሮ ስናሸንፍ ጎል አስቆጥሬያለው። ያው ሁለታችንም ባልተሟላ በታዳጊዎች ገብተን ነው ጎል ማስቆጠሬን የማስታውሰው። ከዚህ ውጭ እንጂ እስካሁን በነጥብ ጨዋታ ጎል አላስቆጠርኩም።

በሸገር ደርቢ የመጀመርያ ጨዋታህ የነበረ ገጠመኝን ታስታውሳለህ?

ሁሉም የሚያስታውሰው ይመሰለኛል። አንድ የተጣለልኝን ኳስ ወደ ፊት በመሄድ ከግብጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቼ የተሰራብኝ ጥፋት ከባድ ነበር። ይህ ሁኔታ በሸገር ደርቢ ላይ ጎል የማስቆጠር አጋጣሚዬን አበላሽቶብኛል። በጣም የሚገርመው ከዛ በኃላ በደርቢ ጨዋታ ተጫውቼ አላውቅም ጉዳት አጋጥሞኝ ወይ ቅጣት ኖሮብኝ ተጫውቼ አላቅም።

ለነገው ጨዋታስ ትደርሳለህ ?

(እየሳቀ) ለነገ ጨዋታማ በጣም ዝግጁ ነኝ። ምንም ከጨዋታው የሚያርቀኝ ምክንያት የለም።

ለጨዋታው ያለህ ዝግጅት ምን ይመስላል?

ያው የተለየ ዝግጅት አላደረግንም። ሆኖም ሁሌም ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ የሚኖረው የደጋፊ ድባብ የተለየ ነው። ያንን መሠረት ያደረገ ዝግጅት ሊኖረን ይችላል። ከዚህ ውጭ ለሁሉም ቡድን የሚኖረን ዝግጅት ነው ለነገው ጨዋታ የሚኖረን።

ከነገው ጨዋታ ጎል እንጠብቅ ?

አዎ ግድ ነው። ምክንያቱም በኮከብ ጎል አግቢነቱ ፉክክር ውስጥ አለሁ። በተጨማሪ ደግሞ ለማሸነፍ ነው የምንገባው። በዚህ ጨዋታ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጌ በሸገር ደርቢ የመጀመርያ ጎሌን አስቆጥሬ እወጣለው ብዬ ተስፋ አድርጋለው።

የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ያለው ትርጉም ?

ዘንድሮ በሊጉ እስካሁን ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን። በዛ ላይ በሀገሪቷ ውስጥ አለ ከሚባለው ተፎካካሪ ቡድኖች ሁለቱ ናቸው። ደጋፊዎቻችን ይህን ጨዋታ ማሸነፍ በጣም ይፈልጉታል። እኛም ይህን ጨዋታ በድል ለማጠናቀቅ እናስባለን። እኔ ኢትዮጵያ ቡና ከመጣው ጀምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን አንዴ ያሸነፍን ይመስለኛል። ሌላውን አቻ እና እነርሱ በማሸነፍ ይበልጡናል። ይሄን ነገር አሁን ለመቀየር ነው ያሰብነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ