ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ5ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መሰረት በማድረግ የሳምንቱን ምርጥ ቡድን እንዲህ አሰናድተናል።

አሰላለፍ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ፍሬው ጌታሁን – ድሬዳዋ ከተማ

በድጋሚ የምርጥ 11ችን ተመራጭ የሆነው ፍሬው በወላይታ ድቻው ጨዋታ ንቁ ሆኖ እና ከስህተት ርቆ ተመልክተነዋል። በጨዋታው የቸርነት ጉግሳን የግንባር ኳስ እና የእንድሪስ ሰዒድን የቅጣት ምት ያዳነበት መንገድም ልዩ ነበር።

ኃይሌ ገብረትንሳይ – ኢትዮጵያ ቡና

ጅብደኛው የመስመር ተከላካይ በዚህም ሳምንት የማጥቃት ስብዕናውን አሳይቷል። ሦስተኛው የቡድኑ ጎል እንድትቆጠር ምክንያት የሆነችውን ኳስም ከራሱ ሜዳ እየገፋ በመግባት መሀል ለመሀል አሾልኮ በመስጠት ቁልፍ ሚና ተወጥቷል። የመጀመሪያው ኳስ ለተቆጠረበት እንቅስቃሴም እንዲሁ ኳስ በመንጠቅ ተሳታፊ ነበር።

ምኞት ደበበ – ሀዋሳ ከተማ

ዳግም የመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ የተመረጠው ምኞት በሀዋሳ እና ጅማ ጨዋታ የትኩረት ነጥብ ሆኗል። በራሱ ላይ ያስቆጠረውን ግብ በግብ ከማካካሱ በላይ ግን በሙሉ አቅሙ ሲያጠቃ ለነበረው ሀዋሳ ከለላ በመሆን በተደጋጋሚ የጅማን መልሶ ማጥቃቶች ከሜዳው አጋማሽ እንዳያልፉ በማድረግ ቁልፍ ሚና ነበረው።

ጊት ጋትኮች – ሲዳማ ቡና

ጊት ለቡድኑ የመጀመሪያ ሦስት ነጥቦች ትልቅ መስዕዋትነትን በጠየቀው ጨዋታ የወልቂጤን ጥቃቶች በድንቅ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ሲያመክን ውሏል። እንደ ቶማስ ስምረቱ እና አህመድ ሁሴን ያሉ ቁመተ መለሎዎችንም በቆሙ ኳሶች ላይ ክፍተት ባለመስጠት ቡድኑን ተከላክሏል።

ኤልያስ አታሮ – ጅማ አባ ጅፋር

ጅማ አባ ጅፋር ሀዋሳን ፈትኖ ውሎ አንድ ነጥብ ባሳካበት ጨዋታ ላይ ስራ በዝቶበት በዋለው የተከላካይ ክፍል ውስጥ ኤልያስ አታሮ ትልቅ ሚና ነበረው። ከግራ መስመር ተከላካይነት ወደ መሀል ተከላካይነት የዞረው ጥንቁቁ ኤልያስ እንደብሩክ በየነ ያሉ ወሳኝ አጥቂዎችን እንቅስቃሴ ታፍኖ እንዲቀር ምክንያት ሆኗል።

አማካዮች

ብርሀኑ አሻሞ – ሲዳማ ቡና

ለመጀመሪያ ጊዜ በቀዳሚው አሰላለፍ ውስጥ የተካተተው ብርሀኑ ከዮሴፍ ዮሀንስ ጋር ያለውን ስኬታማ ጥምረት ዳግም አሳይቷል። ሲዳማ ያጣውን ከኃይል አጨዋወት በራቀ መንገድ የተጋጣሚን አማካዬች የመቆጣጠር ኃላፊነት በአግባቡ ተወጥቷል።

ኤልያስ ማሞ – ድሬዳዋ ከተማ

ኤልያስ አሁንም የድሬዳዋ ከተማ የማጥቃት ሂደት ቁልፍ ተጫዋች መሆኑን ያሳየበትን ሳምንት አሳልፏል። የመታት ድንቅ የቅጣት ምት በግቡ አግዳሚ ብትመለስበትም ለሙኸዲን ሙሳ ግብ መቆጠር ምክንያት የሆነችውን ኳስ ያመቻቸበት መንገድ የቡድኑ ወሳኝ ግብ ቀጥተኛ ተሳታፊ አድርገዋለች።

ታፈሰ ሰለሞን – ኢትዮጵያ ቡና

ታፈሰ በሰበታው ጨዋታ በታታሪነት የተሞላ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ውሏል። የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር ኳስ ቀምቶ ማጥቃቱን በማስጀመር እንዲሁም ሦስተኛውንም ግብ አመቻችቶ በማቀበል ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆኗል። በእንቅስቃሴም ሜዳ አካሎ በመጫወት ለተጋጣሚውን አማካዮች ፈተና ሆኖ ውሏል።

አጥቂዎች

ሀብታሙ ታደሰ – ኢትዮጵያ ቡና

የግራ መስመር አጥቂነት ሚና ተሰጥቶት ጨዋታውን የጀመረው ሀብታሙ ከአማካይ ክፍሉ ጋር ጥሩ መናበብን አሳይቷል። አጥቂው የመጀመሪያዋን ግብ አመቻችቶ ሲያቀብል ሁለተኛውን ደግሞ ባልታሰበ መልኩ በቀጥታ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሯል።

ሳሊፉ ፎፋና –ሀዲያ ሆሳዕና

ኮትዲቯራዊው የፊት አጥቂ ቡድኑ አዳማ ከተማን በረታበት ጨዋታ ተከላካዮችን ሲረብሽ ውሏል። ግዙፉ አጥቂ ሦስተኛውን ግብ ከማስቆጠሩ ባለፈ በአይዛክ ኢሲንዴ ተጨርፎ ከመረብ ላረፈው የመጀመሪያ ግብም በግንባር በመግጨት መነሻ ሆኗል።

ሙኽዲን ሙሳ – ድሬዳዋ ከተማ

ለሁለተኛ ጊዜ የመጀመሪያ አሰላለፍ ዕድልን ያገኘው ሙኸዲን በድቻው ጨዋታ ፈጣን አጥቂ መሆኑን ያሳየበትን ጨዋታ አሳልፏል። በጨዋታው ከቡድን ጓደኞች ጋር ጥሩ ቅንጅት በማሳየት የግል ብቃቱን ያሳየበትን ግብ ከማስቆጠሩም በላይ በመጨረሻ ደቂቃ የግቡን መጠን ሁለት ለማድረስ ተቃርቦ ነበር።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን ያሳካበት ጨዋታ ቀላል አልነበረም። አሰልጣኝ ዘርዓይ ከድል የራቀውን ቡድን ተነሳሽነት ከፍ በማድረግ እና ዳግም በጨዋታ ላይ በተከሰተ ጉዳት የተፈጠረውን ክፍተት በመድፈን ሲዳማ እስከመጨረሻው ታግሎ ውጤት ይዞ እንዲወጣ አስችሏል።

ተጠባባቂዎች

ፋሲል ገብረሚካኤል – ሰበታ ከተማ
ፈቱዲን ጀማል – ሲዳማ ቡና
እንየው ካሣሁን – ፋሲል ከነማ
ዳዊት ተፈራ – ሲዳማ ቡና
ፀጋዬ ብርሀኑ – ወላይታ ድቻ
አቤል ከበደ – ኢትዮጵያ ቡና
አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና


© ሶከር ኢትዮጵያ