የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የትኩረት ነጥቦች

የ2013 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በተበታተነ መልኩ ቅዳሜ ተጀምሯል። በዚህ ውድድር መክፈቻ ጨዋታዎች እና በአጠቃላይ በውድድሩ ላይ የታዘብናቸው ጉዳዮችን እንደሚከተለው ቃኝተናል።

-ስሜታዊ አሰልጣኞች

በከፍተኛ ሊግ ደረጃ የሚደረጉ ውድድሮችን ለሚከታተል ሰው በስሜታቸው የሚነዱ እና ለቁጥጥር አስቸጋሪ የሆነ የአሰልጣኞች ባህሪን መመልከት የተለመደ ክስተት ነው። ይህ ችግር በሊጉ ረጅም አመታት ካሰለጠኑት አሰልጣኞች እስከ አዳዲሶቹ የሚታይ የጋራ ችግር ነው።

አሰልጣኛች ሜዳ ሲገቡ ዋነኛ አላማቸው መሆን የሚገባው የቡድኑን መንፈስ መጠበቅ ቡድናቸው ከጨዋታው አዎንታዊ ውጤት ይዞ እንዲወጣ መጣር እንጂ ከዕለቱ የጨዋታ ዳኞች ጋር አላስፈላጊ ሰጣ ገባ ውስጥ በመግባት የሚገኝ ይህ ነው የሚባል ትርፍ አለመኖሩን ሊረዱ ይገባል። በተለይ በምድብ ሀ እና ለ የመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታዎች የተዛብናቸው አንዳንድ ገጠመኞች ስሜትን በመቆጣጠር ረገድ ያልተሰሩ ቀሪ የቤት ስራዎች ስለመኖራቸው ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነበር።

-የኮቪድ 19 ጥንቃቄ ጉድለት

በ2013 የሀገር ውስጥ ውድድር በተመረጡ ቦታዎች ላይ ከመደረጋቸው አንፃር ቡድኖች ከጨዋታዎች 72 ሰዓት በፊት ምርመራ የቡድን አባላቶቻቸው የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በማድረግ ውጤቱን ማሳወቅ እንደሚገባቸው ደንቡ ላይ በተቀመጠው መሠረት ክለቦች ተጫዋቾች በማስመርመር ውጤታቸውን ቢያሳውቁም ተጫዋቾቻቸውን መቋጣጠር ረገድ ግን ክፍተቶች ይስተዋላል።

ምርመራ የተደረገላቸው ተጫዋቾች በተወሰነ ስፍራ ላይ ተለይተው እንዲቆዩ ቢጠበቅም የአንዳንድ ቡድን ተጫዋቾች ከማረፊያ ቦታቸው ወጥተው በተለያዩ ስፍራዎች መታየት ቡድኑቹ ከማስመርመር በዘለለ በተጫዋች ላይ ቀጣይነት ያለው ክትትል ማድረግ ላይ ያላቸውን የላላ አሰራር መፈተሽ ይኖርባቸዋል።

– አይበገሬዎቹ ለገጣፎ ለገዳዲ እና ደሴ ከተማ

በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ ለገጣፎ ለገዳዲ በ45ኛው እንዲሁም ደሴ ከተማ በ30ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ተጫዋቾቻቸውን ቢያጡም በተጋጣሚያቸው ላይ የጨዋታ ብልጫ ሳይወሰድባቸው ጨዋታውን ተቆጣጥረው ከጨዋታቸው መልካም ውጤቶችን ይዘው መውጣት ችለዋል። ይባስ ብሎ ደሴ ከተማ በጎዶሎ ተጫዋች ከመመራት ተነስተው ማሸነፍ መቻላቸው የቡድናቸውን ተነሻሽነትና ጥንካሬን ገና በመጀመሪያው ሳምንት አስመስክረዋል።

– ቆራጥ ዳኝነት

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድሩ በራሱ ከፍ ያለ ጫና እና ውጥረት የተሞላበት መሆኑ ለዳኞች ጨዋታዎችን ከባድ ሲያደርግባቸው ይስተዋላል።

በዚህ ሳምንት ጅማሮውን ባደረገው የምድብ ሀ ጨዋታዎች ሁለት የመሀል ዳኞች ያሳዩት ቆራጥ የሆነ የውሳኔ አሰጣጥ እንዲሁም ጨዋታውን ተቆጣጥረው የመሩበት መንገድ ለቀጣዩ የውድድር ሂደት ተስፋ ሰጪ ሆኖ ተመልከተነዋል።

– የመከላከያ አመራሮች

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከወረደ ሁለት ዓመታቶችን ያሳለፈው መከላካያ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ከቀጠረ በኃላ ያደረገው የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታኔ በድል ተውጥቷል። በጨውታውም ዕለት የቡድኑ የቦርድ አመራሮች በጨዋታው ስፍራ በአካል በመገኘት ቡድኑን ሲያበረታቱ ተስተውሏል።

ይህም በክለቡ አመራሮች ዘንድ ቡድኑን ወደ ቀደመው የስኬት ዘመኑ የመመለስ ቁርጠኝነት ስለመኖሩ በማሳያነት ሊወሰድ የሚችል ተግባር ነው።

-የከፍተኛ ሊግ ቡድኖች መልካም ተግባር

በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ የሆኑትና በገጠማቸው የፋይናንስ ችግር ወደ ድሬዳዋ ውድድራቸውን ለማከናወን ጉዞ ማድረግ ያልቻሉትን ባቱ ከተማዎች ለመደገፍ ለውድድር ባቱ የከተሙ ክለቦች እጅግ በጎ የሆነ ተግባርን ፈፅመዋል።

ክለቦቹ የባቱ ከተማን መለያ በብዛት በመግዛትና በተናጥል የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ ተስተውሏል። ይህም ፍፁም ቅንነት የተሞላበት ተግባር ሊመሰገን የሚገባ ተግባር ነው።

– መከላከያና የኮቪድ ምርመራ

ወትሮም ንትርክ እና እንከን የማያጣው ከፍተኛ ሊግ በመጀመሪያው ሳምንት ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከመከላካያ ባገናኘው ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ውዝግብ ተፈጥሯል።

በህክምና እና በሊግ ኮሚቴው መካከል ውዝግብ የፈጠረው ጉዳይ እንደ ክለቦች ገለፃ ከሆነ መከላካያ የኮቪድ ምርመራ ያደረገው ከ72 ሰዓት በፊት ነው። ይህም ህጉ ከሚፈቅደው ውጭ ነው በሚል ቅሬታቸውን ለኮሜቴው አቅረበዋል።

– በወጥነት የማይመራው የከፍተኛ ሊግ ውድድር

በታህሳስ 24 ይጀምራል ተብሎ እቅድ የወጣለት የክፍተኛ ሊግ ውድድር በእቅድ ያለመመራቱ ችግር ውድድሩን ለከፍተኛ ኪሳራ ይዳርጋል።

ቆራጥነት የሆነ አመራር ሰጪነት የጎደለው ስለመሆኑ ዘንድሮም ከወዲሁ እየታየ ሲገኝ ምድብ ሀ ለሚዲያ በተገለፀበት ሰዓት እና ቦታ ሲደረግ በአንፃሩ ምድብ ለ አስቀድሞ በተያዘለት ታህሳስ 24 ቀን አንድ ጨዋታ ብቻ ሲደረግ ምድብ ሐ ደግሞ ገና በ27 የሚጀመር ይሆናል።

ለንትርኮች በር የሚከፍተው የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ጉዳይ

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በምድብ ሀ 9 ቡድኖች እንዲሁም በምድብ ለ እና ሐ 12 ቡድኖች ይካፈሉበታል። በየምድቦቹ ተሳታፊ ክለቦች እኩል ባልሆኑበት ሁኔታ የውድድር ኮከብ ግብ አስቆጣሪዎች በምን መንገድ እንደሚለዩ በግልፅ በውድድር ደንቡ ላይ አለመቀመጡ በቀጣይ ጊዜ ለንትርክ በር ሊከፍት የሚችል ስለሆነ ከወዲህ ትኩረት ተሰጥቶት ሊስተካከል ይገባል።

የኮቪድ ምርመራ ሒደት

በ2013 ውድድር አመት በሊጉ አዲስ የሆነው ነገር የኮቪድ ምርመራ ሲሆን ለዚህ የሚሆን የምርመራ አካላቶች በውድድር ቦታ የሚገኙ ሲሆን የሚስፈልገውን ቅድመ ሁኔታዎች ቅድም ማሳወቅ እንደተነገረ ቢታወቅም በእየለቱ ሳይሰለቹ የመከናወን ግዴታዎች ማሳወቅ ለምርመራ የሚስፈልጉ እቃዎችን በበቂ ሁኔታ ማያዝ ከዚህ በተጨማሪ የቡድኖች የምርመራ ቀን እና የውጤቱ ቀን ማሳወቅ ውጤቱን በሚስጥራዊነት መያዝ ያስፈልጋል።

የስራ ድርሻን ለይቶ አለማወቅ

በከፍተኛ ሊግ ውድድር ወትሮም ሁሉም ፈላጭ ቆራጭ በሆነበት አካሄድ የመጣበት ሂደት ውድድሩን ይበልጥ ያከረረው ሲሆን ዘንድሮም ይህ ነገር ከጅምሩ ይሳታዋላል ደንቦችን እና ቅድመ ውድድሮች ዝግጅት ላይ ቀድሞ ማለቅ ያለበት ጉዳይ ሳያልቅ ሜዳዎች ላይ ይህ ይፈቀዳል ይህ አይፈቀድም ለእገሌ ቡድን ተፈቀደ ለእገሌ ቡድን ተከለከለ የሚሉት ሁኔታዎች ይበልጥ ነገሮችን ማክረር እንጂ የመፍትሔ አካል መሆን አይችሉም በዚህም ምክንያት ቡድኖች ላይ ሆነ ኮሜተው በተጠያቂነት መንፈስ ሊሰሩ ይገባል።

– የዳኝነትን ውሳኔ በፀጋ አለመቀበል

በከፍተኛ ሊግ ውድድር ውድድሩን ይበልጥ አሰልቺ እና ውጥረት የሙላበት የሚደርጉት የዳኝነት ውሳኔን በፀጋ አለመቀበል አንዱ አካል ነው። በዚህ ሳምንት የተደረጉት ሁለቱ ምድቦች ጫዎታ ላይ እንዲ አይነቱ ተግባር የተስታዎለ ሲሆን አወዳዳሪው አካል መቆጣጠር ካልቻለ ውድድሩ ከመርህ ሊርቅ እንደሚችል ያጠፏትንም ዳኞች በቅርብ ሆኖ ቅጣትም ሆነ አስተምሮ ማድረግ የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት።

ችላ የተባለው የተጫዋቾች የመለያ ቁጥር ጉዳይ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ክለቦች በአመዛኙ በሜዳቸውና ከሜዳቸው ውጭ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የሚገለገሉባቸው ሁለት አለፍ ሲል ደግሞ ሦስት የተለያየ የቀለም አማራጮች የተዘጋጁ መለያዎች አሏቸው።

በእነዚህ የተለያዩ መለያዎች ላይ ግን የተጫዋቾች መለያ ቁጥሮች ግን ወጥነት ሲጎድላቸው ይስተዋላል። በተለይም በእርጅና ምክንያት የቁጥራቸው ቀለም የለቀቀ፣ ከርቀት መለየት የማያስችሉ ደቃቅ እና የቀለም ስብጥራቸው ያልተመጠነ መለያዎችን በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታዎች ተስተውሏል።

ምንም እንኳን ይህ ችግር በከፍተኛው የውድድር እርከን የሚስተዋል ቢሆንም አወዳዳሪው አካል በትኩረት ሊመለከተው ይገባል።


© ሶከር ኢትዮጵያ