ሪፖርት | ጅማ አባጅፋር ከሰበታ ከተማ ነጥብ ተጋርቷል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ጅማ አባጅፋር ለረጅም ደቂቃ ሲመራ ቆይቶ በስተመጨረሻ ነጥብ ለመጋራት ተገዷል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በኢትዮጵያ ቡና ከተሸነፈው ስብስባቸው ስድስት ለውጦችን በማድረግ ምንተስኖት አሎ፣ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ፣ ጌቱ ኃይለማርያም ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ፣ ያሬድ ሀሰን እና ታደለ መንገሻ በመጀመሪያ ተመራጭነት ሲጀምሩ በጅማ አባጅፋሮች በኩል ከሀዋሳ ከተማ ነጥብ ከተጋራው ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ሙሉቀን ታሪኩ እና ሮባ ወርቁን በብዙዓየሁ እንደሻው እና ጄይላን ከማል ምትክ ተጠቅመዋል።

ከጅምሩ አንስቶ ጅማ አባጅፋሮች በሁለቱ መስመሮች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው መከላከልን ምርጫቸው ሲያደርጉ በአንፃሩ ሰበታ ከተማዎች በተሻለ ኳስን መቆጣጠር ቢችሉም ከመሀል ሜዳ በዘለለ በሜዳው የላይኛው ክፍል እምብዛም መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል።
በ26ኛው ደቂቃ ጅማ አባጅፋሮች ሰበታ ሳጥን ጠርዝ ላይ ያገኙት የቅጣት ምትን ሮባ ወርቁ አክርሮ በመምታት አስቆጥሮ ጅማዎችን መሪ ማድረግ ችሏል።

ቀዝቃዛ መልክ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በ41ኛው ደቂቃ ያሬድ ሀሰን ያቀበለውን ኳስ እስራኤል እሸቱ ከሳጥን ውስጥ በአስገራሚ መልክ ከሳተው ኳስ በተጨማሪ ከተሻጋሪ ኳሶች እስራኤል እሸቱና ፉአድ ፈረጃ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን አምክነዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ውጤቱን ለመቀልበስ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ቡልቻ ሹራ ፣ ናትናኤል ጋንቹላ እና ፍፁም ገ/ማርያምን ቀይረው ቢያስገቡም በእንቅስቃሴ ረገድ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ነገርን ማሳየት ሳይችሉ ቀርተዋል።

ጅማ አባጅፋሮች በሁለተኛው አጋማሽም ተግተው ቢከላከሉም በ81ኛው ደቂቃ መስዑድ መሐመድ በጅማ አጋማሽ ወደ ግራ ካደላ ቦታ ያሻማውን ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ፍፁም ገ/ማርያም በግንባሩ በመግጨት ሰበታ ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል።

ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ 1-1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ