ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የአዲስ አበባው የሊጉ መርሐ ግብር የመጨረሻ ጨዋታን የተመለከቱ ጉዳዮችን እንዲህ አንስተናል። 

ባህር ዳርን ከረቱ በኋላ በሲዳማ የተሸነፉት ወልቂጤዎች ወደ ድል ለመመለስ እስካሁን ሙሉ ነጥብ ካሳካው ሀዲያ ሆሳዕና ጋር ይፋለማሉ። ከሲዳማው ጨዋታ በኋላ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በሰጡት አስተያየት በወቅቱ የነበረው ከተጋጣሚያቸው የወቅቱ ድክመት አንፃር የተፈጠረው የተጫዋቾች የማሸነፍ እርግጠኝነት ስሜት በነገው ጨዋታ ይኖራል ተብሎ አይገመትም። በዚህም ቡድኑ ከሀዲያ ወቅታዊ አቋም አንፃር በተሻለ መነሳሳት ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። ነገር ግን ከሲዳማ ጋር በተወሰኑ የጨዋታው ክፍሎች የተመለከትነው ወደ መከላከል በሚደረግ ሽግግር ወቅት ያለው መበታተን ካልተስተካከለ ለተጋጣሚያቸው ፈጣን አጥቂዎች አሳልፎ የሚሰጣቸው ይሆናል። ፊት መስመር ላይም አሁንም ተደጋጋሚ ለውጦችን እያስተናገደ ያለው እና በወጥነት የሚተማመንበትን ሁነኛ አጥቂ ማግኘት ያልቻለው ወልቂጤ ከጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ባለቤቱ ተጋጣሚው ከባድ ፈተና እንደሚገጥመው መናገር ይቻላል። በሌላ በኩል ስብስቡ እንደ ያሬድ ታደሰ ፣ አብዱልከሪም ወርቁ እና ፍሬው ሰለሞን ዓይነት ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋቼችን የያዘ በመሆኑ በፈጣን ጥቃት ውስጥ ተጋጣሚውን ማስከፈት የሚችልበት ዕድል ስለመኖሩ መካድ አይቻልም።

ሀዲያ ሆሳዕና ሙሉ ነጥቦችን የሰበሰበ ብቸኛ ክለብ በመሆን የአዲስ አበባ ቆይታውን ለማጠናቀቅ የነገው ጨዋታ ብቻ ይቀረዋል። ቡድኑ በውድድሩ መጀመሪያ ላይ ከነበረው የመከላከል ጥንካሬ በተጨማሪ ጎል የማግቢያ አማራጮቹም እየሰፉ መምጣታቸው ይበልጥ አስፈሪነትን ጨምሮለታል። ከዳዋ ሆቴሳ በተጨማሪ የሳሊፉ ፎፋና እና ቢስማርክ አፒያ ተነቃቅቶ መታየት ተቀይሮ በመግባት ልዩነት መፍጠሩን ካላቆመው ዱላ ሙላቱ ብቃት ጋር ተደምሮ ለጎል ቅርብ የሆነ ይመስላል። አማካይ ክፍሉ ላይም የእነ ተስፋዬ አለባቸው ተፈላጊውን የተከላካይ መስመር ሽፋን መስጠት እና የነካሉሻ አልሀሰን የማጥቃት ቀጥተኛ ተሳትፎ የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ቡድን ነገም በሙሉ ጥንካሬ ልናየው እንደምንችል የሚጠቁም ሌላው ነጥብ ነው። በእንደዚህ ዓይነት የተሟላ ቅርፅ ላይ የሚገኙ ቡድኖች ከፍ ባለ የራስ መተማመን ምክንያት የሚፈጥሩት መዘናጋት የሚያስከፍላቸው ዋጋ በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ከነገው ጨዋታ በፊት ትኩረትን የሚሻ ጉዳይ ይመስላል። በተለይም ከወገብ በታች ያለው የቡድኑ ክፍል የወልቂጤን ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋቾች በማቆሙ ረገድ መዘናጋት ከታየበት ግብ ላያስተናግድ የሚችልበት ምክንያት አይኖርም።

በጨዋታው ወልቂጤ ከተማ በጉዳት ምክንያት የኋላ መስመር ተሰላፊዎቹን ስዩም ተስፋዬ እና አሚን ነስሩን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና ከመሀመድ ሙንታሪ ቅጣት ውጪ ሙሉ ስብስቡን የመጠቀም ዕድል እንዳለው ሰምተናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በተሰረዘው የውድድር ዓመት ወልቂጤ 2-1 ካሸነፈበት ጨዋታ ውጪ ቡድኖቹ የመጀመሪያ የሊጉ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

ተስፋዬ ነጋሽ – ቶማስ ስምረቱ – ዳግም ንጉሴ – ረመዳን የሱፍ

ያሬድ ታደሰ – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ

ፍሬው ሰለሞን – ሄኖክ አየለ – አሜ መሐመድ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

ደረጄ ዓለሙ

ሱሌይማን ሀሚድ – እሴንዴ አይዛክ – ተስፋዬ በቀለ – ሄኖክ አርፌጮ

ካሉሻ አልሀሰን – ተስፋዬ አለባቸው – አማንኤል ጎበና

ቢስማርክ አፒያ – ሳሊፉ ፎፋና – ዳዋ ሆቴሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ