ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

ቀጣዩ የዳሰሳችን ትኩረት የድሬዳዋ እና ባህር ዳር ጨዋታ ይሆናል።

ተከታታይ ድሎችን በጅማ እና ድቻ ላይ ያሳካው ድሬዳዋ አሁን ደግሞ ባህር ዳርን ይገጥማል። መሻሻሎችን እያሳዩ የሚገኙት ብርቱካናማዎቹ በማጥቃቱ ረገድ የግብ አማራጮቻቸው እየበዙ ነው። ወደ ፊት በመሄዱ እና የተከላካይ መስመሩን በማስከፈቱ በኩል የኤልያስ ማሞን ኃላፊነት አስቻለው ግርማ መጋራቱ አንዱ የቡድኑ ጥንካሬ ሆኖ ታይቷል። ነገም ኤልያስ ከባህር ዳር የተከላካይ አማካዮች ጥምረት ፣ አስቻለውም ከሚኪያስ ግርማ እና ሰለሞን ደሬሳ ጋር በሚገናኙባቸው ቅፅበቶች ድሬዋች ዕድሎችን ስለመፍጠር ያልማሉ። የሙኸዲን ሙሳ ወደ ግብ አስቆጣሪነቱ መምጣትም ለቡድኑ ተጨማሪ ጉልበት ይሆናል። አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን ከሁለቱ ናሚቢያዊያን አጥቂዎች ሌላ የሙኸዲን ጥሩ አቋም ላይ መገኘት ምርጫቸው እንዲሰፋላቸው አድርጓል። ነገም ድሬዎች ከአማካይ ክፍሉ የሚነሱ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች ለእነዚህ አጥቂዎች ከግብ ጠባቂ ጋር የሚያገናኙ የመጨረሻ ዕድሎች እንዲፈጥሩላቸው ይጠብቃሉ። የኤልያስ ማሞ የቆሙ ኳሶችም ለብርቱካናማዎቹ ተጨመሪ የግብ መፍጠሪያ አማራጫቸው እንደሚሆኑ ይታሰባል።

ከድል ከራቀ ሁለት ጨዋታዎች ያለፉት ባህር ዳር ነገ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሞት ሽረት ትግል እንደሚያደርግ ይጠበቃል። በእርግጥም የፋሲሉ ጨዋታ የተጠናቀቀበት መንገድ ፣ በመጨረሻ ደቂቃ ነጥብ መጣሉ በራሱ የቡድኑን ተነሳሽነት የሚጨምር ነው። ከሁሉም በላይ ግን ቡድኑ በግብ ጠባቂው ሀሪሰን ሄሱ ስህተቶች ምክንያት ዋጋ የከፈለባቸውን ጨዋታዎች ተንተርሶ ለውጥ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ከዛ ውጪ የአፈወርቅ ኃይሉ ወደ ጨዋታ መመለስ የሳምሶን ጥላሁን አለመኖር የፈጠረውን ክፍተት ለመድፈን እንደሚችል የፋሲሉ ጨዋታ ጥሩ ፍንጭ የሰጠ ሆኖ አልፏል። አብዛኛውን የተከላካይ መስመር መሀል ክፍተት የመፍጠር ሚና በፍፁም ዓለሙ ላይ የተጣለ መምሰሉ ግን ቡድኑን ተገማች ያደረግው ይገኛል። በነገውም ጨዋታ ከፍፁም ግራ እና ቀኝ ያሉ አማካዮች እንዲሁም የመስመር ተከላካዮች ጭምር የድሬን የመከላከል ክፍል በመለጠጥ ለአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድን የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚጥሩ ይጠበቃል። በሲዳማ ቡናው ጨዋታ የታየው ዓይነት የባዬ ገዛኸኝ እንቅስቃሴም ስህተት የማያጣው የድሬን የኋላ ክፍል እና ጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ፍሬው ጌታሁንን ከመፈተሽ አንፃር ለጣና ሞገዶቹ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል።

በዚህም ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ በኩል መረጃ የሚሰጠን አካል ባለማግኘታችን የቡድን ዜናውን ማሰናዳት ባንችልም የባህር ዳሮቹ ሳምሶን ጥላሁን ፣ ዜናው ፈረደ እና አቤል ውዱ ከጉዳታቸው እንዳላገገሙ ማወቅ ችለናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት በ 2011 ሲሆን ባህር ዳር በሜዳው፣ ድሬዳዋም በሜዳው በተመሳሳይ 2-1 አሸንፈዋል። ዓምና ባህር ዳር 4-1 ቢያሸንፍም ውድድሩ በመሰረዙ በሪከርድ ውስጥ አይያዝም።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-1-3-2)

ፍሬው ጌታሁን

ምንያምር ጴጥሮስ –ያሬድ ዘድነህ – ፍቃዱ ደነቀ – ኩዌኩ አንዶህ

ዳንኤል ደምሴ

ሱራፌል ጌታቸው – ኤልያስ ማሞ – አስቻለው ግርማ

ጁኒያስ ናንጄቦ – ሙኸዲን ሙሳ

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ፅዮን መርዕድ

ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – አፈወርቅ ኃይሉ

ሄኖክ አወቀ – ፍፁም ዓለሙ – ግርማ ዲሳሳ

ባዬ ገዛኸኝ


© ሶከር ኢትዮጵያ