ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

የሀዋሳ እና የድቻን ጨዋታ ከተመለከተው ዳሰሳችንን እነሆ።

ያለፉትን ሁለት ሳምንታት በሁለት የአጨዋወት ፅንፎች ያሳለፈው ሀዋሳ ነገ በተመጣጠነ የማጥቃት እና የመከላከል ሂደት ወላይታ ድቻን እንደሚገጥም ይጠበቃል። ቡናን በጥብቅ መከላከል ነጥብ የነጠቁት ሀዋሳዎች ነቅለው በማጥቃት ባደረጉት የጅማው ጨዋታ ደግሞ አንድ ነጥብ ተጋርተዋል። የነገው ጨዋታ ግን ከሁለቱ በተለየ የተመጣጠነ ጨዋታ የሚታይበት እንደሚሆን ይታመናል። በዚህም የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የማግኘት ዕቅድን እንደሚተገብሩ ያሚጠነቁት ሀዋሳዎች ከጅማው ጨዋታ የተሻለ ክፍተት የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል። በጎ ለውጥ እየታየበት የሚገኘው የቡድኑ በራስ መተማመንም ተጋጣሚን በማስከፈት እና ዕድሎችን በመጨረሱ የሚፈተንበት ጨዋታ ይሆናል። አማካይ ክፍል ላይ የኤፍሬም ዘካሪያስ እና ወንድምአገኝ ኃይሉ ጥምረት መደጋገም ለዚህ ፋይዳው ከፍ ያለ ሲሆን ቡድኑ ከግራው ዮሀንስ ሴጌቦ በተጨማሪ ኤፍሬም አሻሞን በቀኝ መጠቀም መጀመሩ የማጥቃት ስርጭቱን ተመጣጣኝ ያደረግው ይመስላል። ነገም በተለይም ከሁለቱ አማካዮች የሚነሱ ኳሶች በሁለቱ የመስመር አጥቂዎች በኩል የድቻ ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታሰባል። ከጉዳት የተመለሰው መስፍን ታፈሰም በሙሉ አቅም ከተመለሰ ለአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የማጥቃት ዕቅድ ተጨማሪ ኃይል መሆኑ አይቀርም።

ሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች ያስተናገደው ወላይታ ድቻ በእንቅስቃሴ ደረጃ መጥፎ ቀናትን ባያሳልፍም በሚሰሩ ስህተቶች እና በማጥቃት ጉጉት ዋጋ እየከፈለ ይገኛል። ቡድኑ ግቦች ለማግኘት አብዝቶ ወደ ፊት ሲሄድ ከተከላካይ መስመሩ ፊት የሚፈጠረው ክፍተት እንዲሁም በራሱ የሜዳ ክፍል የሚሰራቸው ግለሰባዊ ስህተቶች ለውጤት ማጣቱ ዳርገውታል። ድቻ በሦስቱም ጨዋታዎች ግብ እያስቆጠረ ለሽንፈት መዳረጉም ለዚህ አንዱ ማስረጃ ነው። ነገም የሀዋሳን የአማካይ ክፍል በበረከት ወልዴ ዙሪያ ክፍተት መስጠት ወጥ ካልሆነው የመሀል ተከላካዮች ጥምረት ጋር ድቻን ለመጨረሻ ጥቃት ማጋለጥ ይሆናል። በሜዳው ቁመት የነበረው የቡድኑ ጥቅጥቅነት ወደ መከላከል የሚደረግ ሽግግር ላይ በቶሎ ካልተመለሰም ለሀዋሳ እጅ እንዳይሰጥ ያሰጋዋል። ድቻ ፊት ላይ የስንታየሁ መንግሥቱን አለመኖር በመሸፈን የፊት አጥቂ ኃላፊነት የተሰጠው ተጫዋች የኋልዮሽ እንቅስቃሴ ከጋብርኤል አህመድ እና ከመሀል ተከላካዮቹ መካከል እንዲቀሳቀስ ማድረግ እንዲሁም የፀጋዬ ብርሀኑ እና እየተቀዛቀዘ ያለው የቸርነት ጉግሳ ከመስመር ወደ ሳጥን ውስጥ የሚያመራ ጥቃት ውጤታማ እንዲሆን መስራት ጥቂቶቹ የቤት ስራዎቹ ይሆናሉ።

ሀዋሳ ከተማ ቅጣት ላይ የነበረው አለልኝ አዘነ እና ጉዳት ላይ የሰነበተው መስፍን ታፈሰን ግልጋሎት ሲያገኝ በድቻ በኩል ከፍንያንስ ተመስገን እና ሰዒድ ሀብታሙ መመለስ ውጪ በድሬዳዋው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው ስንታየሁ መንግሥቱ እና እዮብ ዓለማየሁ ጉዳት ላይ ይገኛሉ።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 6 በማሸነፍ ቀዳሚነቱን ሲይዝ ሀዋሳ 2 ጨዋታ አሸንፏል። በአራት አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ድቻ 13፣ ሀዋሳ 8 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ዘነበ ከድር – ምኞት ደበበ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሐንስ

ወንድምአገኝ ኃይሉ – ጋብርኤል አህመድ – ኤፍሬም ዘካሪያስ

ኤፍሬም አሻሞ – መስፍን ታፈሰ – ዮሐንስ ሴጌቦ

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

ሰዒድ ሀብታሙ

አናጋው ባደግ – አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – መሳይ አገኘሁ

በረከት ወልዴ

ነጋሽ ታደሰ – ኤልያስ አህመድ – እንድሪስ ሰዒድ – ቸርነት ጉግሳ

ፀጋዬ ብርሀኑ


© ሶከር ኢትዮጵያ